አዝማሪውም አለ …

ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትም ሆነ ሕብረት አንድ ወገን ስለ ፈለገና ስለተመኘ ብቻ የሚመጣ የምኞት ፍሬ ሳይሆን ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትም ሆነ ሕብረት እውን ሊሆን የሚችለው በሚፈጠሩ አለመግባባቶች እያንዳንዱ ዜጋ እንደ ዜጋ ለመፍትሔ በሚያበረክተው ድርሻና አስተዋጽዖ፤ በሚያሳየው መልካም ፍላጎትና በጎ ተነሳሽነት የሚገኝ ፍሬ ለመሆኑ በብዙዎቻችን ዘንድ መዘንጋቱ  ምንም አያጠያይቅም። የሰሙኑ የአርቲስት አሉባይ በየነ ርካሽና አፍራሽ ተልዕኮ በእስራኤል ይህን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሁነኛ ምሳሌ ነው።

የሥነ ባህሪ ተማራማሪዎች እንደሚሉት በራስ መተማመን የሌለው፣ ያለ አቅሙ የሚንጠራራ ጎደሎ ሰው ከዕለት ዕለት ድርጊቶቹ የተነሳ በግለ ህይወቱ ሁልጊዜ የበታችነት ስሜት እንደሚሰማው፣ እንደሚረበሽና ሰላሙ እንደሚያጣ ከዚህም አልፎ በግላጭ የሚያሳየው ጸባይና የሚስተዋልበት አቋም ሲገልጹ ግልሰቡ ውጋት በሆነበትና በሚያሸብሩት ሁኔታዎች ራሱን እያስቀመጠ የሌለውን እንዳለው በመቁጠርም ራሱን ለማጽናናት ስብእናውን የመካብና ከፍከፍ የማድረግ አባዜ እንደሚታይበት ይገልጻሉ። ይህን የሚደርገውም ይላሉ ሊቃውንቱ በሽተኛው ከገጠመው የማንነት ቀውስ ራሱን ሊያረጋጋና እፎይታ ሊሰማው የሚችለው ይህን ሲያደርግ እንደሆነ ሆኖ ስለሚሰማው ነው ይላሉ። ስለሆነም የማንነት ቀውስ ያላቸው ሰለባዎች በእነዚህና ሌሎች ምልክቶች ተለይተው እንደሚታወቁም ይጠቁማሉ።

አርቲስት አሉባይ በየነ “ያ አዝማሪ ደግሞ ምን አለ?” በማለት የሚፈሩኝ አሉ ይላል የየዋኅን ዜጎች ኪስ ለመቦርቦር ወደ እስራኤል ባደረገው ጉዞ። እርግጥ ማንንም ወክዬ የመናገር ድፍረቱ ባይኖረኝም በበኩሌ ግን ይህ ግለሰብ የሚፈራ ሰው ገና አልተወለደም ባይ ነኝ። ይህን በተመለከተ ሦስት ነጥቦችን በማስቀመጥ ወደ ርዕሰ ጉዳዬ አልፋለሁ።

አንደኛ፡ ፍርድን ወደ ሐሞት የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት የምትለውጥ ተለላ ዓይነት ሰው በመሆንህ እንጅ እኔ እንኳ “አዝማሪው አሉባይ ምን አለ?” ብዬ አንተን የምከታተልበት ምክንያት የለኝም። ሃያ ዓመት ሙሉ የተቀመጥክባት ምድር እኔ አልተጠቀምኩባትምና ሌላውም እንደ እኔ የመንደር አውራ ደሮ ነው ብለህ የምታስብ ከሆነ ደግሞ በእውነቱ ነገር ትልቅ ስህተት  ነው።

ሁለተኛ፡ ነጻ መደረክ ቢኖርና አንተን ፊት ለፊት የማናግርበት ዕድል ቢፈጠር ምንም የሃያና የሣላሳ ዓመት የዕድሜ ልዩነት ቢኖረንም ሰው ዓይኑ እያየ አጥቤ ላሰጣህ እንደምችል ስለማውቅ በድርጊትህ ምንም ስጋት ያለኝ ሰው አይደለሁም።

ሦስተኛ፡ የጭብጨባ ብዛት የአንተ እውነተኝነትን እንደማያረጋግጥ ደግሞ በዚህ አጋጣሚ ላረዳህ እወዳለሁ። ጭብጨባ ለጭብጨባውማ በርባንም የአንድ ከተማ ሕዝብ ወጥቶ አጨብጭቦለታል። ለመሆኑ በርባን ማን እንደሆነ ታውቃለህ? በርባን ማለት ሁከተኛ፣ አመጸኛ፣ አዋኪ፣ ዘራፊ፣ ወንበዴ፣ ነፍሰ ገዳይ ሰው ነበር። የከተማው ሕዝብ ግን አምላኬ ነው ከምትለው ከኢየሱስ ይልቅ ይህ ነፍሰ ገዳይ ሰው ይወድ ነበር። ጥበብ በጎዳና ላይ ትጮሃለች!

ቃለ አዝማሪው፡

“ምን ሁነን ነው ገና እዚያ ጋ ሰዎች ቡና እየጠጡ “ቧዕ” ካሉ “እኔ አይደለሁም! (3)” [55: 36]

“ኢትዮጵያ ውስጥ በነጻነት ከጥቂቶቹ በስተቀር ሌላው እኩል ነው። ፈሪ ነው። ከኤርፖርት ጀምራችሁ አሳይመንት ልስጣችሁ ለቫኬሽን ስትሄዱ ቼክ አድርጉ እንደ ልባችሁ አታወሩም። ለምን? እዚህ ኤርፖርት ለምሳሌ ‘ዓተ’ ምናምን አይላችሁም ልክ እዛ ‘ዓ’ ሲላችሁ አሃ ረስቼ እሺ ነው የምትሉ።” [59: 50] ሙሉ የንግግሩ ይዘት ለማድመጥ ቀጥሎ የተቀመጠውን ሊንክ ይጫኑ [http://www.youtube.com/watch?v=vAYdPwGEnTM#t=3170]

ጠቅለል ባለ መልኩ፥

ጸሐፊው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና አንድነት መስፈን ካላቸው ሙሉ ፍቅር የተነሳ፤ ተልዕካቸውም ዜጎች እርስ በርስ መዋደድ መጠባበቅና መፋቀርን ይለማመዱ ዘንድ እውነትና ጽድቅን በፍቅር መናገር፣ ማስተማር፣ መጻፍና ማወጅ እንደመሆኑ መጠን ከላይ ከፍ ሲል የምናነበውን የስንፍና ቃል በሰፊው ከመተርተር ከማተትና ከመተርጎም ተቆጥበዋል።  ቢሆንም ግን መጽሐፍ “የሰነፍ አፍ ለራሱ ጥፋት ነው፥ ከንፈሩም ለነፍሱ ወጥመድ ነው” እንዲል

አንደኛ፡ “ኢትዮጵያ” ተብላ በምትታወቅ አገር ገዢና ተገዢ ሁለት አማርኛና ትግራኛ ተናጋሪ ሕዝቦች እንዳሉ። በብሔር መጠሪያ ስም ያቀመጥነው እንደሆነ ትግሬ የሚባል ገዢ ሕዝብና አማራ የሚባል ተገዥ ሕዝብ እንዳሉ መታወቁ።

ሁለት፡ ሁላችን እንደ ምናውቀው “ቧዕ” ብሎ ትግርኛ እንጅ “ቧዕ” ብሎ ጋሞኛ እንደሌለ ሁሉ የዚህ ቋንቋ ባለቤት/ተናጋሪ ሕዝብ ‘ኢትዮጵያዊ’ ተብሎ የሚታወቀው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ ጠላት እንደሆነ።

ሦስት፡ እንደ አዝማሪው እምነትና ቅስቀሳ እንዲሎከስ የሚፈለገው ጦርነትና እንዲነድ የተፈለገው እሳት በአዝማሪው አንደበት ፈሪ ተብሎ የተገለጸው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብና  “ቧዕ፣ ዓተ፣ ዓ” የመሳሰሉ ቋንቋዎች ተለይቶ የሚታወቀው የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ሕዝብ መካከል እንደሆነ ነው።

በግሌ በአዝማሪው አጠቃላይ እምነት ሆነ አንድን ሕዝብ እንደ ጠላት ፈርጆ እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ሰብስቦ ያደረገውን የቅስቀሳ ንግግር  ምንም ዓይነት ቅሬታ የለኝም። የትግራይ ሕዝብ የአማራ ጠላት ነው! የሚለው እምነቱም ያደርሰኛል ብሎ ያቀደው ቦታ እስኪያደርሰው ድረስ የመግፋት “መብት” አለው። ጥያቄው የትግራይ ሕዝብ አማራ በጠላትነት እንደሚያየውና አጋድሞ ሊያርደውም ቀን እየጠበቀለት እንዳለስ ያውቃል ወይ ነው? የትግራይ ሕዝብ በአጉል ሽንገላ “ኢትዮጵያዊ ነህ!” እየተባለ ራሱን ሳያዘጋጅና በሚገባም ሳይደራጅ ከየትኛው አቅጣጫ ለሚሰነዘርበት ጥቃትስ ተጠያቂው ማን ነው? ኢትዮጵያ ማለት ለአዝማሪው አማራ ሕዝብ ብቻ ነውና።

(አዝማሪ የሚለውን ቃል  አገልግሎት ላይ የዋለበት ምክንያት ግለሰቡ አዝማሪ ነኝ ሲል ራሱ በማስተዋወቁ ብቻ ነው።)

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Sep. 25, 2013

Advertisements