ይድረስ ለአቶ ተመስገን ደሳለኝ፡ ፋክት ወይስ ፕሮፖጋንዳ?

በቅድምያ “ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?” [ፋክት መጽሔት፤ ቁጥር 14 መስከረም 2006 ዓ.ም] ሲሉ ባልዋሉበት አልያም በሽፍጥነት የሐሰት ምስክርነታቸውን ለሰጡ/ለጻፉ ግለሰብ ራሴን ላስተዋውቅ። ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል እባላለሁ። ከልጅነት እስከ እውቀት ያደግኩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነው። ራሱን “ማኅበረ ቅዱሳን” እያለ የሚጠራ መንፈሳዊ መልክ ያለው መሰሪ – ጸረ ሀገር፣ ጸረ ትውልድና ጸረ ቤተ ክርስቲያን ቡድን ተገንዞ ከተቀበረበት መቃብር ቀስቅሰው ሊነግሩን እንደቃጣዎት ዓይነት ሳይሆን “ማህበረ ቅዱሳን” ማለት ሰይጣን ራሱ በቁሙ የሚመለክበት፣ የሚዘከርበትና የሚታሰብበት የሲዖል ተረፈ ምርት ለመሆኑ በህወይቴ የማውቀው ሰው ነኝ።

ሕገ መንግሥታዊ የመማር መብቴ ተጥሶ ለዓመታት ከለፋሁበት የትምህርት ገበታዬ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ያለ ስሜ ስም ተለጥፎብኝ እንድባረር የተደረግኩ፣ ከአንድም ሁለቴ በአንድ የክስ መዝገብ ለከፍተኛ እንግልትና ለእስር የተዳረግኩ፣ በሞትና በህይወት መካከል የተገረፍኩና በመጨረሻም አገሬን ለቅቄ በስደት ምድር በኬንያ ለሁለት ዓመት ከአምስት ወር ያለ ምንም የህይወት ዋስትንና እርዳታ የተንገላታሁ የሰው ሚስት ሳማግጥ ተገኝቼ ይመስሎታል? ከነተረቱ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” ነው የሚባለው።

ለመሆኑ እርስዎ ስለ “ማኅበረ ቅዱሳን” ያልሆነውን ነው! በማለት ይህ ያህል ለማለት የደፈሩ እንደ አንድ የማኅበሩ አባል በጋዜጠኝነት ስም የአባልነት ግዴታዎ መወጣትዎ ነው ወይስ ነኝ እንደሚሉት “በጋዜጠኝነትዎ” ነው? ቁምነገሩ ያለው ወዲህ ነው። “ቀጣዩ የኢሕአዴግ ዒላማ ማኅበረ ቅዱሳን ይኾን?” ሲሉ በጻፉት ጽሑፍ በጋዜጠኝነትዎ እንዳልነቅፎት፥

በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርተው ያለ ተጠያቂነት ለመኖር ይሻሉ?  

እንግዲያውስ በጋዜጠኝነት የሥራ መስክ ይሰማሩ።

ተብሎ በሚነገርባትና ጋዜጠኝነት በረከሰባት አገር ነዋሪ ሆኑብኝ፤ ከዚህም የተነሳ ይሁንም አይሁንም “ጋዜጠኛ ነኝ” ብሎ ራሱን የሚያስተዋውቅ ግለሰብ መንካትና ቀና ብሎ ማየት ስም በሚያሰጥበት ሰዓት ስራዎትን መተቸት፣ ስህተትዎን መጠቆም፣ እውነቱን ማስተማር፣ ማንነትዎን ማሳየትና ልክ ልክዎን መንገር ጠላት ማፍረት ብቻ ነው የሚሆነው። “ሰማይ አይታረስ ጋዜጠኛ አይከሰስ!” እንዲል። ይህን ጠንቅቀው ስለሚያውቁም ነው የፈለግኩትን ብሆን፣ እንደው ወተቱን አጥቁሬ ማሩንም አምርሬ በጽፍና ብሸቃቅጥ ማን አባቱ ይጠይቀኛል! ይህን ጻፍክ ብሎ በሕግ ሊጠይቀኝ የሚቃጠው አካል ካለ ደግሞ CPJ, AI, HRW … አሉልኝ! እንደው የናፈቀኝና የምመኘው  “አዋርዱን” ላገኝ የምችለው ህዝብና ሀገርን የሚጠቅም ስራ ሰርቼ ሳይሆን በሕግ ፊት የሚያስጠይቀኝ፣ ግልጽነት የጎደለበት፣ ወደ ውህኒ የሚያስወረውረኝ ሥራ (ወንጀል) የሰራሁ እንደሆነ ነው። ሲሉ በሚገባ አስበውበት በስምዎ ድረ ገጽ ተከፍቶሎት ትልቁም ትንሹም ስለ እርስዎ ሲያወራ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ትላልቅ ከተሞችም በስምዎ ስብሰባዎች እየተጠሩ የሻማ መብራት ፕሮግራም ተዘጋጅቶሎት ሲወደሱና ሲቀደሱ እየታዮት እንደጻፉት ስነግሮት በአክብሮት ነው። 

በተራ አባልነትዎ (እንደ ምእመን) የጻፉት ጽሑፍ እንደሆነ ግን (ነው ብዬም ስለማምን) በእውነቱ ነገር መጽሐፍ “ኤልሳዕም አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን፥ እባክህ ግለጥ ብሎ ጸለየ እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠ፥ አየም” እንዲል እግዚአብሔር ዓይኖትን ይከፍት ዘንድ ከመጸለይ ያለፈ ከእርስዎ ጋር እንካ ሰላንቲያ የምገጥምበት ምክንያት ሰዓቱም የለኝም።

እኔምለው ከዚህ በላይ መሄድ አይቻልም ወይ?

  • የኢትዮጵያ ፖለቲካ በቦሌም በባሌም ኢህአዴግ መቃወም ብቻ ነው?
  • እንዴት ነው ኢህአዴግን መቃወም ማለት ጸረ ሀገር ጸረ ትውልድ የሆኑ ድርጊቶችና አጀንዳዎች መደገፍ፣ ማራገብ አስፈጻሚ መሆን የሆነው?
  • መቼ ነው ህዝብ ነጻ የሚያወጣው፣ የሚያሳርፈውና የሚበጀውን እውነት “ተናግረን” ሕዝብ ራሱን ችሎ በሐሰት ጫንቃ ላይ ይቆም ዘንድ ዜግነታዊ “ግዴታችንን” የምንወጣው?
  • መቼ ነው ይህን ህዝብ በቅንነት “የምናገለግለው?”
  • መቼ ነው ሀገራዊ አጀንዳ “ኖሮን” ለሆድ ሳይሆን ለትውልድ “ራሳችንን አሳልፈን የምንሰጠው?”
  • መቼ ነው ራዕይ “ኑሮን ነገን እያየን” ውጤታማ ሥራ ለመስራት “ከራሳችንን ጋር የምንታረቀው?”

+ ይሄ ነው ጋዜጠኝነት፡ በሐሰት ምስክርነት ሕዝብን ማደናገር?
+ ይሄ ነው ጋዜጠኝነት፡ በስራዎችህ ሕዝብን መናቅ?
+ ይሄ ነው ጋዜጠኝነት፡ በሕዝቦች መካከል ሰላም ለማንገስ በመስራት ፈንታ ሁከትንና ብጥብጥን ለመፍጠር እንቅልፍ ማጣት?
+ ይሄ ነው ጋዜጠኝነት፡ ባልዋልክበት ባላለፈብህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ብዙና ጥቂት ማለት፣ ራስህን ማስገምገምና ማዋረድ?
+ ይሄ ነው ጋዜጠኝነት፡ በሞያው ለሚሰራው ስራ ተጠያቂነትም ሆነ ኃላፊነት አይሰማውም?

+ ጽድቁ ይቅርና እውነት ለኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ (ሁሉንም አላልኩም) አላርጅክ የሆነበት ምክንያት ምንድ ነው? እውነት ላለመናገር ምላችኋል ልበል?

ወዳጄ ተመስገን! ለወደፊቱ እንደ አንድ ለሚሰራቸው ስራዎች ህዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለው አውቆ ለስራው ክብር የሚሰጥና የሚተጋ ብቁ ዜጋ መጻፍ ይለምድቦት ዘንድ “ማኅበረ ቅዱሳን” ወይስ ማኅበረ ሰይጣን? የሚለውን ክፍል አንድ መጽሐፌ ያነቡ ዘንድ በነጻ ጋብዤታለሁ። Assocaition of Saints or Association of the Davil?

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E- mail- yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 7,  2013

Advertisements