አገር እየመራ ያለው ኢህአዲግ እንጅ ህወሐት አይደለም!

ካለፈው የቀጠለ (ክፍል ሦስት – 3)

salsaywoyane

ህወሐት የደም ዋጋ የተከፈለበት የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ነው!” የሚለውን ክፍል አንድ ጽሑፍ የትግራይ ሕዝብ ምንነትና ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም “መስማት የማይፈልጉት የህወሐት ታሪክ!” በሚል ርዕስ ህወሐት ማለት የትግራይ ሕዝብ የታሪክ አሸራ እንደሆነ የቀረበ ክፍል ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች ልብ ብለው ተከታትለውኝ እንደሆነ በዛሬው ዕለት “አገር እየመራ ያለው ኢህአዲግ እንጅ ህወሐት አይደለም!” በሚል ርዕስ የምንዳስሰው ሦስተኛና የመጨረሻ ጽሑፍ ለማስተላለፍ በተፈለገው መልዕክት በሚገባ እንግባባለን የሚል እመነት አለኝ።

ልዩ ማሳሰቢያ፥

በክፍል ሁለት ጽሑፌ የትግራይ ህዝብ እወክላለሁ የሚለው በተለምዶ “ህወሐት” በመባል የሚታወቀው አንጃ የትግራይ ህዝብ እንደማይወክልና “ህወሐት” ተብሎም መጠራት እንደማይገባው ከሆነም መሰሪ ግብራቸው የሚገልጽና ፍንተው አድርጎ የሚያሳይ ትክክለኛ መጠሪያ ስም እስከምናገኝላቸው ድረስ በጊዜያዊነት “የትግርኛ ቋንቋ” ተናጋሪዎች ባለ ስልጣናት ተብለው ተለይተው መታወቅ እንደሚገባ “ጥብቅ ማሳሰቢያ” በሚል ንኡስ ርዕስ ሥር አጽንዖት ሰጥቼ አስተዋውቄ ነበር። ሆነም ግን ከዛሬ ዕለት ጀምሮ “የትግርኛ ቋንቋ” ተናጋሪዎች ባለ ስልጣናት የሚለው አጠቃቀም ሙሉ በሙሉ ተሰርዞ  አንጃው “ህዝባዊ ወያነ ባርነት ትግራይ በአህጽሮተ ቃል ህወባት” ተብሎ ይታወቅና ይጠራ ዘንድ ስጠይቅ በታላቅ አክብሮት ነው።

ሐተታ፥

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተወሳ ቁጥር በትረ ሥልጣኑን የጨበጠ አካል ለመግለጽ ሆነ ኢህአዴግ ብልው ለመጥራት የሚቸገሩ ወገኖች ጥቂቶች አይደሉም። ኢህአዴግ በማለት ፈንታም “ህወሐት” ብለው መጥራት የሚቀናቸው ወገኖች አሁንም በቁጥር ለማስቀመጥ ባያመችም ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ተቃዋሚ ነኝ የሚል ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት በማወቅም ባለማወቅ ቋንቋውን በማስተጋባት ተለይተው ይታወቃሉ። ይህ የሆነበት ምክንያትና ምሥጢሩም በክፍል ሁለት ጽሑፌ ግልጽ በሆነ ቋንቋ መነጋገራችን ይታወሳል። በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ኃይሎች አከባቢ የኢትዮጵያ መንግሥት “ህወሐት” ብሎ መጥራት ተአማኝነት የማስገኘቱ ያክል መንግሥት ትክክለኛና መሆንም ባለበት ኢህአዴግ ብሎ መጥራት ደግሞ በአንጻሩ በገዛ ፍቃድህ ከካምኙ የማሰናበት ያክል ነው። እውነት ግን አገር እየገዛ ያለው ማን ነው? ህወባት ወይስ ኢህአዴግ?

ኢህአዴግ የአራት የተለያዩ ክልላዊ መዋቅር ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ማለትም ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድና ህወባት ግንባር መሆኑን ይታወቃል። ከእነዚህ ክልላዊ ውክልና ያላቸው ድርጅቶች መሃከልም በምድሪቱ ተከሰተ ለሚባለው አሉታዊ ተጽእኖ ሁሉ ቀዳሚና ተከታይ በሌለው ሁኔታ ተነጥሎ ሲከሰስና “ዕድሜህ ይጠር!” እየተባለ ሲረገም የምንሰማው የትግራይ ክልል ይወክላል የሚባለው ትግራይን እያወደመና እያደቀቀ የሚገኘው ህወባት ብቻ ነው። በነገራችን ላይ ከዚህ ክስ ጀርባ ያሉ አካልት በሦስት መልኩ ከፍለን ማየት እንችላለን ይኸውም፥

አንድ፡ በእጃቸው የንጽሐን ደም ያላቸው ከፍርድ ያማለጡ የደርግ ባለ ሥልጣናት፣ ካድሬዎችና ወታደር ነበር  (ለምሳሌ ኢሳት)።

ሁለት፥ “ትግራይ ሳትደማ ኤርትራ አትለማም!” ብሎ የሚያምንና ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ትግራይን  ለመውጋትና ለማዳከም ብሎም ለማውደም የሌሊት ዕንቅልፍ ያጣ የአስመራ መንግሥት ተላላኪዎችና  መልዕክተኞች (ለምሳሌ ግንቦት 7)።

ሦስት፥ አለቦታው የሚቀመጥ ጠማማ ሰው ሲያብብና ወደ ፊት ገፍቶ ሲመጣ “ፖለቲካ” ብዙሐኑን ማታለያና ማደናገርያ ሁነኛ መሳሪያ ስለሚሆን ከቋንቋው ጀርባ ያለው መርዛማ ፖለቲካ በቅጡ ሳይረዱና በውል ሳይገነዘቡ ስለ ተባለ ብቻ የሚያስተጋቡ ንጹሐን ዜጎች ይጨምራል። ይህ ክፍል ብዙ ጊዜ በጎሳ ፖለቲካ የተጠቁና የተጠለፉ ያቀፈ ነው። ለምሳሌ ያክል “በኢትዮጵያ ፖለቲካ “ህወሐት” ተጠይቂ ማድረገና ኢትዮጵያ “በህወሐት” ብቸኛ የበላይነት የምትገዛ አገር ናት!” የሚለውን ምክንያታዊ ያልሆነ ደመ ነፍሳዊ እምነት የወሰድን እንደሆነ “ህወሐት” ከሚለው ቋንቋ ጀርባ መልዕክቱ በዋናነት የሚያነጣጥረውና ኢላማ የሚያደርገውም የትግራይ ሕዝብ መሆኑን የተረዳ አንድ ሰው አባባሉን አይጋራም። አይጋራም ብቻ ሳይሆን የአባባሉ አመንጪዎች በመቃወም ድምጹ እንደሚያሰማና ለኢትዮጵያ አንድነት እንደሚቆምም አልጠራጠርም።

ያም ሆነ ይህ “አገር እየገዛ ያለው ማን ነው?” ለሚለው ጥያቄ የሀገሪትዋ ችግር በሚገባ በማጤን ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ለማምጣት የሚታገሉ ዜጎች/ወገኖች አቋምና እምነት የሚከተለውን ይመስላል።

 • በኢትዮጵያ ውስጥ “መልካም አስተዳደር የለም” ከተባለ ለዚህ ተጠያቂ ኢህአዴግ ነው። 
 • በኢትዮጵያ ውስጥ “ሙስና አለ” ከተባለ ለዚህ  ጋጠ ወጥ ድርጊት ተጠያቂ ኢህአዴግ ነው።
 • ኢትዮጵያ “በጸረ ኢትዮጵያ ኃይሎች እየተገዛች ነው” ከተባለ አሁንም ይህ ጸረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ኃይል አንድና ሁለት በሌለው ሁኔታ ኢህአዲግ ነው።
 • “የሀገር ጠላት አለ” ተብሎ የሚታመን ከሆነና ካለም ይህ ጠላት የብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድና ህወባት ድምር ውጤት ወይም ግንባር የሆነ ኢህአዴግ ነው። 
 • የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ መስተዳደር የማይዋጥለትና መዋቅሩም ስህተትም ነው ብሎ የሚያምን አካል ካለ አሁንም ይህን ያደረገ ኢህአዴግ ነው። 
 • የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን ተቆርሶ ተሰጠ ብሎ እሪ የሚል ካለ “ወንጀሉን” የፈጸመ ኢህአዴግ ነው።
 • የኢትዮጵያ መሬት ለባለ ለውጭ ዜጎች (ባለ ሃብቶች) እየተቸበቸበ ነው የሚል ካለ ይህን ያደረገና እያደረገ ያለ በዚህ ድርጊትም ተጠቃሚ እየሆነ ያለ አሁንም ሌላ ማንም ሳይሆን ኢህአዴግ ነው።
 • ዜጎችን ከቦታ ወደ ቦታ ተፈናቀሉ ብሎ ህመም የሚሰማው ካለ  ይህን ያደረገ ኢህአዴግ ነው።
 • እንዲሁም ሌሎች ዓበይት የኢትዮጵያ መንግሥት ርዕሰ ኃጢአቶች ተብለው የሚጠቀሱ ሁሉ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድና ህወባት እኩል ተጠያቂዎች ናቸው። በሌላ አነጋገር በምድሪትቱ እየተፈጸ ላለ ወንጀል ኢህአዴግ ኃላፊነቱን ይወስዳል። ይህ ማለት የብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደህዴድና ህወባት ባለ ሥልጣናት ማለት ነው።

መሬት ላይ ያለው ሐቅ ይህ ሆኖ ሳለ ግን ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ይህ ሁሉ ኃጢአት ተሸክሞ የምናገኘው የግንባሩ አባል የሆነ አንድ ድርጅት ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያትም የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ ለመሆኑ ጭብጥ ላይ የተመሰረተ ነገር ኖሮ ሳይሆን ድርጅቱ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ክልል በላቀ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ኃይል ነው ተብሎ ስለሚታለም ነው። በእውነቱ ነገር የትግራይ ሕዝብ እንደሚጮኸው ህወባት አንጃ በተለየ መልኩ ተጠቃሚ የሆነ ሕዝብ ነውን?

ጆሮ ያለው ያድምጥ አስተዋይ ልቡና ያለውም ልብ ይበል!

 • አሁንም በኢትዮጵያ ምድር “ግፍ አለ!” ከተባለ የትግራይ ሕዝብ ከየትኛው ክልል ይልቅ በከፋ መልኩ እየተገፋ፣ እየተረገጠና በግፍ ብዛት እየተሸበረ ያለ ሕዝብ ነው።
 • በኢትዮጵያ ምድር “ፍትህ የለም!” ከተባለ የትግራይ ሕዝብም እኩል በፍትህ መጓደል እየተስተጓገለ ቁም ስቅሉ እያየ ያለ ሕዝብ ነው።
 • በኢትዮጵያ ምድር “ነጻነት የለም!” ከተባለ የትግራይ ሕዝብም እንዲሁ በነጻነት እጦት አንገቱ ደፍቶ እየተናጠ፣ መከራውን እያየና እያለቀሰ ያለ ሕዝብ ነው።
 • በኢትዮጵያ ምድር “ዲሞክራሲ የለም!” ከተባለ በትግራይ ክልል ተወላጆች መካከልም እንዲህ ሁኔታው የከፋ ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ኤፍ ኤም የሬድዮ ጣቢያ የሌለው ክልል የትግራይ ክልል ብቻ ነው።
 • ለመሆኑ የትግራይ ህዝብ ምኑ ነው ያደገ? የተለወጠው? የዕድገት መለኪያ ምን ቢሆን ነው? የትግራይ ህዝብ ከተቀረው ክልል ይልቅ በላቀ መልኩ ተጠቃሚ ነው ተብሎ ፕሮፖጋንዳ የሚነፋው? አንድን ሕዝብ ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ተጠቃሚ ሆነዋል ለማለት ምን የተለየ ነገር በትግራይ ክልል ቢኖር ነው?

እንግድያውስ ሐቁ የትግራይ ሕዝብ በህወባት ደቀቀ እንጅ አልተጠቀመም የማይገልጸው የተንኮታኮተ ሕዝብ ነው። በአጭር ቋንቋ የህዝባዊ ወያነ ባርነት ትግራይ ልሂቃን ለኤርትራ የበላይነት ለትግራይ ሕዝብ ባርነት፣ ውርደት፣ ድቀትና ውድቀት “የታገሉ” መሰሪዎች ናቸው። የትግራይ ሕዝብ በህዝባዊ ወያነ ባርነት ትግራይ አይደለም ተጠቃሚ ሊሆን “አይደለም ጠግቦ ተርቦም አልተቻለም” እየተባለ እየተረገጠ ያለ ሕዝብ ነው። ይልቁንስ በኢትዮጵያ ምድር እየተጠቀመ ያለ ሕዝብ አገራቸው ሲዖል የሆነችባቸው ኤርትራውያን ናቸው። ሁላችን እንደምናውቀው ኤርትራ ለኤርትራውያን እንደ አዳኝ ስታሳድዳቸው ኢትዮጵያ ማለት ግን ለኤርትራውያን ንጽህ አየር የሚተነፍሱባት ገነት ናት። ኤርትራውያን በሱዳን፣ ግብጽ፣ ሲና፣ ሊብያ፣ በኬንያናና ኡጋንዳ የሚገጥማቸው ሕይወትና የሚደርስባቸው አሰቃቂ ግፍና በደል ዓለም የሚያወቀው ሐቅ ነው። የኤርትራውያን ሕይወት በምድራችን የተመለከትን እንደሆነ ግን፥

 • የትግራይ ገበሬ በሃይል ተገዶ የወሰደው መዳበሪያ ዕዳው አልከፈልክም እየተባለ የቤቱ ቆርቆሮ እየተነቀለ ቤት አልባ ሲደረግ መንግሥት ኤርትራውያን ወታደሮች በኢኮኖሚ ለሟቋቋም ተጠምደዋል።
 • የትግራይ ሕዝብ አንዲት ሊትር ዘይትና አስር ኪሎ ስንዴ ለማግኘት በቀንም በሌሊትም ተራራ ሲያስቆፍሩት የኢትዮጵያ ባንኮች ለኤርትራውያን ከልዩ መስተግዶ ጋር ክፍት ናቸው።
 • የመንግስት ኢ-ፍትሐዊ አስተዳደር የሚቃወሙ የትግራይ ተወላጆች ከየተቋማቱ እየተለቀሙ ወደ ውህኒ ሲወረወሩ የምድሪቱ ከፍተኛ ተቋማት በአቶ ኢሳይያስ  ወታደሮች እየተጣበቡ ይገኛሉ።
 • የትግራይ ሕዝብ የሚላስ የሚቀመስ ከማጣቱ የተነሳ ለልመና ወደ መኸል አገር ሲፈልስ አስመራውያን የትግራይ ከተሞች ገበያ እየተቆጣጠሩ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ  ንብረትነቱ የህዝባዊ ወያነ ባርነት ትግራይ የሆነው ኢፈርት እንዲህ ላለ ቀን ኤርትራ ለመደጎም ታስቦ የተቋቋመ እንደሆነስ ማን ያውቃል?

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Sep. 24, 2013

Advertisements