ኢትዮጵያ፡ ጨወታ ለማሳመር የምትመዘዝ ጆከር ናት!

የኢሳት የዕለተ ዕለት ፕሮፖጋንዳ፣ የግንቦት 7 ሊሂቃን ቃለ ምልልስ፣ በቅርቡ ደግሞ የኤርትራ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መባቻ ምክንያት በማድረግ ከኤርትራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያ አስመልክተው ያንጸባረቁት ጎደሎ አመለካከት ተከትሎ ሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት “በሀገር ክህደትና በጸረ ኢትዮጵያዊነት” በመክሰስ የሚታወቁ ኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጋዜጣዊ መግለጫ በመቃወም አንዳች ያሉት ነገር አለመኖሩን ተደማምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ ምን እየሆነ እንዳለና በተለይ “ኢትዮጵያ ማን ናት? ኢትዮጵያዊስ ማን ነው?” የሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጣቸው “ኢትዮጵያ ሀገሬ! ኢትዮጵያ እናቴ! .. ወዘተ” ተብሎ የሚጮኸው ጭሆት ከዘፈንና ከመፎክር ያለፈ ፋይዳ እንደማኖረው ለአፋታም ልንጠራጠር አይገባም። 

“ሀገሬ፣ እናቴ፣ ኢትዮጵዬ ዬዬ ምን ልሁንልሽ?! … ብቀነጠስልሽ!፣ … ብንፏቀቅልሽ!፣ … ብከርበትልሽ! ያንስብሻል!! አንቺ ማለት እኮ ለእኔ ክብሬ ነሽ! … ዘራፍ! ዘራፍ! … ኧረ ስንቱን ዘርዝሬ አዘልቀዋለሁ በአጭሩ ግን ይህ ሁሉ መመጻደቅ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ዓይናችን እያየ ጉድጓድ መቆፈር ሳያስፈልጋቸው በተቆፈረ ጉድጓድ ቀብረውታል። እኔ ግን ሳስበውና ሳሰላስለው የአቶ ኢሳይያስ ማያዢያ መቋጠሪያ የሌለው አባባል ሳይሆን “ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!” እየተባለ ከውስጥም ከውጭም በታላቅ ድምጽ ከሚጮኸው ጭሆት ጀርባ ያለው እጅን በአፍ የሚያስጭን ፖለቲካ አሳስቦኛል።

ለመሆኑ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በጠራራ ጸሐይ ሀገር ሲያዋርዱና ሕዝቦችዋም ሲዘልፉ “ኢትዮጵያዊነትን የሚጠይቅ ሁሉ በአማራነት ነው የሚወነጀለው” በማለት በሕዝቦች መካከል እሳት የሚያነዱና መርዝ የሚረጩ አጨብጫቢዎች ለምን ዝምታን መርጡ ሲሉ ለራስዎ ጠይቀው ያውቃሉ? ጠይቀው እንደሆነ ከእኔ ጋር መስማማትዎ አይቀርም። ጨርሰው ያላሰቡበት እንደሆነ ግን ራሳቸውን ከመጠየቅ ያልቦዘኑ ዜጎች በጋራ የደረስንበት እንደሚከተለው አካፍሎት ዘንድ ወደድኩ።

በእውነቱ ነገር “ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!” እያለ የሚጮህ ሁሉ በሀገር ፍቅር የነደደ “ንጹህ” ኢትዮጵያዊ፣ ሀገር ወዳድ ዜጋ ነው ብለው የሚያምኑ/የሚያስቡ ከሆነ የዋህ ኖት። ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅር መግለጹም ሳይሆን ከዚህ ጭሆት ጀርባ ያለው ትርፍ ያሰላ ልዩ ተልዕኮና አጀንዳ ያለው ሰው ነው ብሎ መጠርጠርም አይከፋም። ኢትዮጵያ፡  

 • መወጣጫ መሰላል፥
 • መሸጋገሪያ ድልድይ፥
 • ማደንዘዣ ዕጽ፥
 • ማታለያ ከረሜላ፥
 • ማጣፍጫ ቅመም፥
 • መደለያ ቋንቋ፥ 
 • ጨወታ ላማሳመርያ የምትመዘዝ ጆከር መሆንዋን የነቃሁም አሁን ቅርብ ጊዜ ነው። ያም ሆነ ይህ ከዚህ ሁሉ ጭኸት ጀርባ ያለው ፖለቲካ አንድና አንድ ነው። እርግጥ የሚያጓጓ መልካም ነገር ባይኖረውም “ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!” እየተባለ ከሚጮሆው ጭሆት ጀርባ ያለውን ድብቅ አጀንዳ ለማወቅ ግን ሳይጓጉ አይቀሩም። ከዚያ በፊት ግን ጸሐፊው ለምን ተብሎ ይዋሻል? ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ይጠቁማሉ።

ለምን ተብሎ ይዋሻል? ጎበዝ! ኢትዮጵያ ውስጥ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ አይደለም የሚፈለገው ያለ። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የፈጠረው/ይዞት የመጣ ችግርም አይደለም። አሁን ያለው ችግር ትናንት የነበረ ሥር የሰደደ ችግር ነው። ችግሩ በጠረጴዛ ዙሪያ ካልተፈታ ደግሞ የችግሩ ቀጣይነት እስከ ምጽአት ድረስ ይሆናል። አሁንም የኢትዮጵያ ችግር የኢህአዴግ ችግር ነው ብሎ የሚያምን ሰው ካለ የኢትዮጵያ ታሪክ የማያውቅ ሰው ብቻ ነው። ወረደም ወጣ፥

 • የኢትዮጵያ ችግር የዲሞክራሲ፣ የነጻነት፣ የህግ የበላይነት፣ የፍትሕ እጦት … ችግር ነው እየተባለ የሚነገርዎት ዓይነት ችግርም አይደለም።
 • የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የርዕዮተ ዓለም ችግር አይደለም።
 • የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ችግር አይደለም።
 • የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የማናቸውም በሚኒስትር ደረጃ የፖሊሲዎች ችግር አይደለም።
 • የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር “የእኔነት” ማለትም የበላይነት ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በዘመነ ፈሳፍንት የነበረው ጎሳ መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ድምጽ አልባ ጦርነት ነው እየተካሄደ ያለው። የፈለግነውን ብንለጣጥፍ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር በብሔር ብሔረሰቦች መከከል የበላይ የመሆን ጥያቄ ችግር ነው። እደግመዋለሁ ጥያቄው የዲሞክራሲ የምናምን የምናምን ገለ መሌ ጥያቄ አይደለም። ጥያቄው አጭርና ግልጽ ነው። ይኸውም፥ የጎሳ/የብሔር የበላይነት ጥያቄ ነው። አንዱ “አንቀጥቅጬ ስገዛ የኖርኩ እኔ ነኝ የበላይ!” ሲል ሌላው ደግሞ ተቀብሎ “የለም! ከእንግዲህ ወዲህ ስትጎርር ትኖራታለህ እንጅ አብቅቶልሃል!” “እስከ መቼ ነው … የምጠብቀው ኢኔም ይገባኛል!” የሚልም ሜዳው ተቀላቅለዋል ይህ ነው እንግዲህ ችግሩ። ልዩነቱ በጥንት ዘመን መሪዎቹ ደጃ ዝማች/ቀኝ አዝማች በመባል የሚታወቁ ሲሆን አሁን ደግሞ ዶክተር ፕሮፌሰር፣ አክቲቪስት ካታሊስት በሚል መጠሪያ ማዕረግ መለወጡ ብቻ ነው። በተረፈ ዶክቶሩም ፕሮፌሰሩም የሚስበውና የሚያሰላስለው የፖለቲካ አጀንዳ የጥንቶቹ ደጃ ዝማችና ቀኝ አዝማች አስተሳሰብና አመለካከት ነው። “ኢትዮጵያ ሀገሬ! ኢትዮጵያ እናቴ! ኢትዮጵያ … የሚሉ ፈሊጦች መጨመራቸውም ከቀድሞ ዘመን ለየት እንዲል አድርጎታል። ሦስተኛ ቀንድ መብቀሉም ሌላ ተጨማሪ ዕድገት ነው። በነገራችን ላይ ጸሐፊው አሁን ባለው ተጨባጭ የሀገሪትዋ ሁኔታ የአንድ ብሔር የበላይነት አለ ብለው አያምኑም። ይህን በተመለከተ በሚቀጥለው ስራቸው በስፋት ይዳስሱታል።

እንግዲያውስ ይህን የመሰለ አንድና አንድ፣ የሚታየውን ማየት ለሚፈልጉ ዓይኖችም ኩልል ብሎ የሚታይ፣ ያጎበጠን ችግር እያለ ነው የተለያዩ ቀለመት እየቀባባንና የተለያዩ ምክንያቶች እየሰጠን/እየደረደርን ነገሮች እያወሳሰብን ከድጡ ወደ ማጡ እየተንከባለልን የምንገኘው።

በመጨረሻ፥ ችግሮቻችን በግልጽ ለመናገር አቅም እስካልገነባን ድረስ እርስ በርሳችን መናቆናችን፣ መነታረካችን፣ መፋጀታችንና መቧቀሳችን ይቀጥላል። ውሎ አድሮ አንድ ቀን ደግሞ አሸናፊና ተሸናፊ በሌለበት ሁኔታ ደም መፋሰሳችንና መተላለቃችን የማይቀር ነው። ይህ ግብዝነት የተሞላበት ጩኸትና ተቃውሞ ደግሞ የሀገሩን ታሪክ የማያውቅ የሰጡትን በልቶና ጠጥቶ ከመተኛት ያለፈ ሌላ ዓለም ያለ የማይመስለው ምስኪን ዜጋ ያደናግር እንደሆነ እንጅ የሚፈጥረው ተአምር አይኖረውም።

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Sep. 21, 2013

Advertisements