አንዳርጋቸው ጽጌ፡ ሻዕቢያን ለመካብ አስልተው ሻዕቢያን ያዋረዱበት ቃል!

በዋናነት በሞት አፋፍ ላይ የሚገኘው የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ መንበረ ሥልጣንና ዙፋን ደህንነት ለመጠበቅ፤ ብሎም ውሎ አድሮ ቀን ሲቆርጥለት ሆ! ብሎ መነሳቱ የማይቀር፤ ባርነት ያስመረረው የኤርትራ ሕዝብ በአቶ ኢሳይያስ መንግሥት ላይ እግሩ ያነሳ ዕለት ምህረትና ርህራሄ በሌለው መልኩ ለመጨፍጨፍና ጸጥ ለማሰኘት በትግራይ ሕዝብ ስም የተቋቋመ በኮሌነል ፍጹምና ኮሌነል ኢሳ የበላይነት የሚመራና ቀጭኝ ትዕዛዝ የሚንቀሳቀስ በአስመራ ከተማና አከባቢዎችዋ የሰፈረው “ዲሞክራሲያዊ ምንቅስቓስ ህዝቢ ትግራይ” [ዲምህት] “አስተባባሪ” መሆናቸው የሚነገርላቸው በአሁን ሰዓት በኤርትራውያን መካከል ትልቅ መነጋገሪያ የሆኑና ከፍተኛ ጥላቻ ያተረፉ አቶ እንዳርጋቸው ጽጌ በህግደፍ መንግሥት ዘንድ ተወዳጅነት ለማግኘት ሲሉ በኤርትራ መንግሥት ከተሰመረላቸው መስመርና ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጭ በመሄድና በማፈንገጥ ሻዕቢያን ለመካብ አስልተው ሻዕቢያን ያዋረዱበት ቃል እንመለከታለን።

የጽሑፉ ውሱንነት፥ 

 • አንደኛ፡ ይህ ጽሑፍ ከመነሻው ስለ ኤርትራ ለመናገር ወይም የኤርትራ ችግር በተመለከተ መፍትሔ ለመጠቆም የተከተበ  ጦማር አይደለም።
 • ሁለተኛ፡ ጽሑፉ በይዘቱ “ምሁር ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ ፍቺ/ትርጓሜ አይሰጥም።
 • ሦስተኛ፡ የወያኔ ሆነ የሻዕቢያ የትጥቅ ትግል መስራች ግለሰቦች የትምህርት ደርጃ በተመለከተ የቀረበ ትንተና ነገሩ ጠቅለል ባለ መልኩ ለመዳሰስ ተሞከረ እንጅ ዝርዝር ውስጥ አይገባም።
 • አራት፡ ሐተታው ከመላ ጎደል ተናጋሪው ግለሰብ (አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ) ሃሳብ መሰረት ያደረገ መሆኑን ስገልጽም በአክብሮት ነው።

ሐተታ፥

“ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሥልጣን ቢኖረው ወያኔ ቦታ አይኖረንም ብለው ይፈራሉ?” ሲል ለቀረበላቸው “ጥያቄ” አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲህ ሲሉ ይመልሳሉ።

“የትግራይ ከፍተኛ ‘ኤሊት’ ምሁር፣ ልሂቅ ወያኔ ውስጥ የለም። ወያኔ ውስጥ የነበሩ በጣም ጥቂት ግለሰቦች እነ መለስ እነ ስዬ የመሳሰሉ ሰዎች በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው። ከሻዕቢያ ጋራ ራሳቸውን በሚያስተያዩበት ሰዓት ላይ ከፍተኛ የዝቅተኝነት ችግር ነበር የነበራቸው ያለው (1)። ሁሉም ነገር ሻዕቢያ የሚያረገው ነገር ነው ሲኮርጁ የነበረው (2)። ከፍተኛ የበታችነት ስሜት ነበረባቸው። በከፍተኛ ደረጃ ይፈሯቸዋል (3)።” 

በነገራችን ላይ ጥያቄው በጥያቄ መልክ ከመቀረጹ/ከመታሰቡ በፊት የመልዕክቱ አንኳር ወይም ለማስተላለፍ የተፈለገው መልዕክት – ሻዕቢያን እንዴት እናወድሰው?፣ እንዴት እንቀድሰው?፣ እንዴት ከፍ ከፍ እናደርገው?፣ እንዴት እናሞጋግሰው?፣ እንዴት … ? በአንጻሩ ደግሞ ወያኔ እንዴት እናዋርደው?፣ እንዴት የጥላሸት እንቀባው?፣ እንዴት እናቃልለው?፣ እንዴት እናጥላላው?፣ እንዴት እናሳጣው? እንዴት እንቦጭቀው? እንዴት … ? የወለደው ጥያቄ ነው። ይህን አስቀድሞ ማወቁ በራሱ ድራማው በቀላሉ እንዲገባን ይረዳል።

1.  “ምሁር” ማለት ምን ማለት ነው? “ምሁር” ማን ነው? 

[ሀ] ወያኔን በተመለከተ፥

አቶ አንዳርጋቸው ወያኔ የገበሬ ማህበር ስብስብ ነው! ብለው ደምድመውታል። ከቆይታ በኋላም “ወያኔ ውስጥ የነበሩ በጣም ጥቂት ግለሰቦች እነ መለስ እነ ስዬ የመሳሰሉ ሰዎች ናቸው” በማለት እንደገለጹት አቶ አንዳርጋቸው እነዚህ ግለሰቦች (መለስና ስዬ) በምን መመዘኛ በምሳሌነት እንደጠቀስዋቸው ግልጽ አይደለም። በሥም የተጠቀሱ ግለሰቦች ምሁራን ተብለው ከተወሱ ዘንዳ ሌላ ፍልስፍናዊ ሥነ ሙግቶች ትተን “ምሁር” ማለት በተጠቃሾቹ ግለሰቦች ‘የትምህርት ደርጃ’ የሚወሰን/የሚተረጎም  ይሆናል ማለት ነው። ከዚህም በመነሳት “‘ምሁር’ ማለት ምን ማለት ነው? ‘ምሁር’ ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄአችን በቂ ማላሽ እናገኛለን ማለት ነው። ሁላችን እንደምናውቀው/ሲነገር እንደምንሰማው አቶ አንዳርጋቸው “ምሁራን” ብለው የጠቀስዋቸው ግለሰቦች (ከወያኔ ወገን ማለት ነው) ለትምህርት ወደ ከፍተኛ ተቋማት ገብተው ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ አቋርጠው ወደ በርሃ የወጡ ግለሰቦች ናቸው።

[ለ] ሻዕቢያን በተመለከተ፥ 

በአቶ አንዳርጋቸው አንደበት ዘንድ ብልጫ ያላቸው “ምሁራን” ተብለው የተገለጹና የተወደሱ የሻዕብያ (በታጋይ ኢሳይያስ የሚመራ) ማንነት ደግሞ እንመልከት። በእርግጥ ከየል፣ ሃርቫርድና ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀው ከአሜሪካ ወደ ሳህል የወረዱ ሻዕቢያን የመሰረቱ ወይም በምሥረታ ጊዜ የተቀላቀሉ ምሁራን (ኤርትራውያን ታጋዮች) ለመኖራቸው አንብቤም ሰምቼም አላውቅም። የሻዕቢያ መሥራቶች ሆኑ አብዛኖቹ ሥም ያላቸው ቀደምት ታጋዮች (ይከአሎ) የትምህርት ደረጃ የተመለከትን እንደሆነ ታጋይ ኢሳይያስ አፈወርቂ ጨምሮ ልክ እንደ ወያኔ ለትምህርት ወደ ከፍተኛ ተቋማት ገብተው ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ አቋርጠው ወደ በርሃ የወጡ ግለሰቦች ናቸው። ከጥቂት ቆይታ በኋላ (ከሀገር ውስጥ ማለት ነው) ከከፍተኛ ተቋማት ተመርቀው የወጡና ትግሉን የተቀላቀሉ ነበሩ ከተባለም በወያኔ ዘንድም ነበሩ። ለማንኛውም እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ አቶ አንዳርጋቸው በምን ዓይነት መመዘኛ ይህን ሊሉ እንደቻሉ ግን ለእኔ ትንግርት ሆኖኛል።

[ሐ] “ኤርትራውያን” ሲተርቱ እንዲህ ይላሉ፥

 • “ንዝገበረልካ ወይ ግበረሉ ወይ ንገረሉ” ወደ አማርኛችን የመለስነው እንደሆነ “ላደረገልህ፡ ወይ አድርግለት ያለዚያም ንገርለት” እንደማለት ነው፡፡ በእውነቱ ነገር አቶ አንዳርጋቸው በአሁን ሰዓት ማድረግ የሚችሉት ነገር ቢኖር ወዲ አፎም (ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ) አሸክሞ የሚልካቸውን ፕሮፖጋንዳ ያለ ምንም ቅደመ ሁኔታ መንፋትና መቅደድ ብቻ ነውና ባይችሉበትም ተልዕኳቸው “በአግባቡ” እየተወጡ ለመሆናቸው አልጠራጠርም።
 • ሌላው የትግራይ ሕዝብ የወለደው ኃይል ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ መሳደብ፣ ማንኳሰስ፣ መቦጨቅ፣ ማጥላላት፣ መዘርጠጥ፣ ማንቋሸሽና ማብጠልጠል አቶ አንዳርጋቸው በትግራይ ህዝብ ያላቸው ሥር የሰደደ ጥላቻ የሚያሳይ ነው። አይመስሎትም?

2. “ሁሉም ነገር ሻዕቢያ የሚያረገው ነገር ነው ሲኮርጁ የነበረው” 

 • ለፕሬዝዳንት ኢሳይያስም ሆነ ለኤርትራ ሕዝብ ከዚህ በላይ ስድብ የለም! አቶ አንዳርጋቸው ቀደም ሱሉ [3:18 ደቂቃ] ወያኔን በዚህ መልኩ ነበር የገለጹት “የወያኔ ዓይነት ውሸታም፣ አጭበርባሪ፣ ለሌብነትና ለዘረፋ የመጣ ኃይል … ” ሲሉ ነበር የገለጹት። ጥያቄው ወያኔ እነዚህ አስነዋሪና አሳፋሪ ድርጊቶች/ተግባራት ከማን ኮረጃቸው? የሚል ይሆናል። ከግንቦት ሰባት! እንደማይሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔምለው፥ አቶ አንዳርጋቸው የተማሩት ትምህርት (እውነቱ ለመናገር አቶ አንዳርጋቸው በከፍተኛ ተቋም ይለፉ አይለፉ ለጊዜው የማውቀው ነገር የለኝም) እንደው ግን (አሁንም ከተማሩ ማለቴ ነው) የተማሩት ትምህርት በጠላትነት የፈረጅከው ኃይል በማንኳሰስና በማቃለል ብቻ የሚገኝ ድል አለ የሚል ትምህርት ነው እንዴ የተማሩ? ቢሆን ነው እንጅ።
 • እንደው የትምህርት ነገር ከተነሳ አይቀር ግን ኢሳት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስመልክቶ “ከመዋቹ ጠቅላይ ሚንስትር በአዲስ አበበ ዩኒቨርስቲ ጓደኛ የነበሩ” – በነገራችን ላይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስማቸው በአደባባይ በተጠራ ቁጥር “የመዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ጓደኛ የነበሩ” ተብለው መጠራታቸው ቢደላቸው፣ ቢመቻቸው፣ ቢኮሩበትና ሞቅታ ቢፈጥራላቸው ነው እንጅ ቢያሳፍራቸው፣ ቢቀፋቸውና ቢከነክናቸው ኖሮማ “ስሙ ቄስ ይጥራውና በምንም ዓይነት መልኩ ከእኔ ስም ተስተካክሎ መጠራት የለበትም” ሲሉ በተጠየፉት ነበር። “ይተዋውቀቃሉ” ለማለት ተፈልጎ ከሆነ ደግሞ ብዙ የማያሻሙ አገላለጾች አሉ። ዳሩ ግን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስማቸው በተጠራ ቁጥር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር ጓደኛ የነበሩ እየተባለ እንዲነገርላቸው ተብሎም ሲነጋርላቸው የልብ ልብ እንደሚሰማቸው አልጠራጠርም። ለመሆኑ ለምን ያህል ጊዜ ነበር ጓደኝነታቸው?
 • “በአሁን ወቅት የአውሮፓ ኑሮአቸውን ትተው በኤርትራ በርሃ መሳሪያ ያነሱ የመንግሥት ተቃዋሚዎችን የፖለቲካ ሥልጠና በመስጠት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ሰው” መቼም ኢሳት ነገርን አድበስብሶ በማለፍ ተክኖበት የለ። ኢሳት አቶ አንዳርጋቸውን ጽጌ በአውሮፓ በምን ዓይነት የሥራ መስክ ተሰማርተው ኑሮአቸውን ይገፉ እንደ ነበር አልነገረንም። በአውሮፓም ቢሆን ሰው ሁሉ ደልቶትና ተመችቶት እንደማይኖር ደግሞ ሁላችን አንስተውም። አቶ አንዳርጋቸውን ጽጌ በአውሮፓ የከፍተኛ ተቋም መምህር፣ በመንግሥት ሆነ መንግሥታዊ ያልሆነ ወይም ዓለም አቀፍ በሆኑ ድርጅቶች በኃላፊነት የቢሮ ሥራ ይሰሩ የነበሩ ግልሰብ ቢሆኑ ኑሮ ኢሳት ይህንን ከማንበልበል ይመለሳል የሚል እምነት የለኝም። ለጉድ እንደሚያቀልጠውም አልጠራጠርም። ብቻ ግን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲህ ነገር መቀላቀል ያበዙ ከአውሮፓ ወደ አስመራ የሄዱበት ምክንያት ሌሎችን የፖለቲካ ትምህርት ለማስተማር ሳይሆን ከወዲ አፎም (ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ) እግር ሥር ቁጭ ብለው የሥልሳዎች አስተሳሰብና አመለካከት ለመቃረም የተጓዙ እንዳይሆኑ ነው የጠረጠርኩ። ሰው ውሎውን ይመስላል! አይደል የሚባለው።

3. “በከፍተኛ ደረጃ ይፈሯቸዋል” 

 • ሻዕቢያ ትልቅና የሚፈራ ኃይል ቢሆን አይደል እንዴ በሳሕል በርሃ በጉልበቱ በቆፈሮው ጉድጓድ እንደገባ መውጣት አቅቶት ተስፋ በመቁረጥም ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ ሲያምጥ ወያኔ ደርሶ ነፍስ የዘራበት። 
 • ሻዕቢያ አቻና ተወዳዳሪ የሌለው “የእግዚሐር ሰራዊት” ቢሆን አይደለ እንዴ “ከባድሜ ወጣን ማለት ጸሐይ ሞታለች ማለት ነው” እያለ ሲፎክር ከአሥመራ ከተማ በቅርብ ርቀት (ተሰነይ) የተገኘ። 
 • ሻዕቢያ እውነትም ብርቱና ገናና፣ በቀንድ አፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው፣ ኃያል መንግሥት ቢሆን አይደል እንዴ መሬቱን አስረክቦ ሲያበቃ (ሃያ አምስት ኪሎ ሜትር) ጭራውን እየቆላ የአልጀርስ ስምምነት ለመፈረም የሮጠ።
 • ሻዕቢያ የሚፈራ ቢሆን ነዋ በአሁን ሰዓት ወያኔ አንዲት ጥያት ሳይቶክስ በአመንምን በሽታ እየገደለው ያለ?
 • የኤርትራ መንግሥት ራሱ በጫረው ጦርነት ላጋጠመው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሽንፈት/ኪሳራ በማስመልከት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር ኃይለ ወልደትንሳኤ (ድሩዕ) ከባድመ ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ፍራንክፈርት ጀርመን ተገኝተው ለኤርትራውያን ባደረጉት ንግግር ወያኔን በዚህ መልኩ ነበር የገለጹት “ወያኔ አሽመድምዶናል/አሽመድምዶን ነበር!” ሲሉ። እናማ ሻዕቢያ የሚፈራ ኃይል ቢሆን ነዋ የተብረከረከው? (በነገራችን ላይ ተናጋሪው ይህን ንግግራቸው ተከትሎ ወደ እስር ከተወረወሩ ጊዜ ጀምሮ በአሁን ስዓት በህይወት ይኑሩ አይኑሩ የሚታወቅ ነገር የለም።)
 • በአሜሪካ የኤርትራ ኢምባሲ አምባሳደር አድሃኖም ገብረማርያምም እንዲህ ይላሉ “ወያኔ አሽመድምዶናል/አሽመድምዶን ነበር! በጣም ቀላል አገላለጽ ነው። ወያኔ መሬታችን ተገለባብጠውበታል/አክሮባት ሰርተውበታል ነው የሚባለው። በመጨረሻም ራሳቸው ነው ከኤርትራ ምድር ሠራዊታቸው ያወጡ እንጅ ማንም ያስወጣቸው ኃይል አልነበረ/የለም። ሐቁ ይህ ነው።” ሲሉ የገለጹት የሻዕቢያን ኃያልነት መናገራቸው/መመስከራቸው ነዋ?

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E- mail- yetdgnayalehe@gmail.com 

Oct 2, 2013

Advertisements