የከሰረ የሲዖል ፈላስፋው ኢሳይያስ አፈወርቂ “Vs.” ሲ. አይ ኤ፡

Isaias Afewerki Vs. CIA

ይህ የሚመለከቱት መታወቂያ አሥመራ ከተማ ቃኘው ተብሎ በሚታወቀው የአሜሪካ መንግሥት የስለላና የመረጃ ማዕከል ተጋዳላይ ኢሳይያስ አፈወርቂ በሚፈለጉበት ሰዓት አንደ አባታቸው ቤት ገብተው የሚወጡበት ወጥተውም የሚገቡበት ልዩ የይለፍ መታወቂያ ነው።

የጽሑፉ ዓላማ፥

የኤርትራና የኤርትራውያን የትግል ታሪክ መዛግብት፤ በወቅቱ በጉዳዩ ቀዳሚ እጅና አስተዋጽዖ የነበራቸው ትውልደ ኤርትራውያን የዓይን ምስክሮች እንደሚተርኩትና እንደሚያወሱት የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂና የምዕራባውያን ሀገራት የጠበቀ ግኑኝነት የማይገልጸው ወዳጅነት ምን ይመስል እንደ ነበረና ይህን ግኑኝነት የሻከረበት ምክንያትም በጣም በጥቂቱ የሚያስቃኝ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውን ለማድማት የተሰለፉ የጥፋት መልዕክተኛ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጨምሮ የመረጃ እጥረት ላላቸው ዜጎች ሁሉ መረጃ ለማድረስ ተጻፈ።

የጽሑፉ ውሱንነት፡

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ እንደ አንድ ግለሰብ ጠንካራና ደካማ ጎን ያላቸው የሀገር መሪ ናቸው። ፕሬዝዳንቱ ምንም እንኳ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ በኤርትራ የቴሌቪዥን ጣቢያና ድምጺ ሓፋሽ ኤርትራ እየቀረቡ በሚሰጥዋቸው ቃለ ምልልሶች ተራ ዜጋ ሳይቀር የሚያስደምሙ፣ ግር የሚያሰኙና በውል ነገሮች መቀላቀል የጀመሩበት አዲስ ምዕራፍ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ይዘትና ውስንነት ግን በግለሰቡ ግለ ጸባይና  የእብደት ልምምዶች የሚያተኩር ሳይሆን ተስፋሚካኤል ጆርጆ የተባሉ ኤርትራዊ ጸሐፊ ጥር 1974 ዓ/ም አምስት ጸሐፊያን በጥምር “የምጽዋ ሲምፖዝዩም” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 44- 62  “የተገጣዮችና የሲ.አይ.ኤ ግኑኝነት” በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር በጻፉት ታሪካዊ ሰነድ ብቻ ላይ መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው።

ሐተታ፥ 

እርግጥ ነው ስለ ኤርትራ ሆነ ስለ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የሚጽያፍ አንዳች ጉዳይ የለኝም። በመርህ ደረጃ ለኤርትራና ለኤርትራውያን የሚበጀውንና የሚረባውን የሚያውቅ ኤርትራዊ “ብቻ” ነውና። ሆነም ግን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስብስብ የሆነችው የአገራችን የኢትዮጵያ አገር በቀል ጠላቶች ስንዋጋ ሳይጠሩና ሳይፈለጉ ከነ ተረቱም “አይጥ ለሞትዋ የድመት አፍንጫ ታሸታለች” እንደሚባለው በቀደመ ዱላ ትምህርት ያልወሰዱ ቀቢጸ ተስፋ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ሳይጠሩ አቤት ማለታቸው ስላልተው ብቻ ነው። እንግዲህ፦

  • አቶ ኢሳይያስ ማለት አሥመራ ከተማ ቁጭ ብለው መላ ዓለም በምላሳቸው የሚያስሱ፣ የሚያዳርሱና የመጨረሻ የየቅዠት “ብጽእና” ደረጃ የደረሱ አገራቸው እንደ አገር ማስቀጠል የተሳናቸው ገዢ መሆናቸው እየታወቀ፤ 
  • አቶ ኢሳይያስ በምላሳቸው ብቻ የሚታይና የማይታይ ዓለም አንቀጥቅጠው የሚገዙና የሚያስተዳድሩ የከሰረ የሲዖል ፈላስፋ መሆናቸው እየታወቀ፤ 
  • አቶ ኢሳይያስ ማለት በገዛ አገራቸውና ሕዝባቸው እያደረሱት ያለው መጠነ ሰፊ ትውልድ የመጨረስ፣ የመቅጨትና የማጥፋት ዘመቻ ተደብቆ የማይደበቅ አሰቃቂ የምድሪቱ ግፍና በደልም ዋና መሃንዲስ ሆኖ ሳለ፤ 
  • ፕሬዳዝዳንት ኢሳይያስ ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየፈጸሙ እስከ ዛሬ ድረስ በህይወት የመሰንበታቸው ምስጢር የሚረከባቸው ኃይል በመጥፋቱ ብቻ በበሰበሰ ዙፋን ላይ የተቀመጡ የሌለች አገር ለይስሙላ የሀገር መሪ ተብለው የሚታወቁ  የትልቅዋ እስር ቤት ሀገረ ኤርትራ መንዳቢ መሆናቸው እየታወቀ፤ 
  • አቶ ኢሳይያስ በምላሳቸው ከጸሐይ በታችም ሆነ ከጸሐይ በላይ እሳቸው የማያውቁት ከእሳቸው የተሰውረ አንዳች እውቀት ባይኖርም መሬት ያለው የሚመርዋት አገር ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከአቅርቦት እጦት የተነሳ ወታደሮቹ በ90ዎቹ መጨረሻ የሰበሰቡት አስርት ዓመታት ያስቆጠረ የጠነበሰና የከራረመ ደረቅ እንጀራ በወንዝ ውሃ የሚመግብ መንግሥት ሆኖ ሳለ የሰው አገር ለማድማትና የሕዝቦች ስላም ለማደፍረስ ግን እንቅልፍ አጥተው የምላስ አርበኞችና ባንዳዎች አሰልፈውብናል።

ለምሳሌ ያክል የተመለከትን እንደሆነ ባሳለፍነው ሳምንት አቶ አንዳርጋቸው የተባሉ አንድ ኢትዮጵያዊ ኮሌነል በዛብህ ጴጥሮስ ማስለቀቅ የተሳናቸው ግለሰብ ዳሩ ግን ሰማኒያ ሚልዮን “ነጻ አወጣለሁ!” ባይ የነጻነት ትርጉም ያጠፉብን ቀልደኛ በበላይነት የሚመሩት የግንቦት 7 ልሳን በሆነው በኢሳት ቀርበው ከላይ ከፍ ሲል የተመለከትናቸው ድፍን ዓለም በአንድ ጉዳይ አንጥሮና አበጥሮ የሚያውቃቸው ፕሬዳዝዳንት ኢሳይያስና  ሻዕቢያ በተመለከተ እንዲህ ይላሉ።

የሀገርና የሕዝብ ክብር የሚባል ነገር አለ ሻዕቢያ ጋር። የምልህ ያለኸው ድሃ ነን ነገር ግን ከድህነት በምጽዋት ለመውጣት አንዋረድም የሚል አመለካከት አላቸው። ከሦስት አስከ አራት ቢልዮን እርዳታ ኢትዮጵያ ታገኛለች ያለው አምስት ሳንቲም ግን እርዳታ ኤርትራ አታገኝም ያለው። ያንን ገንዘብ አግኝቶ ሥራ ላይ ለማዋል አለመፈለግ አይደለም ገንዘቡን ስጡን ሥራ ላይ እናውላለን እንደማነርቀው እንደማናጭበረብር መከታተል ትችላላችሁ ነገር ግን እናንተ በፈለጋችሁትና በውስጥ ፖሊሲያችንን ተጽእኖ ማሳደር በሚችል መንገድ እኛ ይጠቅማል በማንለው ቦታ ላይ ለእናንተ ልጆችና ዘመዶች ደመወዝ መክፊያ በሚሆንበት መልኩ እርዳታ ሰጥተናል እያላችሁ እንድታሾፉ ግን አንፈቅድም ነው እያሉ ያሉት።” አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

አዳፍኔ ምስክርነት በመስጠት የተካኑ እንደ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሐሰት ምስክርነት መሰረት “አቶ ኢሳይያስ ለምራባውያን መንግሥታት የማይንበረከኩ፤ የማይበገሩና ሕዝባቸው ጥይት የማይበሳው ዳቦ ጋግረው የሚያጎርሱ፤ ምንም በተጽእኖ ውስጥ ቢሆኑም ያሰቡትን ከማድረግ የማይመለሱ ጀግና መሪ ናቸው” በማለት በውዳሴ እያሽሞነሞኑ ሲያስተዋውቁንና በተራ ቃላት ሲያደክሙን አቶ አንዳርጋቸው ኢሳይያስ አፈወርቂን ጥጦ እያጠባ ያሳደገ፣ በሞራልና በማተርያል ያደራጀ ከዚህም አልፎ ሁለት እጃቸውን ይዞ ወደ አሥመራ ቤተ መንግሥት/ወደ ሥልጣን ያመጣ፣ እስከ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግሥት ድረስ የአስመራ መንግሥት የጀርባ አጥንት ስለ ነበረ ኃይል/መንግሥት ግን አልነገሩንም። ለመሆኑ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኤርትራም ሆነች አቶ ኢሳይያስ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ለማስተዋወቅ የደፈሩበት ምክንያት ምንድ ነው? ማንስ ሆዳቸው ቢረግጣቸው ነው እንደ ክፉ ደብተራ ያልተጻፈ የሚያነቡልን?

አቶ ኢሳይያስ አፋቸው በከፈቱ ቁጥርና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲ.አይ.ኤ ሆነ የአሜሪካ መንግሥት ሳይወነጅሉ፣ ሳያብጠለጥሉ፣ ሳይዘልፉና ሳይወነጅሉ ያለፉበት ዕለት የለም ቢባል ማጋነን አይደለም። በሌላ አነጋገር አቶ ኢሳይያስ በመንግሥትነት የሚመርዋት ትልቅዋ እስር ቤት ሀገረ ኤርትራ አሁን ለምትገኝበት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፤ አገራቸው ጥለው የሚኮበልሉ ወጣቶች ቁጥር መበራከት፤ የሕዝቦችዋ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋና እየከረፋ የመጣው የዘቀጠ የኑሮ ደረጃ፤ በአጠቃላይ ኤርትራ አሁን ለምትገኝበት ድቅድቅ ጨለማ በቃላት ተገልጾም የማያልቅ ምስቅልቅል ያለ የዜጎችዋ ህይወት በዋናነት የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲ.አይ.ኤን ተጠያቂ ሲያደርጉ ነው የምንሰማቸው። (ሲ.አይ.ኤ ምግባረ ሰናይ ድርጀት ነው እያልኩ እንዳልሆነ አንባቢ እንዲገነዘብልኝ እወዳለሁ።)

አቶ ኢሳይያስ ሲ.አይ.ኤ ሆነ የአሜሪካ መንግሥት በነጋ በጠባ ቁጥር የእርግማን መዓት የሚያወርዱበት ምክንያት ምን ቢያገናኛቸው ነው? አቶ ኢሳይያስ ለመንግሥትነት ያበቃ ኃይል ማን ሆኖ ነውና ዛሬ አቶ ኢሳይያስ በምዕራባውያን ያላቸው አቋም ትኩረት ተሰጥጦት አቶ ኢሳይያስ የሚወደሱና የሚሞገሱ? ለመሆኑ የትናንቱ ሽምቅ ተዋጋ የዛሬው የሀገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂና የምዕራባውያን መንግሥታት ግኑኝነት ምን ይመስል ነበር? ጸቡስ እንዴትና መቼ ተጀመረ? ለመሆኑ ኤርትራ ማን ናት ምንድ ናት? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው።

ሁላችን እንደምናውቀው ኤርትራ እስከ 1890 እ.አ.አ እንደ አገር ምንም ዓይነት ህልውና ያልነበራትና የትግራይ ክፍለ ግዛት የነበረች ለጣልያን ተላልፋ ከተሰጠች በኋላ ግን ጣሊያን ኤርትራ ሲል የሰየማት አገር መሆንዋን ይታወቃል። ወደ ርዕሳችን የተመለስን እንደሆነ ወደኋላ መለስ ብለን የኤርትራና የኤርትራውያን በተለይ በአቶ ኢሳይያስ ይመራ የነበረውን የትግል መስመር አደረጃጀት፣ እድገትና ግብ ታሪክን በጥንቃቄና በጥልቀት የመረመርን እንደሆነ አቶ አንዳጋቸው ሳያፍሩ እንደቀደዱልን ሳይሆን እውነቱ የአቶ ኢሳይያስ ከአሜሪካ መንግስትም ሆነ ከሲ.አይ.ኤ ጋር መላተም የአቶ ኢሳይያስ አገር ወዳድነትና አርበኝነት ሳይሆን ምስጢሩ የታጋይ ኢሳይያስ ከጀብሃ መገንጠል ማግስት ጀምሮ አቶ ኢሳይያስ ወታደራዊ አቅማቸው ለመገንባትና ተቃናቃዮቻቸው የውኃ ሽታ ለማድረግ አጋጣሚዎች ሁሉ ለመጠቀም በወሰዱት እርምጃ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የስለላ ድርጅቶችም እርዳታ ሊያገኙ በሚችሉበት መንገድ የተለያዩ ታሪኮች በመፍጠር ግኑኝነት መጀመራቸውን ተያይዞ በወቅቱ ከአሜሪካ መንግሥት ለሚሰጣቸው ተልዕኮ በአግባቡ እስከተወጡ ድረስ ማንኛውም ዓይነት ዕርዳታ ለማግኘት እንደሚችሉ ከሲ.አይ.ኤ በተሰጣቸው አፈጣኝ ምላሽ አቶ ኢሳይያስ ዓይናቸውን ሳያሹ ጊዜያዊ ጥቅማ ጥቅሞች ለማግኘት ሲሉ ብቻ የአገራቸውና የህዝባቸውን ጥቅም አሳልፈው በመስጠት የተፈራረሙት ውሎችና የፈጸሙት የሀገር ክህደት ወንጀል ከተጠያቂነት ለማምለጥ እንዲሁም የኤርትራ ሕዝብ ድጋሜ ለመደለል እንደውም አቶ ኢሳይያስ ሲ.አይ.ኤ ተብሎ ከሚታወቅ ስጋ ለበስ ማህበረ አጋንንት የስለላ ድርጅት ምንም ዓይነት ግኑኝነትም ሆነ እውቀት እንዳልነበራቸው ለመሸምጠጥ ሆነ ተብሎ አስበውበት እያደረጉት ያለ የክህደት ሥራ ነው። የሚያሳዝነው ይህን ታሪክ ጠንቅቀው የሚያውቁ በዓላ በርሃ አከባቢ ከነበሩ ታጋዮች መካከል ዛሬ አንዳቸውም በህይወት የሉም።

ይህን በተመለከተ ማለትም አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በሕዝባቸውና በሀገራቸው የፈጸሙት ክህደት፣ አድርባይነት፣ ነፈሰ ገዳይነትና በተለይ ፕሬዝዳንቱ ከአሜሪካ መንግስት የስለላ ድርጅት ጋር የነበራቸው ወዳጅነትና ስምምነቶች በስፋትና በጥልቀት የሚዳስስ ከመታሰቤ በፊት ለህትመት የበቃ ለጸሐፊው ህይወት መቀጨትም ምክንያት የሆነ ሰነድ ሊንኩን በመጫን ማንበብ ይችላሉ http://www.ehrea.org/TesfaMikegiorgioAmarina.pdf

ሰነዱ “የምጽዋ ሲምፖዝዩም” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ ለህትመት የበቃ ጥር 1974 ዓ/ም [ምጽዋ] ሲሆን ጸሐፊው ተስፋሚካኤል ጆርጆ ይባለሉ። ተስፋሚካኤል ጆርጆ በኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ ሥርዓት የደቀ ምሐረ ወረዳ ገዥ የነበሩ፤ በወቅቱ ሻዕቢያ ለማግባባት ከተሰየመው ጉባኤ አባላት መካከል አንዱ ሲሆኑ ኢሳያያስ ከዓላ በርሃ እጁን ይዘው አስመራ ድረስ በመምጣት በኤርትራ ክፍለ ሀገር በችግኝ ተከላ ሽፋኝ ይንቀሳቀስ ከነበረ በቀንድ አፍሪካ የሲ.አይ.ኤ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ሪቻርድ ፓውላንድ ያገናኙ ሰው ናቸው። የጀብሃ በወያኔና ህግሓኤ ትብብር መመታት ተያይዞ በሱዳን በኩል ወደ ውጭ ለመውጣት ያደረጉት ሙከራ ቀደም ብለው በአቶ ኢሳይያስና በሲ.አይ.ኤ መካከል የነበረ ግኑኝነት ይፋ በማድረጋቸው ከአሜሪካ መንግሥት ጥግተኝነት ሳያገኙ የቀሩና ከዚያ በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ይኖሩ እንደ ነበርና ሚያዝያ 13/1982 ዓ/ም በአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች መኸል አዲስ አበባ በድምጽ አልባ መሳሪያ ተደብድበው የተገደሉ ሰው ናቸው።

በነገራችን ላይ አቶ ኢሳይያስ በአሜሪካ መንግሥት ሆነ በሲ.አይ.ኤ ላይ አፋቸው ማላቀቅና ጸረ ምዕራባውያን ሀገራት አቋም ማንጸባረቅ የጀመሩት አቶ ኢሳይያስ በአንድ ወቅት በጀርመን አገር የሚገኙ ኤርትራውያን ሰብሰበው፦

“በባድመ ጦርነት ስለሆነ ነገር ራስህን ማባበል የምትችለው ነገር አይደለም። በእውነት ለመናገር ከሆነ ቆሽጥን የሚያሳርር ነው። ከምገልጸው በላይ የከፋ ነገር ነው የተፈጸመው። ሌላ መግለጫ የለውም። በውግያው የተሳተፉ ያውቁታል። ስትናገረው መልሶ መላልሶ የሚያናድድና የሚያበግን ነው። ይህ የምናገረው ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን ነው።” 

ሲሉ የገለጹት ለአንዴና ለመጨረሻ በባድመ ተጀምሮ በባድመ የተገባደደውን የአቶ ኢሳይያስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የመሆን ህልም የከሰመበትና አቶ ኢሳይያስ ባሰቡት ቁጥር የሲዖል ያህል የሚከብዳቸው የሞት ያህልም የሚመራቸው ጉም የዘገኑበትና የሲዖል ፈላስፋ ሆነው አርፈው የተቀመጡበት ከባድመ ጦርነት በኋላ እንደነበር ታሪክ ልብ ይለዋል። አቶ ኢሳይያስ በምዕራባውያን ላይ ምላሳቸውን ማስረዘም የጀመሩ እንግዲህ ከባድመ ጦርነት ሽንፈት ወዲህ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያትም አቶ ኢሳይያስ ኢትዮጵያን ስወጋ አሜሪካ ለምን አልደገፈችኝም?! ለምን ከጎኔ አልቆመችም?! ከሚል አጉል ልጅነትና እልህ ነበር። ሕዝባቸው እንደ እህል እየፈጩትና በማጭድ እየላጩት የሚገኙም ከአሜሪካ ጋር እልህ መጋባት ከጀመሩ ወዲህ ነው (በሰፊው)። ከዚያ በፊት የሁለትዮሽ የወዳጅነት ግኑኝነት ምን ይመስል ነበር? በማለት ጥያቄ ያነሳን እንደሆነ ግን አሜሪካውያን አቶ ኢሳይያስን “መተኪያ የሌለው!” በማለት ሲያወዳድሱት አቶ ኢሳይያስም በተመሳሳይ ጌቶቹን በቁልምጫ ይቀዳና ይጠራ እንደነበር ነው የሚታወቀው።

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Sep. 28, 2013

Advertisements