ትናንት አንድ አልነበርንም! ዛሬም አንድ አይደለንም! ለወደፊቱም አንድ ልንሆን አንችልም!

ከተራ ጭኸትና መፎክር ያላለፈ፤ መያዣና መቸበጫ የሌለው፤ ልብ አውልቅ፤ ባለቤት ያጣ፤ ግልጽ የሆነ ራዕይና ግብ የሌለው፤ የተዘበራረቀና የተምታታበት፤ አይደለም ሰፊው ሕዝብ ለአንድ ዓላማ ሊያሰልፍ፣ ሊያሳምንና አግባብቶም ከጎኑ ሊያስከትል ቀርቶ እርስ በርስ መስማማትና መደማመጥ ያቃታቸው የሥመ ፖለቲከኞቻችን አስቀያሚና አሳፋሪ መልክና ምንነት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች በሚነሱ ጊዜያዊ ኃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎችና አለመግባባቶች እንደ ባልቴት እየተለጠፍክና እየተንጠላጠልቅ ሕዝብ እንደ መሰላል መወጣጫ በማድረግ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ዘው ብለህ ለመግባትና የሥልጣን ሁሉ ባለ ቤት ለመሆን የሚደረገው ሩጫና ጥድፊያ ሳስበው ኢትዮጵያውያን እስከ ዳግም ምጽዓት ድረስ የሚያስፈልገን ሳናገኝ እንዲሁ እንደጮህን፣ እንደናፈቀንና በሰው አገር ኢምባሲ እንደ ብቅል እንደተሰጣን እንዳናልፍ ነው የምፈራው። 

የጽሑፉ ዓላማ፥

ጽሑፉ በይዘቱ ቀለል ያለ፤ በጣም በስሱ የተዘጋጀ ሲሆን የጽሑፉ ዓላማ ደግሞ ሀገር ወዳድ ዜጎች ለማወያየት ታስቦ የተጦመረ ጽሑፍ ነው። ጽሑፉ ምንም እንኳ በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ ከወትሮ ቀለል ያለ ቢሆንም ምድራችን አሁን ለምትገኝበት የተመሰቃቀለ ገጽታ መፍትሔ ሐሳብ በማበርከት/በመጠቆም ረገድ የራሱ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታመናል።

ማሳሰቢያ፥

አንባቢ ሆይ! ይህን ታሪካዊ ማንነታችን አንስቼ ለመወያያ ሳቀርብ የሕዝቦች ልብ ለመክፈል ሳይሆን የጽሑፉ ዓላማ በሚል ንኡስ ርዕስ ሥር ግልጽ በሆነ ቋንቋ ለመግለጽ እንደተሞከረ አገር ካንጃበበባት አደጋ ለመታደግ እንደ አንድ ዜጋ ግዴታዬን መወጣቴ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ስጠይቅ በአክብሮት ነው።

* * * * *

ሐተታ፥

ትናንት … 

በህይወቴ የሚከብደኝ ነገር ቢኖር ስለ ትናንት [ስለ ስላልነበርኩበት] ዘመን መናገር ነው። በተለይ ታሪክ ነክ ጉዳዮች አንዳንድ ጊዜ ከአረጊቶች ተረት ባልተናነሰ መልኩ እንደ ደራሲው/ጸሐፊው ዝንባሌ፣ ውስጣዊ ምኞት/ፍላጎትና ተልዕኮ በአጠቃላይ ታሪክ ነክ ትረካዎች ከሐቁ እጅግ ርቀው ጸሐፊው እጅ ላይ የወደቀ ሆኖ የምናገኝበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። በተለይ በብዙ ነገር ወደኋላ የቀሩ አገሮች የታሪክ መዛግብት አያያዝና ሳይከለስ፣ ሳይሰረዝ፣ ሳይበረዝና ሳይደለዝ በአግባቡ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ተአማኝነቱ እስከዚህም ነው። እንዲህ ዓይነት ወጥነት የጎደለበት የእርስ በርስ የታሪክ መጣረስና መፋለስ እውን የሚሆንበትምና የሚፈጠርበትም አንድ ራሱ የቻለ ምክንያት አለው።

ቀላል ምሳሌ ላንሳ። ይኸውም፥ የኢትዮጵያ ታሪክ የተመለከትን እንደሆነ [ኢትዮጵያ በስምምነት ሳይሆን በሃይል የተመሰረተች አገር ናት የሚለው አስተሳሰብና አመለካከት እንደተጠበቀ ሆኖ] በአሁን ሰዓት በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ የምትገኝ ኢትዮጵያ ተብላ በምትታወቅ አገር ስር የተጠለሉና የታቀፉ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስለ ምድሪቱ ወጥ የሆነ ታሪካዊ አስተሳሰብም ሆነ አመለካከት የላቸውም። የኢትዮጵያ ታሪክ በአማራ ተወላጅ ጸሐፊ ያለው ሚዛን በኦሮሞ ወይም በትግራይ ተወላጆች እንዲሁም በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የታሪክ ጸሐፊዎች ያለውን ሚዛን አንድ አይደለም።

ምሳሌው ያጠበብነው እንደሆነ “አከራካሪ” የምኒልክ ታሪክ ለተነሳ ርዕስ ጥሩ ምሳሌ ነው። በአማራ ተወላጆች የታሪክ ጸሐፊዎችና ተናጋሪዎች ዘንድ ምኒልክ ማለት ጀግና፣ የተዋጣለት የዲፕሎማሲ ሰው፣ የሰለጠነ፣ ቆፍጣና መሪ ሲሆን በኦሮሞና በትግራይ የታሪክ ጸሐፊዎችና ተናጋሪዎች ዘንድ ደግሞ ምኒልክ ጀግና መሆኑ ይቀርና ምኒልክ ማለት አረመኔ፣ የእናት ጡት ቆራጭ፣ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ፣ ግፈኛ፣ ዘራፊ፣ ከሐዲ (እምነት የሌለሽ)፣ ቤተ ክርስቲያን ሳይቀር የሚዘርፍ ወመኔ፣ ሐሞት የሌለው ሽንታም፣ ሀገር ለባዕዳን አሳልፎ የሸጠ ባንዳ … ወዘተ ዓይነት ሰው ሆኖ ነው የምናገኘው።

በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ “ምኒሊክ ማን ነው? ምን ዓይነት ሰው ነበር? (ግለ ሰብእናው?) የአመራር ብቃቱ? ፖለቲካዊ አስተዳደር (አገዛዙ) ምን ይመስል ነበር? ከበቀለበት ብሔር ውጭ ከሌሎች ብሔር ብሔረሶች ጋር የነበረው ግኑኝነት ምን ይመስል ነበር? ማወቅ እፈልጋለሁ።” ብሎ የምኒሊክ ታሪክ ለማጥናትና ለማወቅ የሚጓጓ ሰው ካለ፤ ቻይናውያን “መንገድ ከመጀመርህ በፊት ለክፉም ለደጉም ደርሰው የተመለሱትን ጠይቅ” እንዲሉ በበኩሌ ለዚህ ሰው ለፍለጋው ስኬታማነት የምመክረው ምክር ቢኖር አንድም ምኒልክ በአካል አግኝቶ መጠየቅ ነው ይህ ካልሰራ ደግሞ በምኒሊክ ዘመን የነበረ ለነፍሱ ያደረ አረጋዊ ሰው አግኝቶ እንዲያነጋግር ብቻ ነው ምክሬን የምለግስለት። ከዚህ ያለፈ በምኒሊክ ዙሪያ የተጻፉ መጻህፍት አገለባብጬ እውነቱን እደርስበታለሁ ማለት ግን ከቅዠት ያለፈ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። ከንቱ ልፋት ነው የሚሆነው። ተጻፉ የሚባሉ መጻህፍት ፉት አድርጎ እንደጨረሰ የተጨበጠ ነገር ስለማያገኝባቸው ዙሮ ዙሮ በምኒሊክ ዘመን የነበረ ሰው ፍለጋ መምጣቱ አይቀርምና። ይህ የምልበትም በቂ ምክንያት አለኝ።

በነገራችን ላይ 2013 ዓ/ም ላይ ሆኖ ስለ ምኒልክ ደግነት፣ ወንድነት፣ አርቆ አሳቢነትና ጀግንነት ሽንጡን ይዞ የሚጮህና የሚሞግት ሰው ሆነ ስለ ምኒልክ ነውራምነት፣ ሌብነት፣ ቅጥፈት፣ ወገበ ነጭነትና ባንዳነት የሚጽፍና የሚያወራ በምኒልክ ዘመን የነበረ የዓይን እማኝ (ቅሪት) ሆኖ ሳይሆን ማንበብ የሚፈልገው (በአወገንተኝነት ወይም ለልዩ ተልእኮ የተጻፉ) ብቻ እየመረጠ አንብቦ እንጅ ሌላ ምስጢር የለውም

ጸሐፊው የአማራ ደም ካለበት ስለ ምኒልክ ቢጽፍ ደግ ደጉን ነው የሚጽፈው። በአንጻሩ ደግሞ ጸሐፊው ከአማራ ብሔር ውጭ የሌላ ብሔር ተወላጅ የሆነ እንደሆነ ደግሞ (የኦሮሞ ሊሆን ይችላል ከትግራይ ሊሆን ይችላል ከደቡብም ሊሆን ይችላል) ከሞላ ጎደል ስለ ምኒሊክ ተቃራኒው ነው የሚጽፈው። የውጭ ዜጎች ጸሐፍት እንደሆኑም አዝነውልን ሳይሆን ራሱ የቻለ ተልዕኮ ያላቸው ሰዎች ናቸው። የምክሬ መሰረትም ይህ ነው። ታሪክ ሂሳብ አይደለም። ታሪክና ሕልም እንደ ፈቺው (እንደ ጸሐፊው) ነውና። ስለ ሌሎች አጼዎችና ነገሥታትም እንዲሁ። ታድያ ይህ ሁሉ የሚያሳየው አንድነታችን ሳይሆን ልዩነታችንን መሆኑ እውቅና ሊሰጠውና ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ለችግሮቻችን እውቅና በመስጠት ነውና ትክክለኛ መፍትሔ ልናገኝ የምንችለው።

ሌላው የአሁኒትዋ ኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት “የምኒሊክ ቤተ መንግሥት” ተብሎ መጠራቱና መታወቁ ታሪካዊና ፖለቲካዊ አንድምታው ምን ዓይነት መልክዕክት እንዳለውና እንደምያስተላልፍስ አስበውበት ያውቃሉ? ለጥያቄው በቂና ምክንያታዊ ምላሽ ካልዎት ማንነትዎና ታሪክዎ ጠንቅቀው የሚያውቁ፤ ስለ ተባለና ስለተነገረ ብቻ የማይደነባበሩ፤ ከነፈሰ ጋር የማይነፍሱ ጭምት ሰው ኖት ማለት ነው። እንግዲያው ለእርስዎ አንድ ባንዴራ ያልነበረን፤ የዛሬ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም ራሳቸው የቻሉ የራሳቸው ሥልጣኔና ታሪክ የነበራቸው መንግሥታት እንደነበሩ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ብሎ አንድ አገር ወይም አንድ ሕዝብ የሚባል እንዳልነበረ ይህች በቂ መልዕክት ናት።

ዛሬም … !

የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በማስመልከት “ለኢትዮጵያውያን” ለመናገር መድፈር ለቀባሪ እንደመርዳት ነው የሚሆነው። አሁን ስለ ምንገኝበት ሁኔታ ብዙ ለማለት መሞከርም በእውነቱ ነገር የአንባቢያን ጊዜ ማባከንና አንባቢን ማሰላቸት ነው የሚሆነው። የኢትዮጵያ ችግር በቅጡ አጥርቶ ማየት የተሳነው ዜጋ ያለ እንደሆነ፤ ወይንም የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ድረ ገጾችና ሚድያዎች የሚያስተጋቡት ጽምጽ እውነት መስሎት የኢትዮጵያ ችግር የዲሞክራሲ፣ የፍትህ ወዘተ ችግር ነው ብሎ የሚያምን ሰው ካለ ከዚህ ቀደም “ኢትዮጵያ፡ ጨወታ ለማሳመር የምትመዘዝ ጆከር ናት!” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የሚጠቁም በማንበብ በቂ ግንዛቤ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ።

በአጭሩ ጥያቄዎቻችን የፈለግነው ቀለማት እየቀባባን ሌላ መልክ ለመስጠትና ለማስያዝ ብንሞክርም “ኢትዮጵያውን” አሁን በዚህ ዘመን የምንገኝበት አሳፋሪ ሁኔታ (ፖለቲካዊ) አንድነታችን የሚያሳይ ነው የሚል ካለ አእምሮውን የጣለ ሰው ብቻ ነው። ትናንት አንድ እንዳልነበርን ሁሉ ዛሬም አንድ አይደለንም። ሰው የሚያየው ጎሳን መሰረት ያደረገ ግጭቶቻችንና ንትርኮቻችን የልዩነቶቻችን ምልክት/ነጸብራቅ ነው።

“ጥሩ ውሀ የጥቅምት ነበርሽ ማን በጠጣሽ፤ ጥሩ ምክር የደሀ ነበርሽ ማን በሰማሽ!”

አሁንም “አዎ! አንድ አልነበርንም።” ወደሚለው መሰረታዊና ታሪካዊ ማንነታችን ልንመጣ ይገባል። በመቀጠልም በጠመንጃ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ላይ ተቀምጠን ኢትዮጵያ ተብላ የምትታወቅ ሀገርም ሆነች ኢትዮጵያዊ ተብሎ የሚታወቅ ሕዝብ የተዳፈነ ማንነት ያለን ሕዝቦች እንጅ አንድ ሕዝብ እንዳይደለን እናስምርበት። [ይህን ስል ምን ለማለት ተፈልጎ እንደሆነ በሚቀጥሉት ተከታታይ ጽሑፎቼ ሰፊ ማብራሪያ እሰጥበታለሁ] ይህን ስናደርግ ወደሚፈለገው ሁሉን በጋራ የሚያሳትፍና ተጠቃሚ የሚያደርግ አገር ገንብተን በሰላም በፍቅርና በመጠባበቅ መኖር ያስችለናል። ይህን ባናደርግ ግን በመግቢያዬ እንደጠቀስኩት “የኢትዮጵያ ሕዝብ/ኢትዮጵያዊ” ተብሎ መጠራቱ ቢያምንበትም ባያምንበትም ሰዎች የኢትዮጵያ ፓስፖርት እስከያዙ ድረስ የምድሪቱ ስም በተነሳ ቁጥር ከርታታ ሕዝብ ተብሎ መታወቁ ይቀጥላል። ትናንት የነበረ ዛሬም ያለ መቆራቆስና ፍጭትም ይቀጥላል። ምን ነው? ቢሉ የያዘም አይለቅም የተያዘም አርፎ አይቀመጥምና። ጥበብ በጎዳና ላይ ትጮሃለች!

ጎበዝ! ታመናል። መታመማችን ደግሞ አምነን እንቀበል ዘንድ ይገባናል። መታመማችን አምነን መድሃኒት ፍለጋ ከተነሳን ደግሞ ለህመማችን መድሃኒት እናገኝ ዘንድ ህመማችን አፍረጥርጠን ልንናገር ይገባል። ይህ ደግሞ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው። አፍ አውጥተን ችግሮቻችን መናገር ያቃተንና እንቢ! ያልን እንደሆነ ግን “በሽታውን የደበቀ መድኃኒት የለውም” እንደሚባለው ህመማችን አፍ አውጥተን እስከምንናዘዛት ድረስ ከነበሽታን እየተሰቃየን መኖራችን ግድ ነው።

በጽሑፉ ቅሪታ ላላችሁና ለተሰማችሁ ግለሰቦች፥

የሲዖል ፈላስፋ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ለመበታተን የኢትዮጵያ ታሪክ አስመልክተው በሰነዘሩት አስተያየት ተስማምተው ሲያበቁ እኔ ስለ ሀገሬ ለመፍትሔ ይሆን ዘንድ በፍቅር እውነት ነው ብዬ የማምንበት መናገር ሆነ መጻፍ የማልችልበት ምክንያት እንዲነግሩኝ ብቻ ነው የምጠይቆት። በጸሐፊው ሃሳብ አለመስማማት መብትዎ ሆኖ ኢትዮጵያ ተከፍላ ለሁላችን እኩል የምትደርሰን አገር እስከሆነች ድረስ ሃሳብን በሃሳብ ከመቃውም ያለፈ ሌላ ስም የመለጠፍም ሆነ የመስጠት ማንም መብት አለው ብዬ አላምንም። የመቃወም መብት እንዳሎት ሁሉ እኔም በሥርዓቱ የመጻፍ መብት አለኝ።

ይቀጥላል

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 16, 2013

Advertisements