ተስፋየ ገብረአብ ከኢሳት ምን ለየው?

ሕዝብ የሚጠቅም፣ አገር የሚገነባ፣ አሳፋሪ ገጽታችንን የሚቀይር፣ ከምንገኝበት በንትርክ የተሞላ ህይወት ለመልካም ነገር አንድ እርምጃ ፈቀቅ የሚያደርግ፣ የሚያግባባ፣ የሚያንጽና የሚረባን፣ ዳቦ የሚያበላ፣ እርቅ ሰላምና ፍቅር የሚያወርድ መነጋገሪያ ርዕስ አይገኝም እንጅ ጉልበት የሚበላ፣ እርስ በርስ የሚያለያይ፣ የሚያናክስ፣ የሚያቧቅስና የሚያነታርክ አይታጣባችሁ ሲለን ለኢትዮጵያውያን የሚሆን መነጋገሪያ ርዕስ አይታጣም።

አንድ ልቤን የሚያደማ ነጥብ ላስቀምጥ። ይኸውም፥ ኢትዮጵያ ለመበታተንና የኢትዮጵያ ህዝብ ለመተረማመስ በተደራጀ መልኩ ለኤርትራ መንግሥት በትጋት እየሰራ የሚገኘው የሻዕቢያ አፍና ጆሮ የሆነው ኢሳት በገንዘብ እየደገፍክ አንድ የሻዕቢያ ሰላይ ተገኘ ተብሎ በተስፋየ ገብረአብ የተባለ ግለሰብ ላይ የተደረገውን ርብርብ ስመለከት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምን ያህል የዘቀጠ፣ ርካሽና ሰው አልባ ስብስብ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ይህ በድጥ ስፍራ ላይ የተቀመጠውን መሰረት አልባ ፖለቲካ የተደገፈ ቅን ልብ ያለው ሰፊው የሀገሬ ሰው ያሳዝነኛል።

ተስፋየ ገብረአብ የተባለ የቀድሞ የደርግ ወታደር ነበር፤ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ታማኝ ሎሌ ሆኖ ሲሰራ የቆዬና በአቅም ማነስ ምክንያት ከነበረበት ኃላፊነት የተጠለዘ፤ ከዚያም ወደ ኬንያ ያቀና በአሁን ሰዓት በአውሮፓ ‘ኒዘርላንድስ’ ነዋሪ የሆነ ኤርትራዊ ለአስራ ሁለት ዓመታት እንጀራችን እየበላ የወይን ጠጃችን እየጠጣ እኛንም ሀገራችንም ሲሰልል የኖረ ግለሰብ መጋለጡና እርቃኑ መውጣቱ እየተቃወምኩ አይደለም።

አለማየሁ መለሰም ሆነ ወልደሚካኤል መሸሻ (ዳኛ) አገራችን ከውስጥም ከውጭም በተፈለፈሉና በተገዙ አገር በቀል አደጋ ጣዮች እየታመሰች ባለችበት ሰዓት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኩራት ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ጋሻ ሁናችኋልና እግዚአብሔር ከክፉ ይጠብቃችሁ። የእኔ ጥያቄ ግን ወዲህ ነው። ከተጠቃሹ “የናት” ጡት ነካሽ ግለሰብ (ተስፋየ ገብረአብ) የጨለማ ሥራና ሰይጣናዊ ግብር ይልቅ ፍጥጥ ባለ መልኩ በኢትዮጵያ ስም የኢትዮጵያ ባንዴራ እያውለበለበ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየሰራ ስላለ መቀመጫው አውሮፓና አሜሪካ ያደረገ የበልዓም አንደበት ስለ ኢሳት ምን አደረግን? ምን አልን? ነው የእኔ ጥያቄ።

ተስፋየ ገብረአብ ይህ ሁሉ አገር የሚያፈራርስና ትውልድ የሚያጨራርስ ሥራ ሲሰራ ደረቱን ገልብጦ ሽንጡን ይዞ “ኢትዮጵያዊ ነኝ!” እያለ ራሱን በቁልምጫ ስም እየጠራ እንጅ “ኤርትራዊ ነኝ!” ብሎ አልነበረም። ወይስ ኢሳት አፍ አውጥቶ “ኢሳት የሻዕቢያ እጅና እግር!” በማለት ማስታወቂያ ሰርቶ እንዲነግረን ነው የምንጠብቀው? በተጨማሪም ኢሳት የኤርትራ መንግሥት ሆነ የሻዕቢያ ተላላኪ ተስፋየ ገብረአብ በመቃወም ዜና ያቀርባል ሐተታ ይሰራል ብለው የሚጠብቁ ከሆነ ደግሞ በእውነቱ ነገር ከማርስ የመጡ ልዩ ፍጡር መሆን አለቦት። እንደው ይህን ስል አንድ አምላካዊ ቃል ትዝ አለኝ። ይኸውም፥ አንድ ወቅት ኢየሱስ ቢማሩም ትምህርት የማይገባቸው ጻፎች ጋር ተገናኝተው ነበርና ሲያስወሩበት የኖሩትን በማስመልከት እንዲህ ሲል ነበር ማፈናፈኛ ያሳጣቸው።

ከኢየሩሳሌም የወረዱ ጻፎችም ብዔል ዜቡል አለበት፤ ደግሞ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል ብለው ተናገሩ። እነርሱንም ወደ እርሱ ጠርቶ በምሳሌ አላቸው። ሰይጣን ሰይጣንን ሊያወጣው እንዴት ይችላል መንግሥትም እርስ በርስዋ ከተለያየች ያች መንግሥት ልትቆም አትችልም፤ ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ ያ ቤት ሊቆም አይችልም። ሰይጣንም ራሱን ተቃውሞ ከተለያየ፥ መጨረሻ ይሆንበታል እንጂ ሊቆም አይችልም።” (የማርቆስ ወንጌል 3፥ 22- 26)

ሻዕቢያ፣ ተስፋየ ገብርአብ ሆነ ኢሳት ከአንድ ምንጭ የተቀዱ መራራዎች ናቸው። ስለሆነም እርስ በርሳቸው ይደጋገፋሉ እንጅ አንዱ ሌላውን የሚያወግዝበት፣ የሚኮንንበትና የሚያጋልጥበት ምንም ምክንያት የላቸውም። ምንም እንኳ በአካል፣  በመልክ፣ በቅርጽና በስም አንድ ባይሆኑ በተልዕኮና በዓላማ አንድ ናቸው። ለምን ራሳችንን እናታልላለን? ኢሳት በድርጅት መልክ ተቋቁሞ በሚድያ – ተስፋየ ገብረአብ ደግሞ እንደ ግለሰብ በሥነ ጽሑፍ ኢትዮጵያን ለመውጋት የተሰለፉ ሁለቱም የሻዕቢያ አጀንዳ አስፈጻሚዎች ጸረ ኢትዮጽያና ኢትዮጵያውያን ናቸው። በተልዕኮና በዓላማ ኢሳት ቀን ሳለ ሰማይ በላዩ ላይ ከተደፋበት ተስፋየ ገብረአብ በምንም ዓይነት መንገድ አይለይም። ታድያ ምን ይሉት አዚም ቢደረግብን ነው ኢሳት ላይ ደርሰን ዓይናችን ከፍተን ማየት የተሳነን/ያቃተን? ግመልን እየዋጥክ ትንኝን ማጥራት ማንን ነው የሚበጀው? ቅዱስ ገብርኤል በተኛሁበት በህልሜ ተገልጦ ካልነገረኝ ከሆነ ነገሩ እንደማይቀናዎት እያወቅኩ ይቅናዎት ብያለሁ። 

የኢትዮጵያ ታሪክ በተመለከተ አቅሜ በፈቀደው በውጭ አገር ሰዎች ሳይቀር የተጻፉ በርከት ያሉ መጻህፍት ለማጥናት ሞክሬ አለሁ። በፍለጋዬም ብዙ የሚቀፉ አገላለጾችና መሰረተ ቢስ ትረካዎች አንብቤለሁ። ታድያ የሲዖል ፈላስፋው ኢሳይያስ አፈወርቂ ሀገራችን ኢትዮጵያ በማስመልከት “ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረች አገር ናት” ሲሉ የተናገሩት መያዣ መጨበጫ የሌለው የዕብደት ቃል የሚስተካከል ግን አንብቤም ሰምቼም አላውቅም። ይሁንና የኢትዮጵያውያን ዓይንና ጆሮ ለማፍረጥና ለመድፈን የተሰለፈ ኢሳት ይህን የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጸያፍ አነጋገር በማስመልከት አንዳች ቃል አልተነፈሰም።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት “ምን-ተስኖት በምላሱ” በዘፈን የሚሰራ መኪና ቢያስተዋውቁና ለገበያ ቢያቀርቡ ግን ኢሳት አውሮፓና አሜሪካ በሚያስንቅ መልኩ ሐተታ እየከተበ መቀመጫ ያሳጣን ነበር። አሁን ደግሞ ተስፋየ ገብረአብ የተባለ ግለሰብ በተራ ወሬና በአሉባልታ ሳይሆን በተጨባጭ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውን የማፈራረስና የማተረማመስ የሻዕቢያ ተልዕኮ ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደነበር በዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻና አለማየሁ መለሰ የተባሉት ሁለት ኢትዮጵያውያን ትብብር ሲጋለጥ ኢሳት ደግሞ ሰበር ዜና በማለት አቦይ ስብሃት በዋሽንግተን ዲሲ ስታር ባክስ ታዩ ሲል አክሎም አንድ የአገሩን ክብር ለቁራሽ ዳቦ ሽጦ የአሜሪካ ዜግነት የያዘ ጥሬ ግለሰብ ባለቤት እንደሌለው ውሻ አቦይ ስብሃትን እየተከተለ ሲጮህባቸው አሳይቶ ይፎግረናል።

ጎበዝ! በዚህ ምድር ሰው ሰው የሚያሰኘው አንድ ነገር ቁምነገር ቢኖር የንቃተ ህሊናው ልክና መጠን ነው። ካልነቃህና ካልባነንክ የነቃና የባነነ ወደፈለገው አቅጣጫ ይመራህና ይጨፍርብህ ዘንድ ግድ ነው። ስለሆነም፥

  • እንደ አንድ ባለ አእምሮ ሰው በራሳችን መቆም ተስኖን ዕድሜ ልካችን ዎፌ ቆመች የምንል ከሆነ፤ 
  • አጥንት መጉረስ በሚገባን ሰዓት አሁንም ወተት መጋት የሚያምረን ከሆነ፤
  • ከየት ተነስተን ወዴት እንደምናቀናና መድረሻችንም በውል የማናውቅ ከሆነ፤
  • በህይወታችን ግልጽና የማያሻማ ዓላማና ግብ ከሌለን የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ በዙሪያችን የሚያንጃብብ ጆቢራ ስፍር ቁጥር የለውም። ከእነዚህ መካከልም  የበግ ለምድ የለበሰ የናቅፋ ተኩላ ኢሳት አንዱ ነው።

አበው “በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ ገደሉን ሳታይ!” ሲሉ እንዳመሳጠሩት ኢሳት፥ የኢትዮጵያ ባንዴራ እያወበለበ አስመራ ከተማ እየተፈበረከ በሚላከው ጸረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ፕሮፖጋንዳ እየነፋ ባንዴራ አልባ አገር አድርጎ የምጥ ህይወት ትኖር ዘንድ እንደሚያደርግህ ደግሞ አትጠራጠር።

እናማ የሀገሬ ሰው ሆይ!

  • የበልዓም አንደበት ኢሳትን መዋጋት ኢትዮጵያዊነት ነው። 
  • የመንገድ ዳር መደዴ ኢሳትን ማጋለጥ ህዝባዊነት ነው። 
  • አጋድሞ እያረደን ያለ ኢሳትን መቃወም ዜግነታዊ ግዴታህን መወጣት ነው።
  • እርስ በርስ በጎሪጥ እንድንተያይ እያደረገ ያለ ኢሳት በቃ! ማለት ጀግንነት ነው።
  • ኢሳትን መደጎምና ከኢሳት ጎን መቆም ደግሞ ጸረ ሀገር፣ ጸረ ኢትዮጵያዊነትም ነውና በገዛ እጅህ አገርህን ሳትበታትንና ሕዝብህን ደም ሳታቃባ ከእንቅልፍህ ንቃ!!

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 14, 2013

Advertisements