የጠፋው ልጅ ኢሳይያስ አፈወርቂ “Vs.” አንዳርጋቸው ጽጌ፡

ፕሬሶች በአዋጅ የዘጋ፤ ጋዜጠኞችና ሚኒስትሮቹን በጅምላ ወደ ግዞት ያወረደ፤ የክርስትና እምነት ተከታዮች መሪዎችና ምዕመናን ኮንተይኔር ውስጥ ቆልፎ የሚያሰቃይ፣ የሚያመነምንና የሚገድል፤ አብሮ አደጎቹ ታጋዮች ከመሬት በታች በተቆፈሩ ጉድጓዶች ውስጥ የሚያኖር፤ ህግ የሌላት/ብርቅ የሆነባትና በአንድ ግለሰብ የዕለት ዕለት አስተሳሰብና አመለካከት የምትመራ አገር ባለቤት በሆኑ በፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ዘንድ ቀልድ ብሎ ነገር ቦታ የለውም። በተግባር ቀርቶ በሃሳብ ደረጃ ከህግደፍ ውስጠ ደንብ የማዘንበል አዝማምያ የሚያሳይ ባለ ሥልጣን፣ ተራ ዜጋ ሆነ ተላላኪ/ባንዳ ቀድሞ መቃብሩ የቆፈረ እንደሆነ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ላለፉት አሥራ ሁለት ዓመታት በኤርትራ ምድር በገሃድ ያየነው ሐቅ ነው። 

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የተባሉ “የኢትዮጽያ መንግሥት ውስጠ አዋቂ” ነኝ ባይ ነጻ ያልወጡ “ነጻ አውጪ” “ከአስመራ” አሜሪካ ድረስ መጥተው ሲያበቁ ታድያ ያመጣቸው ርዕሰ ጉዳይ ትተው (አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከአስመራ አሜሪካ ድረስ የመጡ የኤርትራ ሕዝብና መንግሥት ለማዋረድ ከሆነ ተልዕኳቸው በሚገባ አሳክተዋል) ያልዋሉበትን ሲዘላብዱ እኛን (ኢትዮጵያውያን) በቆይታቸው ደህና አድርገው እንዳዝናኑን ሁሉ ኤርትራውያንና የኤርትራ መንግሥት ከእኛ ጋር እኩል ቁጭ ብለው ሙድ ይይዛሉ የሚል እምነት የለኝም። ይልቁንስ አቶ አንዳርጋቸው በጊዜ ውስጥ የሚጠብቃቸው የቅጣት ዓይነት ወዲ አፎም ብቻ ነው የሚያውቀው። ያም ሆነ ይህ የኤርትራ ህዝብ ቃላት የማይገልጸው ችግር፣ ባርነትና ሰቆቋ እንዲሁም የኤርትራ መንግሥት ወታደራዊና ፓለቲካዊ ቀውስ/ኪሳራ ወይም ውድቀት  ለማወቅ አስመራ ድረስ መሄድ አላስፈለገንም። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስለ ትልቋ እስር ቤት ሀገረ ኤርትራ ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ ማወቅ የሚገባንን ሁሉ “በቅንነትና” “በታማንነት” አስኮምኩመውናል።

ጥብቅ ማሳሰብያ፥ 

የኤርትራ ሕዝብ ለ፴ ዓመታት ያደረገውን ትግልና የከፈለውን መስዋዕትነት “ኤርትራን እንደ አንዲት ራስዋን የቻለች ነጻና አዲስትዋ ሉዓላዊት አገርና ሕዝብ ለማቆም ነው!” ስል የማቀርበው ጽሑፍ ከራሴ የተገኘ ሳይሆን መንግስታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የኤርትራ የመገናኛ ብዙሐን የዕለት ዕለት ሐተታና ትንተና ጨምሮ በጉዳዩ የኤርትራ መንግሥት ሆነ የኤርትራ ሕዝብ፤  ህጋዊ ውክልና ያላቸው የአገሪትዋ ባለ ሥልጣናት ከነጻነት በፊትም ሆነ በኋላ በአገሪትዋ ቋንቋ ተጽፈው ለንባብ የበቁ የተለያዩ መጻህፍት የሚሉትንና የሚያስነብቡትን የተገኘ/መሰረት ያደረገ መሆኑን ስገልጽ በአክብሮት ነው።

ሐተታ፥

ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ አገር ሆና የመቅረትዋ ነገር የማን ጥፋት ነው? የአቶ መለስ ጥፋት ነው? የኤርትራውያን ጥፋት ነው? የማን ጥፋት ነው? የባህር በሩ ላይ የእናንተ አቋም ምንድ ነው? ሲል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ እንጀምር።

“… ኤርትራ ፋታ እግኝታ ሕዝቡ ደቡብ ሱዳን ላይ እንደ ተወሰደ ዓይነቱ ውሳኔ ማለት ነው የአምስት ዓመት እረፍት አግኝቶ ጉዳቱንና ጥቅሙን ከነጻነት መልስ በሆነ መንገድ በፌደሬሽን ይሁን በኮንፈደሬሽን ይሁን በሌላ ‘አረኝጅመት’ መኖር ይሻላል ያለው።” አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

አንደኛ፡ (ሀ) የኤርትራ ሕዝብ ፴ ዓመት ሙሉ የታገለው ምን ለመሆን ነበር ነውና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይህን ለማለት የደፈሩ? የኤርትራ ሕዝብ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የከፈለው መስዋዕትነት ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን አልያም በኮንፈደሬሽን ለመጠቅለል ነበር/ነው ወይ? በእውነቱ የእኝህ ነጻነት የማያውቁ “ነጻ አውጪ” ግለሰብ ምጸታዊ አነጋገር በትግሉ እንደ አገር የቆመ ሕዝብ መስደብ አይሆንም ወይ? ወይስ በትግራይ ልጆች መስዋዕትነት መሳቅና መቀለድ የለመዱ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኤርትራ ልጆችም አመል ሁኖባቸው ተመሳሳይ ቅሌት መድገማቸው ነው? ምንም እንኳ የኤርትራ መንግሥት በሀገራችን ዙሪያ የሚያንጃብቡ ጠላቶች ሁሉ መናገሻ ቢሆንም በትግሉ ኤርትራን ያቆመ ሕዝብ ግን የኤርትራ እንደ አገር መቆም በስለት ወይም በምትሃት የሆነ ነገር/ያመጣው ሳይሆን የልጆቹን ደም ገብሮ ያመጣው የመስዋዕትነት ፍሬ  መሆኑን እንዴት ማስተዋል አቃታቸው?

(ለ) የኤርትራ እንደ አንድ ሕዝብና አንደ አንዲት ነጻና ሉዓላዊት አገር የማቆም/የመቆም አጀንዳ ደግሞ እርስዎ እንደሚሉት መሸታ ቤት ተጠንስሶ እዛው በሞቅታ ውሳኔ ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ሳይሆን ፴ ዓመታት የወሰደውን የኤርትራ ሕዝብ የትግል ህይወት መንስኤ ነው። ቅጣትዎት ያቅልሎት!!

(ሐ) ከመነሻው እስከ መጨረሻ የኤርትራ ሕዝብ ትግልና አጀንዳ ኤርትራን እንደ አገር የማቆም ግልጽ አጀንዳ እንጅ ከነጻነት በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራት የሚችለውን ግኑኝነት በፌደሬሽን አልያም በኮንፈደሬሽን አብሮ የመቀጠል አጀንዳ አልነበረም አይደለምም። በኤርትራ በኩል እዚህ ጥግ ድረስ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበት ምክንያትም በዋናነት ኤርትራ እንደ አገር የቆመች ዕለት ኢትዮጵያ ነፍስ ዘርታ ትኖራለች የሚል እምነት ስላልነበረ ነው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ኤርትራ መዳፍ ሥር ነው ተብሎ ስለሚታመን ነበር። የታለመው ህልም ሲፈታ ፍቺው ለየቅል ሆነ እንጅ።

(መ) በመሰረቱ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኤርትራን ወክለው ይህን ሲሉ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ተወያይቶውበትና መክረውበት በኤርትራ መንግሥት አፍ ፈንታ በአማርኛ ቋንቋ ከዋሽንግተን ዲሲ መናገራቸው ነው? ወይስ እንዲህ ያለ የደም ዋጋ የተከፈለበት ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ ገብተው ለመፈትፈት ድፍረቱ ያገኙ ከኤርትራ ሕዝብ ይሁንታ አግኝተው ነው? ወይስ ውሎ አድሮ የህይወት ዋጋ የሚያስከፍላቸው ከአጉል ቅናት የተነሳ የቀላቀሉት ስህተት ነው?

ሁለተኛ፡ (ሀ) ሌላው የዚህ ንግግር ፖለቲካዊ ገጽታው የተመለከትን እንደሆነ የንግግሩ አንኳር መልዕክት አሁን ኤርትራ የምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መስተዋት ነው። ይኸውም፥ በሚገርም መልኩ የኤርትራ መንግሥት አሁን ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ ሩቅ መሄድ እንደማይችል፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካዊ አቅምም ከምን ጊዜ በላይ እንደወደቀና የኢትዮጵያ የእርዳታ እጅ በብርቱ የሚያስፈልጋት አገር ለመሆንዋ በግልጽ ቋንቋ የሚያመላክት ነው።

(ለ) አቶ አንዳርጋቸው ይህ የኤርትራ ሕዝብ ውሳኔ የሚያንኳስስ ንግግራቸው በአቶ ኢሳይያስ ፈቃድ ከሆነ ወይም  ፍሬ ነገሩ የፕሬዝዳንቱ እምነትና ሃሳብ ከሆነ አቶ ኢሳይያስ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በመጠቀም አመጹን በማጧጧፍ  አንድ በተሎ ሊገላገሉት የፈለጉት ከአቅማቸው በላይ የሆነና ያስመረራቸው የአገራቸው ጉዳይ እንዳለ ማየት ይቻላል።

(ሐ) ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ይህን ለማድረግ የተገደዱበት ማለትም ነገራቸው በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኩል ማስኬድ የፈለጉበት ምክንያት ደግሞ በቀጥታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የእርቀ ሰላም አጀንዳ ለመያዝ ተነሳሽነት ማሳየትም ሆነ ጉዳዩ በዲፕሎማሲ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ ልኡካን ማዘጋጀት ውርደት ሆኖ ስለታያቸው ነው። ይህ ደግሞ የሚያመራን አቶ ኢሳይያስ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በማደራጀት ሥራ ላይ የተጠመዱ አንድና ሁለት በሌለው ሁኔታ በማንኪያ ሰጥተው በአካፋ የሚቀበሉበት ዕድል ማመቻቸታቸው ነው።

(መ) አቶ አንዳርጋቸው ሌላ ሊነግሩን የፈለጉት ቁምነገር “ምን ነው እኔ ያየኹትን የአስመራ ጉድ ባያችሁ!” እያሉን ነው። ይህ ማለት “የኤርትራ መንግሥት ሪፈረንደም! ሪፈረንደም! ሲል በወሰነው ውሳኔ ተጸጽተዋል፣ አገሪትዋ ችግር ላይ ነች፣ ነገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ ከቀጠሉ የኤርትራ መንግሥት እንደ መንግሥት የመቀጠል ዕድሉ ተመናምነዋል።” እያሉን ነው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ። አክለውም “በአሁን ሰዓት የኤርትራ መንግሥት በእኛ በኩልም ሆነ አሁን ስልጣን ላይ ከሚገኘው መንግሥት የመነጋገር ዕድል ቢያገኝ የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ የሚፈልገው ነገር ቢኖር አንድና አንድ ነው ይኸውም ኢትዮጵያ በሚያቀርብለት ማናቸውም አማራጮች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ መዋሃድ መመለስ ይፈልጋል።” ነው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ መልዕክት። ጎበዝ! ቢሆን ነው እንጅ ከዚህ ቀደም ከአገሪቱ ባለ ሥልጣናት ሆነ ከተራ ዜጎችዋ ተሰምቶ የማይታወቅ ከሃያ ዓመት በኋላ እንዲህ ያለ የልመና ቃል ማሰማት ታድያ ምን ይሉታል? አቶ እንዳርጋቸው ይህን መልዕክት በኢሳት በኩል ይናገሩ  ዘንድ የአቶ ኢሳይያስ ምክር ይሁን አይሁን ግን ኃላፊነቱን አልወስድም።

ለማንኛውም የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የምህጽንታ ቃል ስሰማ ወደ አእምሮየ በቀጥታ የመጣው በመጽሐፍ ቅዱስ በተለምዶ “የጠፋው ልጅ” ተብሎ የሚታወቀው የእግዚአብሔር የምህረቱ ብዛትና ገናናነት የሚተርክ ክፍል/አንቀጽ ነበር ያስታውሰኝ። ልዩነቱ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰፈረው ባለ ታሪክ (የጠፋው ልጅ) ቀድሞ የወሰደው እርምጃ ተከትሎ የሚገኝበት ምስቅልቅል ያለ ህይወት ተጠያቂ ራሱ እንደሆነ አምኖ በመቀበል ወደ አባቱ ቤት ሲመልስ የአቶ ኢሳይያስ ነገር ደግሞ ምንም እንኳ ጥፋቱም ሆነ አገሪትዋ አሁን የምትገኝበት አስከፊ ሁኔታ አምነው ቢቀበሉም ለመፍትሔው ግን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ  ስህተትን በስህተት ለማስተካከል መሰለፋቸው ለየት ያደርገዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ይህ የሳህል በርሃ አሰራር በመተው በጊዜ ሳይመሽ የሚሆን ቢያደርጉ ግን አገራቸውና ሕዝብቸው እንደሚያተርፉ አልጠራጠርም።

ቃሉ እንደሚከተለው ይነበባል፥

“እንዲህም አለ፦ አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን። አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገዘቡን በተነ። ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም። ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊጥ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞጭ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ልጁም። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው። አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ። ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር።” (የሉቃስ ወንጌል  15፥ 11- 24)

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E- mail- yetdgnayalehe@gmail.com

Oct 1, 2013

Advertisements