ለምን ተለያይተንም ቢሆን አንሞክረውም?

በእርግጥ ጸሐፊው በሰላምም ሆነ በጠመንጃ በየትኛም መንገድ መለያየትም ሆነ መበጣጠስ ችግርን የሚያባብስ የመልካም ነገር ሁሉ ተቃራኒ፣ የጥፋትም ሁሉ ራስና አውራ እንደሆነ እንጅ መፍትሔ ነው የሚል እምነት የላቸውም። ምክንያቱም የአንድ አካል ብልቶች ምንም እንኳን በቅርፃቸው፣ በስማቸው፣ እንዲሁም በሥራ ድርሻቸውና በአቀማመጣቸው ልዩ ልዩ ቢሆኑም እንደ አንድ የአካል ስሪቶች አንዱ በአንዱ ላይ ሳያምጽና የበላይነትንም ሳያንጸባርቅ ለአንድ አካል በወጥነትና በህብረት ተባብረው እንደሚሰሩ ሁሉ እንዲሁም የቁጥሩ ያክል ልዩነት የሚታይበት የሰው ልጁም እንደሆነ በተቻለ መጠን ልዩነትን በማጥበብ ሊደረስ የሚችለውን ሰላማዊ የሆነ ቅብብልና የጋራ ጥቅም ላይ ያተኮረ ሕብረትና ስምምነት ገንዘብ ማድረግ ይቻላል ብለው አጥብቀው ስለሚያምኑ ነው።

ቢሆንም ግን እንዲህ ያለ ገንቢ አመለካከት እምብዛም የማይዋጥላቸው በጣት የሚቆጠሩ ከራሳቸው አልፈው ማንንም ሊወክሉ የማይችሉ ራስ ወዳድ ግለሰቦች ከቀደመ ስህተታቸው እርምት ሳይወስዱና ሳይስተካከሉ ዳግም ነፍስ ዘርተው በተለያየ መንገድ ሕዝብን የማሳሳት ተግባር ላይ ተሰማርተው ውዥንብርን ሲፈጥሩና እሳት ሲጭሩ ማየቱ የተለመደ ሆነዋል። እንግዲህ እነዚህ ጥላቻና አመጻ የወለዳቸው ጥቃቅን ቀበሮዎች የማጥመድ፣ እጃቸው ምክራቸውን እንዳይፈጽም የማምከን፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ የሚያነሳሳ መሰረተ ቢስ ክሶቻቸውን የመንፈግና ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ደም የሚያቃባ አጀንዳቸውን የመቃወም የአለመቀበልና ድጋፍን የመንፈግ ሚና/ድርሻ የዜጎች ሁሉ ግዴታ እንደሆነ ለማሳሰብ፤ ራሳችን ለመልካም፣ በጎ ለሆነ ሁሉ እንዲሁም ሰላምን የሚሻ ልብ ሳይኖረን የቀረ እንደሆነ ግን የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ በዙሪያችን የተንጠለጠለውን የጥፋትና የዋይታ ደመና ለማመላከት ተጻፈ።

የሰው ልጅ አይደለም ከባለ እንጀራው ከራሱ ጋርም ቢሆን ምክንያት ፈጥሮ ለመጣላትና ራሱን ለመጣል አልሞና አቅዶ የተነሳ እንደሆነ እጅግ ቅርብ፣ የሚያቆመውም የሌለው ቀላል ፍጥረት ነው። እንደ የአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ልጆች ሰላም ለመፍጥርና እርስበርስ በመዋደድ፣ በምህረትና በይቅርባይነት ላይ የተመሰረተ ህይወት ለመኖር ብዙ ምክንያት እንዳለን ሁሉ እንደ ሕዝብ እርስ በርስ ተጨፋጭፈን ለመተላለቅ፣ ጦር ተማዘን ደም ለመፋሰስ እንዲሁም ተለያይተንና ተበጣጥሰን ዘንተዓለማችን እንደ ጋለሞታ ልጆች በጎሪጥ እየተያየን ለመኖርም ብዙ ምክንያት አለን። በነገራችን ላይ ጸብ ከፈፈለገ አሁንኑ ከ70- 80 የሚደርሰው ቋንቋችን ባህላዊ ልማዶቻችንና ወጎቻችንን፣ ሃይማኖታችን፣ የመልከዓ ምድር አቀማመጣችን፣ ታሪካዊ አመጣጣችን ወዘተ ምክንያቶችን በመደረደር እርስበርስ ተበቋቅሰንና ተላልቀን ምድሪቱ ኦናና በደም የታጠበች የወደመች ሀገር ለማድረግ ይህን ያክል ከባድም አይደለም። የአለመቀባበል ፍጻሜው ግልጽ እንደሆነ ሁሉ መንገዱም ቀላል ነውና።

አንድነት ለራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለሀገር ከዚህም አልፎ ለአህጉራዊ ለውጥና ልማት መሰረት ነው። ሰላም የሌለው ቤተሰብ ጤናማ ማህበረሰብ ሊያፈራ እንደማይችል ሁሉ እርስበርስዋ የምትለያይና የምትከፋፈል መንግሥትም እንዲሁ ናት። አሁን ባለው ነባራዊ የሀገራችን “የተወሳሰበ” የሚመስል ሁኔታ ይባስ ወደከፋ አዘቅትና ስብራት ከመሸጋገሩ በፊት ምድሪቱም ሆነ ትውልዱ ለማትረፍና ለመታደግ ከተፈለገ እያንዳንዱ ዜጋ ከእንቅልፉ ነቅቶ የድርሻውን የሚወጣበት ሰዓት አሁን ነው። ጆሮ ያለው ያድምጥ አስተዋይ ልቡና ያለውም ልብ ይበል! ሀገር ስለ አንድነት የሚጮክ፣ ስለ ሰላም የሚቆም፣ ከጥላቻና መራራነት የጸዳ መሪ ትሻለች! በተረፈ ግን

  • መቻቻል አቅቶን መናቆር ምርጫ ካደረግን: 
  • መደማመጥ ተስኖን መጠቋቀም ከመረጥን:
  • ሰላምን የሚያወርድ ቃል በመናገር/በመጻፍም ፈንታ እንደ ዘማ አንድ ወገን ላይ ያነጣጠረ አሽሙርና ሽምጠጣ ከተያያዝነው፡
  • ሰላምን እንደሚሻ የፍቅር ሰው ማሰብና መመላለስ አቅቶን እንደባልቴት አሮጌ ፋይል እያገለባበጥን ያለፈውን የሰዎች ስህተትና ነውር ማውሳትና ማነብነብ ከተያያዝነው፡
  • እንደ ግለሰብ ለፍቅር እንደ ሕዝብ ለሰላም የሚሸነፍ ልብ ከሌለን: 
  • ልዩነት ሊያስከትለው የሚችለው የተገለጠ አደጋ አልታይ ካለን: 
  • እንደ የአንዲት ሀገር ልጆች በሰላምና በፍቅር መግባትና መውጣት ኋላቀርነት ሆኖ እንደ ጅብ በጎሪጥ መተያየት ደግሞ ሥልጣኔ ሆኖ ከታየንና ከተሰማን: 
  • ፖለቲካዊም ሆነ ግላዊ የአስተሳሰብ ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይተንና ተነጋግረን ለመፍታት ከመትጋት ይልቅ ትንኝዋን ስህተት (ለራሳችን ስላልተመቸን ብቻ) ለማጉላት እንቅልፍ የምናጣ ከሆነ፤ 
  • ያበጠ ይፈንዳ! በማለት ሳይሆን ደም መፋሰሱን ቀርቶ በፍቅር ለምን ለአሥርም ሆነ ለአሥራ አራት ከዚያም ለሚበልጥ ቁጥር ተበጣጥሰን የየራሳችን መንግሥት መስርተን ለማየት የምንመኘውን ዓይነት ኑሮ ለመኖር አንሞክረውም? አይመስሎትም ክቡር? በመለያየትና በመበጣጠስ የሚገኝ ጥቅም ካለ ለምን ቀዳሚ ተጠቃሚዎች አንሆንም? አንድ ከመሆናችን የተነሳ ድህነት ከሚነግስብን ችጋርና ርሃብም መታወቂያችን ከሚሆኑ ለምን ተላያይተንም ሆነ ተበጣጥሰን ዕድገትን ማስመዝገብ ከተቻለን ምነውሳ ዘገየን? 

ምንም እንኳ በነገድ፣ በቋንቋ፣ በወግ፣ በሥርዓትና በልማድ ብዙሐን ብንሆን በአስተሳሰብ አንድ መሆን አቅቶን ተከባብረን፣ ተጠባብቀን፣ ተፈቃቅረን፣ ተስማምተን/ተደማምጠንና ተግባብተን ኑሮአችን ማሻሻል ሀገራችንም ከምትገኝበት አስከፊ ገጽታ መታደግ ካልተቻለንና ከተሳነን፣ በጥላቻ ፈንታ ፍቅርን የሚናገር፣ በመለያየት ፈንታ አንድነትን የሚሰብክ፣ በጎጠኝነት ፈንታ ኢትዮጵያዊነት የሚታይበት፣ በኃይል በጠመንጃ በግርግር በትርምስና በሁከት ፈንታ ሰላማዊ በሆነ ቅብብል ላይ የሚያምን ሰላማዊ ልብ ያለው መሪ ከታጣ፤ አባቶቻችን እንዳወረሱን እንደ ኢትዮጵያን አንድ ልብ ሆነን እጅ ለእጅ ተያይዘን ልማት፣ ሰላምና ብልጽግና ማምጣት ካልሆነል ለምን ተበጣጥሰን አንሞክረውም? ተለያይተንና ተበጣጥሰን የጽድቅ ጸሐይ ለማውጣት ከተቻለን (አይሆንም እንጅ) ለምን ተበታትነን ኑሮ አንፈትነውም?

ልዩነቶቻችን አምነን በመቀበል ለአንዲት ሀገር “ከአንዲት ባንዴራ” ስር ተጠለን ራሳችንን ለለውጥ መነሳት ካልተቻለንና አንድ በመሆን የሚገኘውን ትርፍና የሚመጣውን ሰላም ካልታየንና ከቀለለን፤ አንድ ሆነን ያቃተንን በተናጠል ለማስመዝገብ ከተቻለን የሚፈለገውም ሰላም፣ ብልጽግና፣ ልማት፣ ፍትህ፣ ነጻነት፣ ዲሞክራሲና ሌሎች እንደ ጠራናቸውና እንደ ጻፍናቸው ያደከሙን የራሳችን ለማድረግ እስከ ሆነ ድርስ መላላጡ ጉበዝ ተነስና ተለያይተን እንሞክረው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

yetdgnayalehe@gmail.com

Advertisements