“ማኅበረ ቅዱሳን” የሚያራግባቸው ቁንጽል መፈክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘኑ፥ 

በእኛ በክርስቲያኖች ማለትም በክርስቶስ ኢየሱስ ደም ከዘላለም ሞት መዳናችን የምናምን የእግዚአብሔር ልጆች በኩል ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ አንድና አንድ ነው ይኸውም፥ መፈክሩ እውን ክርስቲያናዊ መፈክር ነው ወይ? ነገሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘንስ ሚዛን ይደፋል ወይ? «አንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት!» ብሎ የአዲስ ኪዳን እምነት ሆነ የክርስቶስ ኢየሱስ ትምህርት አለ ወይ? ነው። መልሱ አጭር ነው።

አንደኛ፡ በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ “በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” እንዲል ክርስትና በነቢያትና በሐዋርያት መሰረት ላይ የታነጸ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስለ ሰዎች በደል፣ ኃጢአትና መተላለፍ ተላልፎ የተሰጠ ብቸኛ አዳኝና ጌታ መሆኑን በማመን የሚገኝ የዘላለም ህይወት እንጅ ኢየሱስ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ሆኖ መፈክር እያሰማህ የምትከተለው አምላክ፤ ክርስትናም የፖለቲካ ድርጅት ፓርቲ አይደልም።

ሁለተኛ፡ በዮሐንስ ወንጌል 13: 35 “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ተብሎ እንደተጻፈ ቀለል ባለ አማርኛ መፈክሩም ክርስቲያናዊ አይደለም አጋፋሪዎቹም ክርስቲያን/የክርስቶስ ተከታዮች ሊሆኑ አይችሉም። አንድ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ የታጠበ፣ የተቀደሰና የጸደቀ ክርስቲያን በዕለት ዕለት ህይወቱ ተለይቶ የሚታወቀው በጸብ ጫሪነቱ፣ በተናዳፊነቱ፣ አልያም በነገር ሳይሆን የአንድ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ መለያው ፍቅር ነው። እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ በመንገዱ ሁሉ የሚያስበውና የሚያሰላስለው ፍቅር ነው። ቋንቋው ስራውም ሁሉ ፍቅርና የፍቅር ውጤቶች ናቸው። ፍቅር ካራሱ ጋራ፣ ፍቅር ከወገኖቹ ጋራ፣ ፍቅር ከጎረቤቱ፣ ፍቅር ከሚያምንም ከማያምንም ጋራ። ታድያ ይህ የክርስትናና የክርትያኖች መታወቂያ (ፍቅር ማለቴ ነው) ራሱ “የቅዱሳን ማህበር” በማለት የሚጠራ ግብረ እኩይ ማህበር በቅርብም በሩቅም በዞረበት: በዋለበት: ባለፈበትና ጥላው ባጠላበት ስፍራ ሁሉ እነዚህ ነገሮች የውሃ ሽታ ናቸው።

በነገራችን ላይ «አንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት» የሚለውን አባባል “ሕገ መንግስት” ብቻ ሳይሆን ጸረ ክርስትና/የክርስትናን መልክ ለማጥፋትና ክርስትናን የጥላሸት ለመቀባት በአዲስ ኪዳን ላይ የተቃጣ የጸረ- ክርስቶስ ሃሳዌ መሲህ አጀንዳ ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ዓቢይ ነጥብ ቢኖር እግዚአብሔር በግርግር፣ በአመጽ፣ በአድመኝነት፣ የማይከብር መሆኑና አመጸኝነት ለባህሪው የማይስማማው፤ ምግባረ እኩይ ልጅ የሌለው፤ ጻዲቅ አምላክ መሆኑ በግልጽ ሊታወቅና ሊሰመርበት ይገባል።

ጌታችን ኢየሱስ በማቴ 28: 19 ለደቀመዛሙርቱ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው” እንዲል ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱ ወደ ዓለም ስያሰማራ “እያስተማራችኋቸው” አለ እንጂ “ያልተጻፈ ቃል በቲሸርታችሁ ጽፋችሁ በታላቅ ጩኸትና ጭፈራ ዱላና ቆመጥም ይዛችሁ ተከታዮች አፍሩልኝ!”  አላለም እንዲህ ያለ እንቅስቃሴም ከክርስቲያናዊ ስነ ምግባር የወጣ ተግባር ብቻ ሳይሆን ሰይጣናዊም ነው።

በፖለቲካ አነጋገር ኢትዮጵያ የሁሉም “ኢትዮጵያዊ ነኝ!” ብሎ የሚያምን ዜጋ ናት! ሰው በክርስቶስ ኢየሱስ ብቸኛ ጌትነትና አዳኝነት ቢያምንም ባያምንም፣ ቢቀበልም ባይቀበልም ኢትዮጵያ ለዚህ ግለሰብም ሆነ ማህበረሰብ ምድሩ፣ ኩራቱ፣ ሀገሩም ናት። በኢየሱስ ማመን ለራስ ጥቅም እንጅ ለአግዚአብሔር ተብሎ የሚደረግ ነገር አይደለም። ክርስትና፡ አላምንም ያለ አንገቱን በሜንጫ ምታው/በስይፍ ቅላው የሚል ትምህርት የለውም። እንደው ግን በአባባሉ [«አንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት» ማለት ነው] ያልተስማማ፣ በነጻ ፈቃ የሚያምን፣ የሌላ እምነት ተከታይ ዜጋ የት ይሂድ ነው መልእክቱ? በምድሪትዋ የተወለደ ሁሉ ምድሪቱ እኩል ትደርሰዋለች። “አንድ ሀገር አንድ ሃይማኖት” የሚለው ማኅበረ ቅዱሳናዊ  መፈክር “ድምጻችን ያሰማ!” ከሚለው ኢስላማዊ (ጅሃዳዊ) ጩኸት ጋር ያስተያየነው እንደሆነ ሁለቱም የአንዲት ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።

ወይ ጉድ! ክርስቲያን ለሰዎች የምስራች ቃል የሚናገርበት፣ ወንጌልን የሚመሰክርበት፣ የእውነትን ቃል በፍቅር የሚያካፍልበት መንገድ ለመፍጠር ይጠበባል እንጂ ያልደረሰበት/ያልነካውን ሰው በቡጢ ለማለት ለጸብ፣ ለነገር፣ ለደምና ለሞት አይተናኮስም አይነካካም። ለመሆኑ እንዲህ ያለ በክርስትና ስም ነገር ፍለጋ መሰማራት ከየት የተገኘ መገለጥ ነው?

አንዱ የሚያምነውን እምነት ሌላው ስላልተከተለ በአገሩ እንደ ባዕድ አቀርቅሮ የሚሄድበት ምንም ምክንያት የለውም። ይህን ሐቅ የማይቀበል ማንም ቢኖር ደግሞ ምድሪቱ እናት አገሩ መሆንዋ ትቀርና እስር ቤት ብትሆንበት ምን ይደንቃል? ይህ ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እምነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሀገራዊ ጥቅም ማእከል ያደረገ አጀንዳ ያላቸው ለህዝብ የቆምና ለሕዝብ የሚቆረቆሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እምነት ሊሆን ይገባል።

በመቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት ይህንኑ ነበር “እንደዚህ ዓይነት ነገር የሚናገሩና የሚያደርጉ ሰዎች ከግንዛቤ ችግር የተነሳ ሊሆን ስለሚችል በትምህርት ሊመለሱ እንደሚችሉ” ይላሉ:: “አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማ” ነው የሚባለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገራቸው በፖለቲካ ቋንቋ ማስረዳታቸው ካልሆነ በስተቀር የ”ማህበረ ቅዱሳንና” ዓላማና ግብ (አጀንዳ) አንድና አንድ ነው። ይኸውም የሀገሪቱ ስልጣን በመላ ቤተ ክህነቱም ቤተ መንግሥቱም መቆጣጠር ነው። እንስቃሴው በተመለከተ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ነው የሚለው በበኩሌ እምነት ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና ሊሆንም የማይችል ነው።

እዚህ ላይ ማህበሩ በቤተ-ክርስቲያን ጥላ ሥር ስለ ተጠለለ ብቻ ከቤተ-መንግስት አካባቢ መሰጠት የሚገባውን ስም አላገኘም። ቁምነገሩ “ማህበረ ቅዱሳን” ብዙዎች እንደሚያውቁት ነጭ ነጠላ ለብሶ ሲያሸበሽብ መላእክት የሚያስቀና መሆኑ ሳይሆን “ማህበረ ቅዱሳን” ማለት  በሽብር ድርጊት ላይ የተሰማራ ሀገርንና ትውልድን የማተረማመስ አጀንዳ ያለው ስራ ፈቶ የተደራጀ የአቡጊዳ ሽፍታ ስብስብ መሆኑ በሀገሪትዋ ጠቅላይ ሚኒስትር በማያዳግም ቋንቋ በይፋ መገለጹ ያስማማናል።  የማህበሩ ቋንቋ እንደ ገደል ማሚቱ የሚያስተጋባ ክፍል ብዙሐኑ የማህበሩ አባላት አንደሆነ ግን እውነትም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ በእጅጉ የሚያጥረው ዜጋ ለመሆኑ አያጠያይቅም።

ይህ ሁሉ ካስረዱ በኋም በሃይማኖት ሽፋን ሌላ ተልእኮ ስለሚያራምዱ እንደ “ማህበረ ቅዱሳን” ያሉ ለሀገርም ለወገን የማይበጁ ኪሳራዎች ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ መንግስታዊ አቋማቸውን ሲገልጹ የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ ለዕብራውያን ሰዎች ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ (ዕብ. 12: 15) ገልጾ መቆረጥ እንደሚገባ ሲል በጻፈው መንፈስ ጠቅላይ ሚኒስትሩም “የሃይማኖት አክራሪነት በአጭሩ መቀጨት ይኖርበታል” በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

በመጨረሻ ኃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ምን ማለት እንደሆነና አስከፊ ገጽታውን በማሳየት ለምን መወገድ እንዳለበትም ጥቂት ነጥቦችን በመዘርዘር ልለያችሁ::

  • ጽንፈኞች ክፉኛ በጅምላዊ አስተሳሰብ የተለከፉ ከመሆናቸው የተነሳ እንደ አማኝ እግዚአብሔር ምን ያላል? መጽሐፉስ? ማለት ቀርቶ ከእግዚአብሔርም ከቃሉም በላይ የሚከበሩና የሚፈሩ የድርጅቱ መሪዎች ስለሚሆኑ እገሌ ምን አለ? እየተባለ የጨለማ ቁራጭ የሲዖል አጋፋሪ ያለውን የአመጻ ቋንቋ እያስተጋባ ለጥፋት የሚሰለፍ ትውልድ ስለሚያፈራ::
  • ጽንፈኞች ነፍሰ ገዳዮች ናቸው፥ “የአብርሃም ዘር መሆናችሁንስ አውቃለሁ ነገር ግን ቃሌ በእናንተ አይኖርምና ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ” እንዲል የዮሐንስ ወንጌል 8: 37, (ማቴ 23: 31)
  • ጽንፈኞች ሐሰተኞ: ውሸተኞችም ናቸው፥ (2ኛ ቆሮ. 11: 13)
  • ጽንፈኞች ተመጻዳቂዎች: ግብዞችም ናቸው፥
  • ጽንፈኞች ከእውቀት ማነስ የተነሳ የሚፈጡሩ እውቀት አልባ ቀናኢያን ናቸው፥ (ማቴ. 22: 29)
  • ጽንፈኞች ማንም ይሁን ምን የሚገባንን ያክል ከሚገባው ማህበረሰብ ጋር እንደ ሰው ሊኖር ስለሚገባ ሰብአዊ ግኑኝነት የሚያሻክሩ: ጸረ ሰብዓዊ መብት አቋም የሚያራምዱ: ለሕዝብ ሰላም ለሀገር ደህንነት ጠንቅ ናቸው፥
  • ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ጸረ- ዲሞክራሲዊ አስተሳሰብ የወለደው በየትኛውም መድረክ ተቀባይነት የሌለው ከይሳዊ አካሄድ ከመሆኑ በላይ የሰው ልጅ ነጻ ፈቃድ የሚገፋም ነው፥
  • በአጠቃላይ “ማህበረ ቅዱሳን” ማለት ሌላ ማንም ሳይሆን ዘርዘር ባለመልኩ የተመለከትናቸውን መጠነኛ የጽንፈኞች መገለጫዎች የሚታዩበትና የሚንጸባረቁበት ሁነኛ አገር አጥፊ ማህበር ከመሆኑ በተጨማሪ በግርግር የሚያምን ድብቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያለው መንፈሳዊ ካባ የተላበሰም ነው::

ስለሆነም በእኔ ላይ ብትፈርዱ ትበተናላችሁ: መንግስታችሁ አይጸናም  እያለ በባዶ ሲያስፈራራና ሲያናፋ የነበረውን ለበርካታ ዓመታት ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ አኳኃን “ክንፍ አለው ይበራል አይሞትም ያርጋል” እየተባለ ሳይገባው ሲፈራና ሲከበር ብዙዎችን ለከፋ ችግር የዳረገ፣ የብዙዎችን ትዳር አናግቶ ቤተ-ሰብን ያፈራረሰ፣ ባለ አውልያና ባለ ክራማቱ “አባባ” ታምራት ያገኘች እጅ ታገኘው ዘንድ የዘወትር ጸሎቴ ነው:: 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Email: yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 13, 2012

Advertisements