“ኢትዮጵያውያን” በምናችን ነው አንድ የሆነው? አንድማ አይደለንም!

በትናንትናው ዕለት “ትናንት አንድ አልነበርንም! ዛሬም አንድ አይደለንም! ለወደፊቱም አንድ ልንሆን አንችልም!“ በሚል ርዕስ ለንባብ ከበቃ ጽሑፍ የቀጠለ ንባብ ነው።

የጽሑፉ ዓላማ፥

ውጫዊ ማንነታችን (ልዩነቶቻችንን) ሕጋዊና ተገቢ የሆነ እውቅና በመስጠት እንደ ሕዝብና እንደ ሀገር ቀጥ አድርጎ ሊያቆመን የሚችል ውስጣዊ ሕብረትንና ውህደትን መፍጠር እንችል ዘንድ ተጻፈ።

ሐተታ

አንድ አንድ ነው። በንድፈ ሃሳብ ደረጃም ሆነ በመርህ ደርጃ ወይም መሬት ላይ ባለው ሐቅ የአንድ ሁለት የለውም። አንድ አንድ ነው። አንድ ሲደመር አንድ ሁለት። አንድ ሲካፈል ለአንድ አንድ ነው። ከራሱ ጋር ከተባዛም ራሱ አንድ ነው። ከተቀናነሰ ደግሞ ዚሮ ነው። ውህደትን በተመለከተ ሊኖረው የሚችለው ትርጉም ግን በመጠኑም ቢሆን ለየት ያለ ነገር አለው። ለዚህም ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጋብቻ የሚናገረውን ቃል ነው።

“ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ይላል (ዘፍ. 2፥24፤ ኤፌ. 5፥ 31)። “ይጣበቃል” እንዲል ጋብቻ (መጋባት/ውህደት) ማለት ምን ማለት እንደሆነ መናገሩ ሲሆን “አንድ ሥጋ” ሲል ደግሞ በባልና በሚስት መካከል ያለውና ሊኖርም የሚገባው እርስ በርስ የመሸካከም፣ በነገሮች ሁሉ የመቻቻል፣ የመስማማት፣ የመደማመጥ፤ የመናበብ ወዘተ በአጠቃላይ ልዩ ቁርኝት፤ አንድ ልብ፤ አንድ ሃሳብ መሆንን የሚያመላክት በባልና በሚስት መካከል ያለ የረቀቀ የግኑኝነት/ውህደት ጥልቅ ትርጉም የሚገልጽ ነው።

ይህ በባልና በሚስት መካከል ያለውን ግኑኝነት ሊፈርስ የሚችልበት ሁኔታ በተመለከተም መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ይላል “እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል”  እንዲል ከሁለቱ አንዳቸው ከትዳር ውጭ/ከሌላ ሰው ጋር ግብረ ስጋ ግኑኝነት (ዝሙት) የፈጸመ እንደሆነ ብቻ ትዳራቸው ሊፈርስ ወይም ሊበተን እንደሚችል ያስረዳል።

 “አሃዳዊነት” ‘Vs.’ “ብዙሐዊነት”፥

 “አንድነት” በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሊኖረው የሚችል ትርጉምና ይዘት  አንስተን እጅግ በጥቂቱ “የአንድነት” ወይም “የውህደት” ትርጉም የተመለከትን እንደሆነ “አሃዳዊነት” አንዱ የውህደት ወይም የአንድነት አይነት ሲሆን ይኸውም፥ ወተትና ውሃ አንድ ላይ መቀላቀል እንደማለት ነው። ይህ ዓይነቱ ውህደት ደግሞ በኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ ዳግም እውን ሊሆን የማይችል፣ ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ ግልጽነትና ፍትሐዊነት የጎደለበት፣ ሚዛኑ የተዛባና አድሉዓዊ ውህደት ለመሆኑ በበቂ ሁኔታ  ካለፉ ሥርዓቶች ታሪክ ለመማር ችለናል።

ሌላኛው የአንድነት ወይም የውህደት ዓይነት ብዙሐንን የሚያሳትፍ ለጊዜው በአማርኛ “ብዙሐዊነት” እንበለው ይኸውም፥ ዘይትና ውሃ አንድ ብርጭቆ ውስጥ እንደማስቀመጥ ማለት ነው። ማንም በማንም ላይ ሳይሰለጥን፤ አንዱ ሌላውን ሳይውጥና ሳያጠፋ፤ ዘይት ዘይትነቱን ውሃ ደግሞ ውሃነቱ እንደጠበቀ የሚፈጥሩት እኩልነት ላይ የተመሰረተ ፍትሐዊና ሚዛናዊ አንድነት፣ ውህደት፣ ወይም ህብረት ማለት ነው።

*      *      *      *      *

በምናችን ነው አንድ የሆነው?

“ኢትዮጵያ” እንደ አገር ከቆመችበትና ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ አስከ ወታደራዊው የደርግ ዘመነ መንግሥት መደምሰስ ያለውን ጊዜ አንዱ በሌላው ላይ የበላይነቱ የሚያሳይበት አሃዳዊ ሥርዓት ስትናጥ የመጣች አገር ስትሆን የኢህአዴግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ያለውን ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ከሞላ ጎደል ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸው በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ብዙሐንን ያሳተፈ ፌዴራላዊ ስርዓት የዘረጋች አገር ሆኖ እናገኛታለን።

ታድያ ቀዳሚ ጥያቄአችን የሚሆነው እውን “ኢትዮጵያውያን” አንድ ነን? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይሆናል። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በጥቂቱ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሊ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የደቡብ ሕዝቦች፣ አፋር፣ ሃራሪ …  ተብለው የሚታወቁ ልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ድምር ውጤት ናት። እንግዲህ እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በምን ሂሳብ ነው አንድ ሊሆኑ የሚችሉ? በምናችን ነው አንድ የሆነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ ማለት “የፋብሪካ ሳሙና” አይደለም። እንደው “አንድ ነን!” ተብሎ ስለ ተጮኸም “አንድ ነን” ማለትም አይደለም።

“የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው!” ሲባል አባባላችን በተጨባጭ አስደግፈን ማስረዳት መቻል፣ በቂና ምክንያታዊ ምላሽ መስጠት አለብን። በምናችን ነው አንድ የሆነው? እግር ኳስ ወዳጆች ኳስ ሜዳ ወጥተን አንድ ባንዴራ ስላውለበለብን? ለጦርነት አንድ ላይ ስለዘመትን? በነገራችን ላይ ለጦርነት መዝመት አንድነታችን የሚያሳይ ከሆነ እርስ በርስ ስንተላለቅበት የኖርን ዘመን ሆነ አሁን ያለው ድምጽ አልባ ቀበሌ ተኮር ጦርነትስ ምን ሊባል ነው? የአንድነት መገለጫ?  እንዲህማ አንቀልድ።

 • ስማችን ልዩ ልዩ፤ 
 • ቋንቋችን ልዩ ልዩ፤
 • ባህላችን ልዩ ልዩ፤
 • ታሪካችን ልዩ ልዩ፤
 • አስተሳሰባችን ልዩ ልዩ፤
 • የኑሮ ዘያችን ልዩ ልዩ፤ 
 • አመጋገባችን ልዩ ልዩ፤
 • አኗኗራችን ልዩ ልዩ፤
 • ማኅበራዊ ሥርዓቶቻችን/እሴቶቻችን ልዩ ልዩ፤
 • ወግና ልምዶቻችን ልዩ ልዩ፤ 

ቀደም ብለን በዝርዝር የተመለከትናቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በምንም ዓይነት መመዘኛ አንድ ሊሆኑ አይችሉም አይደሉምም። [አንድና ሁለት አንድ ናቸው በማለት ሳይንሳዊ ያልሆነ ሙግት አንስተን መነታረክ ካላማረን በስተቀር] ሀገራዊ አንድነት በውጫዊ ማንነት አይለካም የሚል ዝሩው ፍልስፍና ለማስተጋባት ብንሞክር እንኳ “ኢትዮጵያውያን አንድ ነን!” በማለት አፋችን ሞልተን ለመናገር እንደ ሕዝብ አንድ ዓይነት አስተሳሰብና አንድ ዓይነት ልብ አለን ወይ? ነው ጥያቄው፤ የለንም። ቢኖረን ኖሮ ጥያቄው ራሱ እንደ ጥያቄ ለማንሳት ባልተገደድን ነበር። አንድነት ምንድ ነው? ለማለት የተገደድንበት ዋና ምክንያትም ሌላ ሳይሆን አንድነት ስለሌለን ነው።

ጎበዝ! የአቢስንያ ሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ የእርስ በርስ ግጭት፣ የመላላጥና የጦርነት ታሪክ ነው። የለም! የሚል ካለ ደግሞ “አቢስንያ/ኢትዮጵያ” ተኝታ ያደረችበት ዘመን በጭብጥ አስደግፎ ይቅረብ። ካልሆነ ግን ሐቁ ታሪካችን የጦርነት ታሪክ ነው። ጦርነት ደግሞ የአንድነት ምልክት ሊሆን አይችልም። ጦርነት የልዩነት መለያ ነው። ተግባብተንም ሆነ አንድ ሆነን አናውቅምና። እንደው ይህ ሁሉ ውስጣዊም ውጫዊም ልዩነት ኑሮን ብንግባባ ነበር የሚደንቀው።

*      *      *      *      *

አንድ ልብ ወይስ አንዲት ባንዴራ?

አንድ ልብ ካለን በአንዲት ባንዴራ ስር ተጠለልን አልተጠለልን ምንም ለውጥ አይኖረውም። አንድ ልብ ኖሮን በአንዲት ባንዴራ ሥር የመጠለልና የየራሳችን ባንዴራ የማውለብለብ ነገር የምርጫ ጉዳይ ነው የሚሆነው። ሰው አንድ ልብ፣ አንድ ሃሳብ፣ አንድ ግብና አንድ ዓላማ እስካለው ድረስም  በቁጥር እልፍ ቢሆንም ምን ጊዜ አንድ ነው። አንድ ልብ ሳይኖረን አንድ ባንዴራ ብናውለበልብ ግን ራስን ከማታለል አልፎ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።

አንድ ባንዴራ ስላውለበለብን አንድ ነን ማለት አይደንም። ጎበዝ! አንድ ባንዴራ ማውለብለቡ ቀርቶብን አንድ ልብ ኖሮን የየራሳችን ባንዴራ እያውለበለብን በሰላም ተፋቅረንና ተዋደን ብንኖር አይመረጥም ወይ? እንደው እየተበጣበጥን ከመኖር መቶ እጥፍ ነው የሚሻለው።

መቼም የሐበሻ ዘር ስንባል ሁሌ ራሳችንን ከሰው አገር ማነጻጸር አይደል የሚቀናን እንግዲያውስ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት አገራት ምን ትማራለች? ብሎ መጠየቅና ከአውሮፓ ህብረት አገራት ተመክሮ መቅሰም ጥበብ ነው። አንድ ባዴራ ኑሮን ሲያበቃ አንድ ልብ መሆን ካቃተን እንደ አውሮፖ “ለአርባ አራት” ተበጣጥሰን የየራሳችን መንግሥት መስርተን የየራሳችን ባንዴራ እያውለበለብን አንድ ልብ ብንሆን/ቢኖረን ነው የሚሻለው። ጭቅጭቅ የሌለው ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ምኑም ምኑም በወንዝዎ ልጆች ቁጥጥር ስር ሆኖ ራስዎን በራስዎ ስያስተዳድሩ። አይመስሎትም? ሁከትና መበጣበጥ ምን ዋጋ አለው ብለው ነው።  ሰላም ማውረድና መፍጠር የምንችልበት ብዙ ምርጫዎች እያሉን ለምን በሆነ ባልሆነ ስንጨቃጨቅ ውድ ጊዜያአችንን እናጠፋለን? ኧረ ወዲያ! ተበጣጥሰን ማደግ ከተቻለ ተበጣጥሰንም ቢሆን እንሞክረው። ታድያ ተመራርቀን። (ለበለጠ ለምን ተለያይተንም ቢሆን አንሞክረውም? ያንብቡ)

*      *      *      *      *

አንዱ ሌላውን የሚፈልግበት ምሥጢሩ ምንድ ነው?

“አንድነት/ኢትዮጵያ” ሲባል ሌላ መታለፍ የሌለበት ጥያቄ ቢኖር አንድነቱ ያስፈለገበት ምክንያት/ምሥጢሩ ምንድ ነው? ለሚለው ጥያቄ ግልጽ የሆነ መልስ መቀመጥ አለበት ባይ ነኝ። ሲዳማው፣ ጋምቤላው፣ ሶማሌው፣ አፋር … የኢትዮጵያ ክፍል ሆነው እንዲቀጥሉ የሚገደዱበት ምክንያት ምንድ ነው? የእነዚህ “አናሳ” ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና ስልጣን እስከ ምን ድረስ ነው? ለምንድ ነው የምንፈልጋቸው? በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እኩል እንደ አማራው ትግሬና ኦሮሞ የማይሰለፉ ከሆነ ለምንድ ነው የምንፈልጋቸው? ምሥጢሩ ምንድ ነው? በእኩልነት ስለምናምን ነው ወይስ አሁንም በአንድነትና በባንዴራ ስም ለመጨፍለቅ፣ ለማሸት፣ ያለ ልክ ተጠቃሚዎች ለመሆን፣ ታላቅነታችንን ለማስመስከር ነው? ለመሆኑ በእንዲህ ዓይነት የድብብቆሽና የውሸት አንድነት በምትመሰረት አገር አትራፊው/ተጠቃሚው ማን ነው? ትናንት ሁሉም እኩል ተቋዳሽ እንዳልነበረ በታሪክ ያየነው እውነታ ነውና። ኢትዮጵያዊ ነህ እያልክ ከምትገድለኝ “ኢትዮጵያዊነት” ቢቀርብኝስ? [አይቀርብኝም እንጅ! ልብ ይበሉ፡ ኢትዮጵያውነት ዋጋቢስ ነው አላልኩም። መልዕክቴም አይደለም] አይመስሎትም? ወይስ በኢትዮጵያዊነቴ መንገሥተ ሰማያት እገባለሁ ብለው ያምኑ ይሆን? ብሎ የሚያምን አይኖርም አይባልም ብቻ ግን አይጣል ነው።

አንባቢ ሆይ! እርስዎስ ምን ይላሉ? እያንዳንዱ የራሱን ይዞ በራሱ በመቆም ፈንታ ለምንድ ነው አንዱ ከሌላው ጋር መኖር የፈለገው/የሚፈለገው ይላሉ? ተፈጥሮአዊ ነው ብሎ ስለሚያምን? ትልቁ “አናሳውን ብሔር” ስላዘነለትና ስለራራለት?  ወይስ አማራ ያለ ትግራይ፣ ያለ ኦሮሞ፣ ያለ ደቡብ … ወይም ትግራይ ያለ አማራ፣ ያለ ኦሮሞ፣ ያለ ደቡብ … እንዲሁም ኦሮሞ ያለ ደቡብ፣ ያለ አማራ፣ ያለ ትግራይ … ወይም ደቡብ ያለ ኦሮሞ፣ ያለ ትግራይ፣ ያለ አማራ … “መሽቶ አይነጋልኝም!” ወይም “ህይወት አይኖረኝም!” ብሎ ስለሚያምን ነው? ወይስ በውስጠ ወይራ አንዱ ሌላውን ለመመዝበር ነው?

ይብዛም ይነስም ሁሉም እኩል የሆነ መብትና ሥልጣን ከሌለው አንዱ ሌላውን የሚፈልግበት ምክንያት ምንድ ነው? ምሥጢሩ ምንድ ነው ይላሉ? ለዚህ ጥይቄ የሚመለከታቸው አካላት በተለይ በአሃዳዊ ስርዓት የተለከፉ መልስ መስጠት አይጠበቅባቸውም ብለው ያምናሉ? ወደድንም ጠላንም ተድበስብሰንና ተሸዋውደን የምንኖርበት ዘመን አብቅተዋል። ትውልድ አልፎ ትውልድ በተተካ ቁጥር እርስ በርስ እንደተበጣበጥን ለመኖር ምርጫ ካላደርገን በስተቀር አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ብሎ ፖለቲካ ሊኖር እንደማይችል ለሁላችን ግልጽ ሊሆን ይገባል።

*      *      *      *      *

 ምን እናድርግ? (ነጥቦቹ ለመወያያ በተነሳ ርዕስ ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥኑ ናቸው)

 • ለችግሮቻችን እውቅና እንስጥ። [የኢትዮጵያውያን ችግር የብሔር/የጎሰኝነት ችግር ነው!]
 • ልዩነታችንን አምነን እንቀበል። [ምንም በታሪክ አጋጣሚ “ኢትዮጵያዊነት” የሚል መሰጠሪያ ብንይዝም ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ደምር ውጤት መሆንዋን፤ ሁሉም (የብሔር ብሔረሰቦች ማለቴ ነው) እኩል መብትና ሥልጣን እንዳለው አምነን እንቀበል።]
 • ግልጽነት ይኑረን።
 • ለጋራ ጥቅም፣ ኢኮኖሚ፣ መከላከያ፣ ከረንሲ … ወዘተ የሚሉትን መደለያ ቋንቋዎች ትተን አንድነት የተፈለገበት ዋና ምክንያት በግልጽ እናስቀምጥ።
 • ዘለቄታ ያለው ሰላም መፍጠር የሚቻለው በኃይል ሳይሆን ምርጫ ላይ የተመሰረተ መሰባሰብ እንደሆነ አምነን እንቀበል።
 • አሃዳዊነት አገር የሚበትን ጨቋኝ ሥርዓት እንጅ አገር እንደማያቆም እንመን።
 • ብዙሐኑን ያሳተፈ ሚዛናዊና ፍትሐዊ እኩልነት ላይ የተመሰረተ የጋራ አገር ለመገንባት አሮጌ አስተሳሰብ እንሻር።

 

ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንጅ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም! 

 ይቀጥላል

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 17, 2013

Advertisements