የሐዘን መግለጫ

በማስቀደም በኢጣልያ ላምፔዱዛ (ደሴት) በሰጠመችው ጀልባ ልጆቻችሁን ላጣችሁ ኤርትራውያን ወላጆች እንዲሁም ሌሎች የዓለማችን ዜጎች ቤተሰቦች በመላ መጽናናትን እየተመኘሁ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን መግለጽ እወዳለሁ። ወዳጆቼ ሆይ! የሰው ህይወት በእግዚአብሔር እጅ ናት። አንድን ሰው የፈለግነውን ያክል ብንወደውም የሰው ህይወት ግን ልንቆጠጠራት አንችልም። ሩቅ አገር ተጉዘው የማንቀላፋታቸው ነገርም የእናንተ ስህተት አይደለም። ይህችም ቀን በእግዚአብሔር ዘንድ የተሰወረች ሳትሆን የታወቀች ነችና ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በሁለተኛ መልዕክቱ “የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል፥ ስለዚህም እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር በምንጽናናበት መጽናናት በመከራ ሁሉ ያሉትን ማጽናናት እንችላለን።” እንዲል የሌለውን እንዳለው የሚጠራ፣ ሐዘንን እንዳለፈ ወንዝ የሚያስረሳ፣ በረከቱም ፍጹም ከሆነ ከልኡል እግዚአብሔር ዘንድ መጽናናትን ይሆንላችሁ ዘንድ ጸሎቴ ነው። eri_refugee_death-500x273

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አጠር ያለች መልዕክት ለአንባቢያን ለማስተላለፍ እወዳለሁ፥

ሃዘን፣ ደስታ፣ ዋይታ፣ እልልታ፣ ፌሽታ፣ መከራ፣ … ጭንቀትና ሃሴት የሰው ልጅ የህይወት ገጽታዎች ናቸው።  የሰው ልጅ በምድር እስካለ ድረስም ዓይነቱና መጠኑ ይለያይ እንደሆነ ነው እንጅ በምርጫው ሳይሆን መሆን ስላለበት ብቻ ከሰይፍ ይልቅ በሚያቆሳስሉ የህይወት ውጣ ውረዶች ማለፉ፣ ማየቱና ገፈት ቀማሽ መሆኑ የማይቀር ነው። በየ ዓይነቱ ምግብ መብላት ብቻ ሳይሆን በየ ዓይነቱ መከራ ማየትና ማስተናገድም ዕጣ ፈንታችን ነው።

የሰው ልጅ፡ ሥልጣንም ሆነ ሀብት የማያስቆመውና የማይደልለው፣ አድልዎ የማይውቅ፣ ሁሉን በእኩልነት የሚዳኝ፣ ልጆች ከወላጆች እቅፍ፡ ወላጆች ከልጆቻቸው ፍቅር ነጥሎ ለመውሰድ ወደኋላ የማይልና የማይራራ፣ ቀጠሮ የማያውቅ፣ አቅጣጫ የማይጠቁም፣ ምርጫ የማይሰጥና ቢዘገይም የማይቀር የሞት ባለ ዕዳም ነው። የሞት ወዳጅ የሞት ጠላት የለውም። ሞት አድራሻ ተለዋጭ ስምም የለውም። ሞት ስሙም “ሥራውም” ሞት ነው። እንግዲህ የሰው ህይወት በዚህ ምድር የዚህ ሁሉ “እንቆቅልሽ” ድምር ውጤት ነው።

ወዳጆቼ ሆይ! ሞት/ሐዘን መራር ነው!! አፍጋናዊ ይሁን ኤርትራዊ በሰው ሐዘንና መከራ ብሎም ሞት ደስ የሚለው ቢኖር የሰው ደስታ ማየት የማይሆንለትና አዙሮ የሚጥለው ሰይጣን እንጂ ሰው ሊኖር አይችልም። ለሰው ማዘን ሰው ደስ ሲለው የደስታው ተካፋይ መሆንና ሲያዝን ደግሞ ከጎኑ በመቆም መጽናናትን መመኘት ሰብአዊ/ባህሪያዊ ነው። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስታችንን ከሚያዝኑ ጋርም እኩል ሐዘናችንን መግለጽ ሞቅ ሲለን የምናደርገው ሲበርደን ደግሞ ፊታችን አዙረን የምንቀመጥበት የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ሰው በፖለቲካ፣ በኃይማኖት፣ በነገድ እንዲሁም በሌሎች ውጫዊ የልዩነት መገለጫዎች የማይለካና የማይመዘን ልዩና ክቡር ፍጥረት ነው። የነፍስ ዜግነት የላትምና!!

ወዳጆቼ ሆይ! ህይወትን የቀመሰ በህይወት አይቀልድም። የፈሰሰ ውሃ እንደማይታፈስ ሁሉ ህይወት እንዲሁ ናት። ህይወትን ማወቅ ማለት ደግሞ ስለ ህይወት የሚያወሩ ጥቅሶች እየለቃቀምን ግድግዳ ላይ መለጠፍ ማለት አይደለም። የህይወት ትርጉም ከየትም ይምጣ ከየት አንድን ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ሰውን እንደ ራስህ መቀበል፣ መውደድ ነው።

ወገኖቼ ሆይ! ፖለቲካዊ አስተሳሰባችን ሆነ ኃይማኖታዊ አመለካከታችን አንድን ሰው በሰውነቱ እንዳንቀበለው አስተዋጽዖ ካላቸው በእርግጥም ታመናል ማለት ነው። በሰዎች ደስታና ሐዘን ተካፋዮች ለመሆን፣ ከበሮ ይዘው በደስታ ከሚዘሉ ደስ እያለን ለመዝለል፣ ድምጻቸው ከፍ አድርገው ከሚያለቅሱ፣ ከሚጮኹና ዋይ ከሚሉም ዋይ ለማለት፣ በአጠቃላይ በነገር ሁሉ ለሰው የሚራራ ዘንበል የሚል ልብ እንዲኖረን የግድ የአንዲት አገር ልጆች፤ አንድ ዓይነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ኃይማኖታዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል ማለት አይደለም። 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E- mail- yetdgnayalehe@gmail.com
Oct 5, 2013

Advertisements