መስማት የማይፈልጉት የህወሐት ታሪክ!

አንድን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ በጦርነት፣ በሁከትና ዜጎችን በማሸበር ሥልጣን ላይ ለመውጣት ከሀገራችን ታሪካዊ ጠላት ግንባር በመፍጠር እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መቀመጫው አውሮፓና አሜሪካ ያደርገ ግንቦት 7 በመባል የሚታወቀው ቡድን ልሳኑ በሆነው ኢሳት የዕለት ዕለት የፕሮፖጋንዳ ስርጭቱ ያለ ኃጢአቱ እየተከሰሰና እየተወነጀለ የሚገኝ የትግራይ ህዝብ ነባራዊ ሁኔታ “ህወሐት የደም ዋጋ የተከፈለበት የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ነው!” በሚል ክፍል አንድ ጽሑፍ መዳሰሳችን የሚታወስ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው ዕለት ደግሞ የትግራይ ሕዝብ የታሪክ አሻራ በሆነ ህወሐት በተመለከተ ጠቅለል ባለ መልኩ ሦስት ነጥቦች ላይ አተኩረን አንወያያለን።

Salsaywoyane

አንድ፡ በህወሐትና በትግራይ ሕዝብ መካከል ያለው የማይሰበር፣ የማይነጣጠልና የማይለያይ ታሪካዊ ግኑኝነትና ቁርጭነት- በጥልቀት፤

ሁለት፡ ህወሐት ብሎ “የጨለማ ቁራጭ” ተደርጎ በሰፊው የሚሰራጨው ፕሮፖጋንዳ መንስኤውና ምሥጢሩ – በጥልቀት፤

ሦስት፡ በክፍል ሦስት በሰፊው የምንዳስሰው በህወሐትና “በትግርኛ ቋንቋ” ተናጋሪዎች ባለ ሥልጣናት መሃኸል ያለውን ገደል ወይም ልዩነት በመጠኑ እንመለከታለን።

ጥብቅ ማሳሰቢያ፥ “የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች” በማለት ለጊዜው አገልግሎት ላይ የዋለው ቃል በየደቂቃው ስም ዝርዝር ከማስቀመጥ አንጻር በጊዜያዊነት ጥቅም ላይ የዋለ እንጅ ትክክለኛ/ተገቢ አገላለጽ አይደለም።

ሐተታ፥

ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ በአህጽሮተ ቃል ህወሐት መቼ ተመሰረተ? እንዴት? ለምን? ዓላማው ምንድ ነው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች አሁን መዘርዘሩ አስፈላጊ አይመስለኝም። አንድም ማወቅና መስማት የማይፈልግ ሰው ካልሆነ በስተቀር በጥላቻ መልክም ሆነ በሌላ “የህወሐት” ታሪክ ሳይሰማ የቀረ ወይም የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት ስለ ማልደፍር  በቀጥታ ወደ ፍሬ ነገሬ አልፋለሁ።

ህወሐት ማን ነው/ምንድ ነው? 

  • ህወሐት እነዚህ አሁን የምናውቃቸው በጣት የሚቆጠሩ ምቾት ያሰከራቸው፣ የደላቸውና የሰቡ ግለሰቦች የጽዋ ማህበር ሳይሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልጆች ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ መስዋዕትነት የከፈሉበት የትግራይ ሕዝብ የታሪክ ማህደር ነው። 
  • ህወሐት የትግራይ ሕዝብ የልጆቹ ደም ገብሮ የመሰረተው የታሪክ አሻራ ነው። 
  • ህወሐት፡ የትግራይ ሕዝብ ለ17 ዓመታት እልህ አስጨራሽ የትግል ጉዞ ምዕራፍ ነው።
  • ህወሐት የትግራይ ሕዝብ ጨለማውን የገፈፈበት፣ እንደ ሕዝብ የቆመበትና መብቱን ያረጋገጠበት ኃይል ነው። 
  • ህወሐት የትግራይ ሕዝብ እየተደጋገፈ፣ ፈንጅ እየረገጠና አርማውን እየተቀባበለ አንባገነናዊ የደርግ መንግሥት ያስወገደበት መስመር ነው።
  • ህወሐት አለ የለም? ለሚለው ያልሰከነ ሙግት ህወሐት አክስዮን ማህበር አይደለም ከስሮ የሚዘጋው። ወደድንም ጠላንም ህወሐት የደም ዋጋ የተከፈለበት የትግራይ ሕዝብ “ነፍስ” ነው። 
  • “ህወሐት የለም!” ብሎ ማሰብም ሆነ መናገር በራሱ ህወሐት ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ በቂ መረዳትና ግንዛቤ የሌላቸው አንድም የትግራይ ሕዝብ ለነጻነቱ ባፈሰሰው ደም መጫወት የሚምራቸው ነፈዞች ቀልድ ነው። 
  • ህወሐትና የትግራይ ሕዝብ የአንዲት ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። የሚነጣጠል ታሪክና ሕዝብ የለምና።
  • ህወሐት በማናቸውም ሥልጣን ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ቅሌትና ግድፈት አይመዘንም። ጎራ ለይተው እየተቧቀሱ የሚገኙ የሰይጣን ወኪል አቦይ ስብሃት ሆኑ ትግርኛ ተናጋሪ ደርግ አባይ ወልዱ ህወሐትና የትግራይ ሕዝብ የከዱ  ወረበሎች እንጅ ግለሰቦቹ ህወሐትም ሆነ የትግራይ ሕዝብ አይወክሉም።
  • ህወሐት “ንብረትነቱ” የትግራይ ሕዝብ ነው። የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ አስካለ ድርሰም የህወሐት ታሪክ ይኖራል። 

ምሥጢሩ …! 

ህወሐት ስሙ በተነሳ ቁጥር ከምንም በላይ በጣም ጥቂት በጣት የሚቆጠሩ ጋጠወጥ “የትግርኛ ቋንቋ” ተናጋሪዎች ባለ ሥልጣናት እንድናስብና እንድናይ የሚያደርጉ ግለሰቦች ሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች በህወሐትና በአሁን ሰዓት በሥልጣን ላይ የሚገኙ “የትግርኛ ቋንቋ” ተናጋሪዎች ግለሰቦች ያለ መጠነ ሰፊ ልዩነት የማያውቁና ያልነቁ ሆነው ሳይሆን በዋናነት  እነዚህ ግልሰቦች ሆኑ የፖለቲካ ጅርጅቶች ይህን የሚያደርጉበትም ዋና ምክንያት ለትግራይ ሕዝብ ያላቸው ስር የሰደደ ጥላቻና የሕዝቡን ታሪክ የመደምሰስ ልዩ ተልዕኮ ክፍል ነው።

የትግራይ ሕዝብ ህወሐት የሚል ቃል በሰማ ቁጥር ራሱን እንዲያሸማቅቅ እየተሰራጨ ያለው ፕሮፖጋንዳና እየተካሄደ ያለው መርዛማ ዘመቻ ምሥጢሩ የትግራይ ሕዝብ ለአስራ ሰባት ዓመታት በደርግ ወታደራዊ አገዛዝ ሁለማናው ተገፎ በግፍ የተገዛበት፣ ይህን አሰቃቂና አረመንያዊ የአገዛዝ ሥርዓት እንቢ! በማለት ብረት አንስቶ ደርግን የተፋለመበት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ ያጣበት፣ የቆሰለበት፣ የሞተበት፣ ደሙንና አጥንቱን የከሰከሰበት የጀግንነት ታሪኩን መልስ ብሎ እንዳያይ፣ እንዳያስብ፣ እንዳያስታውስና እንዳይዘክር ሆነ ተብሎ ታስቦበት በስሌት የተደረገና እየተደረገም ያለ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ መቆም የማይዋጥላቸው ጎሳን መሰረት ያደረገ በሕዝቡ ላይ ስር የሰደደ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸው አካላት ፕሮፖጋንዳ ነው። 

ህወሐት “የጨለማ ቁራጭ” አድርገን ስለን ስናበቃ “የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችን ነው!” በማለት ህዝብ የምንሸነግልበትና የምናታልልበት ዘመን አብቅተዋል። ጥጉ፥ የትግራይ ሕዝብ እንደ ህዝብ የሚቀበል ግለሰብ ሆነ የፖለቲካ ድርጅት አንድ፡ የትግራይ ሕዝብ አርማ ህወሐት መቀበል የማይከብዳቸው ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የሚቀበል ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት “የትግርኛ ቋንቋ” ተናጋሪዎች ባለ ሥልጣት ንብረትነቱ የሕዝብ ከሆነ ከህወሐት ነጥለው ማየት አያቅተውም/ታቸውም። ምን ነው? ቢሉ ህወሐት ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው የትግራይ ሕዝብ ማለት ደግሞ ህወሐት ነው። የትግራይ ሕዝብ እንደ ህዝብ የማይቀበል፤ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ መቆምም ሆነ ህልውናው የሚያንገሸግሻቸው፣ የማይዋጥላቸውና ደም የሚያስቀምጣቸው በተመሳሳይ ህወሐትም ሆነ የህወሐት ታሪክ ይቀበላሉ ብሎ ማሰብ በራሱ ሲበዛ የዋህነት ነው። አይመስሎትም?

በዚህ አጋጣሚ በዙሪያው አንድ በጣም የሚገርመኝና የሚያሳዝነኝ በፖለቲካ የአመራር ቦታ ሳይቀር የተቀመጡ ራሳቸው እንደ “ፖለቲከኛ” የሚጠሩ ግለሰቦች ሳይቀሩ ከመጋረጃ በስተጀርባ ተቀምጠው ጨወታውን በሚጫወቱት  አጋፋሪዎች ተታለው የደም ዋጋ የተከፈለበት የሕዝብ ታሪክ ህወሐት ከግለሰቦች ልቅ ልምምድና ምግባረ ብልሹነት ነጥለው ማየት ተስኖአቸው የጠላት ቋንቋ ሲደግሙ፣ የተሳሳተ ትርጓሜና አንድምታ ሲያስተጋቡ ስመለከት የሚሰማኝ የልብ ሐዘን ጥልቅ ነው።

ይቀጥላል …

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Sep. 20, 2013

Advertisements