እግዚአብሔር የለም!

አንድ ሃኬተኛ ሰው ነው አሉ ከዕለታት አንድ ቀን ዓይኑ ያረፈበት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል/ክፍል እያገለባበጠና እያነበበ ሲሄድ መጀመሪያ “ታንቆ ሞተ” (የማቴዎስ ወንጌል 27፥5) የሚለውን ቃል ያገኛል። ሰውየው ያነበበው ቃል ስላልተመቸውና እጅግም ስለ ከነከነው ይህን ይተወና ሌላ ቃል ፍለጋ መጽሐፉን ሲያገለባብጥ አሁንም በድንገት ዓይኖቹ “ይቀናሃል ውጣ እንዲህም አድርግ” (መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 18፥21) የሚል ቦታ ያርፋሉ። ሰውየው ውሎውን ለማሳመር ቃሉ ሳይመቸው በመቅረቱ አሁንም የያዘውን መጽሐፍ ማገለባበጥ እንደ ተያያዘው ነው። ለሦስተኛ ጊዜ ዓይኑን እንደጨፈነ ሌላ አንድ ክፍል ይመዝና ዓይኑን ከፍቶ ሲያነብም እንዲህ የሚለውን ቃል ያገኛል “ይህን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው” የሚል። ታድያ ሰውየው ምን ብያደርግ ጥሩ ነው? ከመቀመጫው ብድግ ይልና ታንቆ ሞተ ይባላል።

ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ግልጽ ነው ብየ አምናለሁ። አንድ ሌላ ቀለል ያለ ተጨማሪ ምሳሌ ልጨምር። በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 14፥1 እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን “ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል።” ይህን ቃል ሙሉ ይዘቱን በማንበብ ፈንታ ግን ከፊትና ከኋላ ያለውን በማስወገድ “አምላክ የለም!” የምትለዋን ቃል ብቻ መዘን/ገንጥለን ለማበብ የሞከርን እንደሆነ እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ ላለመኖሩ ብዙ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን ስለ እግዚአብሔር የሚናገር መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ነው) ራሱ እግዚአብሔር ላለመኖሩ ሁነኛ ምሥክር ወይም ማስረጃ ሆኖ ሊያገለግል ነው ማለት ነው። አይመስሎትም?

ሌላው ይቅር “እግዚአብሔር የለም!” የሚለውን የጽሑፌ ርዕስ – በእግዚአብሔር ህልውና የሚያምን ወገን ያለውንና የሌለውን አቅሙ አጠራቅሞ “ስንሻው ተገኘ!” እየተባለ ለመሳደብ፣ ለመራገም፣ ብሎም የቡና ማጣጫ ሊያደርገኝ፤  ከነ አካቴው “እግዚአብሔር የለም!” ብሎ የሚያምን ደግሞ ተጨማሪ ማብራሪያና ማጣቀሻ ፍለጋ፤ በመቦጨቅ ከፍተኛ ልምድ ያካበተ የወሬ ሱሰኛ ደግሞ ለወሬ በሚያመቸው መልኩ እየቀመመ ለማውራት፤  ሌሎችም እንዲሁ በተለያዩ ምክንያቶች  ተጣድፎ ዘው ብሎ የሚገባ ቁጥር ሁላችን አንስተውም።

ግን ደግሞ “እግዚአብሔር የለም!” ብየ ስጽፍ ከራሴ ፈጥሬ አይደለም። በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 14፥1 ተጽፎ ካገኘሁት [“ሰነፍ በልቡ አምላክ የለም ይላል።”] በዋናነት ስለ ሰነፍ ሰው ማንነት የሚናገር የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው።  አንባቢ ሆይ! “እግዚአብሔር የለም!” በማለት ሽንጤን ገትሬ ስከራከርና ሙግቴ በማስረጃ እንዳስደግፍ ስጠየቅ ደግሞ መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 14፥1 “አምላክ የለም!” ይላል  በማለት ሙሉውን ክፍል ሳይሆን ለእኔ በሚያመች መልኩ በቁንጽል ጎደሎ ማስረጃ ሳቀርብ አይተውልኛል አይደል?

ይሄውሎት ውድ አንብቢ! የሀገራችን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የፈለግነውን የቀለም ዓይነት እንቀባባው ችግሩ መቶ በመቶ የጎሳ የበላይነት ጥይቄ ችግር ነው። እንዲህ ያለ የተበከለ የአየር ጸባይ ባለበት አከባቢ ደግሞ የሆነውንና ያለሆነውን ዓይነት ማንኛውም ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ … እንቅስቃሴዎች ሁሉ እየተዘረዘሩና እየተመነዘሩ ወደ ጎሳ ፖለቲካ መጠምዘዝና ጩኸህ ማስጮህ ዋነኛው የጨወታው ሕግ ነው። በነገራችን ላይ ይህን ሐቅ የማይቀበል፣ የሚክድ ወይም የማያውቅ አልያም ያልበራለት ነገር ግን በኢትዮጵያ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ለመሳተፍ የሚቃጣው ግለሰብ ካለ/ያለ እንደሆነ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ አውቃለሁ!” ብሎ እንዳይናገር ብቻ ነው የሚመከረው።

 “እንኳዕ ካባኻትኩም ተፈጠርና” መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር

ዛሬ በህይወት የሌሉ መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር “ዘረኛ ናቸው!” ብሎ ለመክሰስ እንደ ማስረጃ የምትመዘዘው መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሃያ ዓመታት በፊት (በሰማኒያዎቹ መጀመሪያ አከባቢ መሆኑ ነው) ገበሬ በእርሻው መካከል የገባውን አረም ከስሩ ነቅሎ ለጸሐይ እንደሚሰጥ ሁሉ ለአሥራ ሰባት ዓመታት የብሔር ብሔረሰቦች መብት ረግጦና አፍኖ አገር በጠመንጃ ሲገዛ የኖረ ወታደራዊ የደርግ መንግሥት ዘመነ ንግሥናው ባበቃለት ማግስት በመቀሌ ከተማ ተገኝተው ለአስራ ሰባት ዓመት ሰለቸኝ ደከመኝ ሳይል ላሳየው ጽናት ለትግሉ ባደረገው ከፍተኛ አስተዋጽዖና አበርክቶ አይደለም የቃላት ምሥጋና ሌላም ቢደረግለት የማይበዛበትና የሚገባው ሕዝብ [አንድ ጊዜ ፈጽሞ ጤና ያጣ ሰው ይህም ዘረኝነት ነው ማለትቱ አይተውም። ይገባኛል!] እጅ ለመንሳትና ለማመስገን ለከተማዋ ነዋሪዎች በአጠቃላይ ለትግራይ ሕዝብ በትግርኛ ቋንቋ ካደረጉት ረጅም ንግግር ማኸል ተቆርጦ [“እንኳዕ ካባኻትኩም ተፈጠርና”] “በዘረኝነት” ሲስከሰሱ ዛሬ ድረስ እንሰማለን።

“ይልቅ እኔ ጉራጌ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ ትርፋማ ያልሆነ ነገር” ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ

የመዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር አለ አግባብ ተቆርጦ እንዴት ከአውዱ ውጭ እንደ ተተረጎመና ለፖለቲካ ፍጆታ እንደዋለም የንግግሩ ሙሉ ይዘት መስማት የማይፈለግበት ሰዓት ደርሰናል። ባሳለፍነው ሳምንት እ.ኤ.አ መስከርም 22/2013 በአሜሪካ አርሊንግቶን ቨርጂኒያ ሀገር በጦርነት ማቅናትና መገንባት ይቻላል ብሎ የተነሳ ኃይል በጠራው ስብሰባ የማያደርጉትን እንደርገዋለሁ በማለት የተካኑ/ያስመሰከሩ፤ በራሳቸው ቃል የተሰላቹ የድርጅቱ ሊቀ መንበር የሆኑ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እንዲህ ብለው ነበር “እንደዛ ዓይነት ውይይት ውስጥማ አንግባ ትርፍ የሌለው ክርክር ነው። ትርፋማ የሆነ ነገር እናድርግ። እንዴት እንደምናደርግ ይልቅ እኔ ጉራጌ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ ትርፋማ ያልሆነ ነገር …” ጥያቄው ትርፋማ ባልሆነ ነገር ተሰልፎ መልፋት፣ መድከምና መንዘላዘል ደስ የሚለውና የሚያሰኘው ማን ቢኖር ነው? ደግሞም ዶክትሩ “ይልቅ እኔ “ኢትዮጵያዊ” እንደሆንኩ ታውቃላችሁ” አላሉም። ለምን? መልሱ አጭር ነው። ይኸውም፥ እንደ ዶክተር ብርሃኑ እምነትና አስተሳሰብ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ ጉራጌ አርቆ አሳቢ አይደለምና።

ዶክተር ብርሃኑ “እኔ ጉራጌ እንደሆንኩ” ሲሉ ማንነታቸው በጉራጌነት ብቻ ወስነው መናገራቸው በራሱ ሌላ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለውና የሚጭር አነጋገርም ነው። እኚህ ሰው “ጉራጌ ብቻ ነው አስቦ የሚሰራ ዜጋ” ሲሉን ማን ነው ዝም ብሎ እንደመጣለት የሚሄድ ራዕይ የሌለው መረን የሆነ ሕዝብ? ተብሎ ለሚነሳባቸው ጥያቄስ መልሳቸው ምን ይሆን? አማራ?፣ ደቡብ?፣ ሀረሬ?፣ ኦሮሞ?፣ ትግሬ?፣ አፋር?፣ … ወይስ እንደ ተለመደ “እኔም አላውቀም!” ሊሉን ነው። በውኑ እኚህ ተናጋሪ “ጉራጌ ብቻ ነው አስቦ የሚሰራ” የሚል አንድምታ ያለው መልዕክት ስያስተላልፉ ለመሆኑ ማን ነው ትርፉንና ኪስራውን የማያውቅ ጅልና ደንቆሮ? … ጎበዝ! ብዙ ማለት ይቻላል።

በመጨረሻ የመዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር [“እንኳዕ ካባኻትኩም ተፈጠርና”] “ዘረኝነት ነው!” ብለው የሚያምኑ ከሆነ የዶክተር ብርሃኑ ነጋ አነጋገርስ [“ይልቅ እኔ ጉራጌ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ ትርፋማ ያልሆነ ነገር”] እንዴት አገኙት? ድንገት ንጽጽሩ የማይገናኝ ሆኖ ከተሰማዎት ነገሩ በራሱ የማይገናኝ ሆኖ ሳይሆን የሚገናኘውን ማገናኘት፣ ለእውነት መሸነፍና ከእውነት ጋር መቆም የማይሆንለት/የማይዋጥለት እንቢተኛ ወገንተኛ አእምሮዎ ሊሆን እንደሚችልስ አስበውበታል? ቅንነት ይሻለናል!

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E- mail- yetdgnayalehe@gmail.com
Oct 4, 2013

Advertisements