አንዳርጋቸው ጽጌ፡ የቁራ መልዕክተኛ!

የአሜሪካ መንግሥት የስለላ ድርጅት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን ሲያሰለጥን፣ ሲዶግም፣ ሲያስታጥቅ፣ ሲረዳ፣ ሞራላዊም ሆነ ቁሳዊ ድጋፎችን ሲሰጥና ለአርባ ዓመታት ከዚያም በላይ እንደ ዛር ፈረስ ሲጋልብበት ተጋዳላይ ኢሳይይስ ኤርትራና ኤርትራውያን ይጠቅማል፣ የኤርትራ ሕዝብ “ከባዕዳዊ አገዛዝ” ነጻ ያወጣል፣ ኤርትራ እንደ አገር ትቆማለች፣ የኤርትራ ህዝብም “ዓዲቦይ!” (በእኛ “እናት አገር” እንደማለት ነው) ብሎ አፉን መልቶ የሚናገርላትና በልቡ ደስ የሚሰኝባት ኤርትራ ያያል! ብሎ አስቦ ሳይሆን የአሜሪካ መንግሥት ጥቅም ያማከለ ነበር። ተጋዳላይ ኢሳይይስማ ለጊዜያዊ ጥቅም ድጋሜ የኤርትራ “ሉዓላዊነትና” የኤርትራ ህዝብ ክብር ያለ ህጋዊ ጨረታ በእከክልኝ ልከክልህ የሸጠ የሻዕቢያ የትጥቅ ትግል መስራችና መሪ እንደሆነ ድፍን ዓለም የሚያውቀው ሐቅ ነው። 

ያም ሆነ ይህ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ደግሞ በተራቸው ወግ ማረግ ደረሳቸውና የሰው አገር ሀብትና ንብረት ለማግበስበስ፣ ያልዘሩትን ለማጨድና ዘፍነው ሲያቅታቸው በአቋራጭ ለመበልጸግ ቋምጠው ይህ የቀን ቅዠታቸው ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አስመራ ከተማ ተቀብለው ሲያስተናግዱና “የአውሮፕላን ትኬት ቆርጠው” “ከአስመራ” አሜሪካ ድረስ ሲያመላልሱ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ትርፋቸውን አስልተው፣ ያዋጣኛል፣ አይሳፍረኝም፣ ለኪሳራም አይዳርገኝም በማለት አስጠጓቸው (ላኳቸው) እንጅ አቶ አንዳርጋቸው ጭራሽ የቁራ መልዕክተኛ ሆነው ለራሳቸው ተዋርደው ህግደፍን የሰፈር መሳቅያ መሳለቅያ ያደርጋሉ፣ ያዋርዳሉ ብለው አልነበረም።

ጥንተ ነገሩ፥

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አሜሪካ ድረስ ልከው በኢሳት የሳይበር ሬድዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው እንዲደሰኩሩ የፈለጉበት/የተፈለገበት ዋና ምክንያት፥

 • የሌላቸውን አለኝ፣ ያልሆኑትን ነኝ በማለት በፈጠራ ወሬ ሀገር ለመናድና የኢትዮጵያ ህዝብ ለማደናገር፥  
 • የተጭበረበሩ መረጃዎች በማቅረብ የኢትዮጵያ ህዝብ ለማሸበር፥ 
 • የአመጽ ቋንቋዎች በመጠቀም የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርስ ለማባላት፥
 • ኢትዮጵያን ለማጠልሸት የኢትዮጵያ መንግሥት በቀደዳ ለማደናገጥ፥ 
 • ህዝብንና መንግስት ለማጋጨት፥  
 • የጥፋት አጀንዳ ለማስተዋወቅ፥  
 • ጥላቻና የሁከት ለመዝራት፥ 
 • ፅንፈኝነት እንዲስብኩ ተላኩ እንጅ ፦
 • ጭራሽ አስመራ ቤተ መንግስት ውስጥ ስለሚጋገረው የማሽላ እንጀራ (ወዲ ዓከር)፣ ስለሚሰራው የምስር ወጥ (ዓደስ) ለማውራት፥ 
 • አቶ አንዳርጋቸው የአሜሪካ ፍርድ ቤት በአለቃቸው (ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ፋይል) የጠራቸው ይመስል ስለ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ንህዘላልነት፣ ግድ የለሽናትና አውደልዳይነት እንዲመሰክሩ፥ 
 • ፕሬዝዳንቱ የቤተሰብ ጉዳይ ውስጥ ገብተው እንዲፈተፍቱ፥ 
 • ስለ አሥመራ ከፍተኛ የፖለቲካ ባለ ሥልጣናት (ሚኒስትሮች) የዘቀጠ የኑሮ ደረጃ እንዲናገሩ፥
 • በአሁን ሰዓት ኤርትራ ስለምትገኛበት ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ማህበራዊ ውድቀት ወይም ኪሳራ ለዓለም በማጉልያ እንዲያሳውቁ፥
 • ፍጥረት ሁለት እጆችዋን ወደ አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ ዘርግታ ፈጣሪ አስከፊ፣ አስደጋጭና አሰቃቂ የኤርትራውያን የዕለት ዕለት ኑሮ አይቶና ተመልክቶ ኤርትራን በምህረት ይጎበኛት ዘንድ በሚማጸንበት ሰዓት የኤርትራውያን ነባራዊ ሁኔታ ለመሸምጠጥ፥ 
 • በነገር ሁሉ ሳይሳካለት ይልቁንስ ልክ እናቱ እንደወለደችው እርቃነ ስጋቸውን ሆነው እንዲሳቅባቸው አልተላኩም። ታድያ አቶ አንዳርጋቸው ለዚህ ካልተላኩ፣ ተልዕኳቸውም በአግባቡ ካልተወጡ ዋጋቸው ምን ይሆን? በማለት ተጨንቀው ይሆናል።

ቅጣትዎን ያቅልሎት!

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ “በባህሪያቸው” ቀልድ አያውቁም። “የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” የምትለዋን ጥቅስም ክቡርነታቸው በደንብ እንደሚያውቋትና ለተግባራዊነትዋም አንድም የሚስተካከላቸው እንደሌለ ሰምቻለሁ።

ወዲ አፎም ሰውን ማሰር፣ ማሰቀየት፣ በሄሊኮፕተርና በ“ኦቶ” (ኦቶ ስምንት ቁጥር መሆኑ ነው በጣልያንኛ) መግረፍ፣ ከነነፍሱ እያለም ጉድጓድ ውስጥ መጨመርና መጣል፣ ኮንተይኔር ውስጥ መቆለፍ፣ የአካል ብልቶች በመቀስና በፒንሳ መቆራረጥ፣ የታደለ ደግሞ በመትረየስ መግደል፣ ስመ ዝክሩ ማጥፋትና ሰውን መሰወር ተሰላችተው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ለምኔ ብለው የተዉትና ንስሃ ገብተው የተቀደሱ እንደሆነም አላውቅም እንጅ በሂደት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር ኃይለ ወልደትንሳኤ (ድሩዕ) የዋጠች ጉድጓድ ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌም መከፈትዋ አይቀርም። ምን ነው? ቢሉ በህግደፍ መንግሥት ወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት “የዳህጸ ልሳን” ቅጣት ከነ ነፍሱ ጉንጓድ ውስጥ መጨመር፣ ድምጹንና ስመ ዝክሩን ከምድረ ገጽ ማጥፋት መሰወርና ማስወገድ ወዘተ ናቸው። አንድም “የሰብዓዊ መብት ተሟጓች” ተብየዎች ምዕራባውያን ድርጅቶች ላያገኙት የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር (ቀይ ባህር) ማስጠም ነው። ወዲ አፎም “እግዚሃር” ባለ ቤታቸው ወ/ሮ ሳባ ሃይሌ አይቶ መጨረሻቸው ያሳምርላቸው እንጅ እሳቸውማ ገባሬ እኩይ ሰይጣን በእሳት ያጠመቃቸው ዕልል ያሉ ጨካኝ ናቸው።

ደግሞስ ማን ያውቃል?

ወዲ አፎም ከራሳቸው ጥላ ሳይቀር የሚጣሉና የሚጋጩ የሲዖል ፈላስፋ እንደ መሆናቸውም መጠን የሚወስኑት ውሳኔ ስለማይታወቅ አቶ አንዳርጋቸውን “እነሆ፥ ለዛሬ ተርፈሃል። ወደ ፊት ግን እንዲህ ዓይነት ስህተት እንዳይደገም።” መልዕክት ያዘለ የሞቀ አቀባበል አድርገው ይቀበሏቸው ይሆናል። በግሌ ሰው ክፉ ስለሆነ ክፉ ተመኝለት የሚል የህይወት መርህ የለኝም። ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ያለኝ ግኑኝነት እንደሆነም የሃሳብ ልዩነት እንጅ  ሌላ ነገር አይደለም። ለማንኛውም “ጥሩ ውኃ የጥቅምት ነበርሽ ማን በጠጣሽ፡ ጥሩ ምክር የደሃ ነበርሽ ማን በሰማሽ”  ካልሆነ በስተቀር አቶ አንዳርጋቸው ዕድሉን ተጠቅመው ጨርቄ ማቄ ሳይሉ ከኤርትራ ምድር ካልወጡ ወዲ አፎም እንደሆነ ብልጭ ያለው ዕለት ራሱ ገድሎ ሲያበቃ “በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚመራ ሰራዊት በዛሬው ዕለት በ … ግንባር ከወያኔ ጋር ባደረገው የቶክስ ልውውጥ የአውሮፓ ኑሮአቸውን ትተው ወደ በርሃ የወረዱ፣ ታዋቂ፣ “አዋቂ”፣ “የፖለቲካ መምህርና” “አዋጊ” “አርበኛው” አንዳርጋቸው ጽጌ “በመስዋዕነት” አልፏል!” ብሎ በድምጺ ሐፋሽ ኤርትራ የሬድዮ ጣቢያ ጡሩምባ ነፍቶ ለማስነፋት ችግር የለበትም።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E- mail- yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 3, 2013

Advertisements