ኤርትራ፡ 52ኛዋ የአሜሪካ ጠቅላይ ግዛት!

አቶ አንዳርጋቸው ዘመኑ ከሚጠይቀው የፖለቲካ ዕውቀትና ብስለት ምን ያህል የራቁ በሰው ሳንባ የሚተነፍሱ ዛሬም “ጃንሆይ ይሙት!” ባይ ግለሰብ ለመሆናቸው፤ በተጨማሪም በመዘዙት ካርድ እምብዛም ያልተሳካላቸው አንደኛው እግራቸው ጉድጓድ ውስጥ እንደተቀረቀረባቸው በታላቅ ስቃይና የሞት ሽረት የህልውና ትግል የሚገኙ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በሚጫወቱት ጨወታ (ሐሸውዬ) ለራሳቸው ተሳስተው፣ ተሸውደው፣ ተደናግረውና ተበውዘው ሲያበቁ ሰው ለማሳሳትና ለማደናገር “መልዕክት አለኝ!” በማለት “ከአስመራ” ዲሲ (DC) ድረስ መጥተው በኢሳት ብቅ ያሉበት ሰሞን የኤርትራ ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም የፕሬዝዳንት ኢሳያያስ አፈወርቂ ሰብእና በተመለከተ የቀደዱት ቀደዳ ብዙዎቻችን ሳያስደምምና ሳያስደንቅ አልቀረም።  አቶ አንዳርጋቸው ስለ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፥ 

“ዛሬ ኤርትራ ውስጥ የትኛው አፍሪካ አገር ውስጥ የማታየው አለ። ከፊትና ከኋላው ሞተር ሳይክል እንኳን አጅቦት የማይሄድ ፕሬዝዳንት ያለበት አገር የማቀው እኔ ኤርትራ ነው።” አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚያርበደብዳቸው ነገር ምን እንደሆነ ባላውቅም (ሲዋሽ ነው! የሚል የሥነ ልቦና ሊቃውንት እምነት እንደተጠበቀ ሆኖ) ፈራ ተባ እያሉም “በኤርትራ በኩል የሚገኘውን ድጋፍ ጠቅላላ ስመለከተው አሁን በአሁኑ ሰዓት ላይ በአራትና በአምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ ሆኖ የሚደረግ ዓይነት ጦርነት ትግል አድርጌ ነው የማየው ያለው። የምትባላውን የምትጠጣውን ምን የምታደርገውን ለሰራዊት በሚገባ የሚለብሰውን ሌላ ቦታ ላይ እኮ ሻዕቢያ ትግል ስያደርግ ከምን እንደተነሳ እናውቃለን ኢቭን ወያኔ ራሱን ከምን እንደተነሳ እናውቃለን በዛ ደረጃ ድጋፍ የሚያገኙ ድርጅቶች ኢሀፓ በምን ደረጃ ይታገል እንደነበር እናውቃለን ከዛ ዘመን ጋር ብታወዳድረው ከኤርትራ መንግሥት የሚደረገው ድጋፍ እንደው የበዛ ነው ጭራሹ።” ይላሉ።

ተናጋሪው የፖለቲካ ጨወታ ለመጫወት አልቻሉበትም እንጅ ሲበዛ ቀልደኛ ናቸው። ለመሆኑ ሰው፥

  • እህል በኩባያ እየተሰፈረ የሚታደልባት፣ 
  • በዳቦ ፈንታ በሎህሳስ ዘፈን ተዘፍኖ የሚተኛባት፣ 
  • “የጤፍ” እንጀራ በህልም የሚበላባት፣ 
  • ዜጎችዋ ቁልቋል (በለስ) ለቀማ ቤት ገርግሽ ውሎ የሚያድሩባት፣
  • በሐዋላ ገንዘብ የቆመች፣
  • በኢኮኖሚ የደቀችና አልጋ ላይ የተጋደመች፣
  • ጊዜ እንደ ሰው የተማረረባት፣ 
  • በውሃና በመብራት እጥረት እየተናጠች የምትገኝ የደዌ ዳኛ የአልጋ ቁራኛ አገር ተይዞ እንዴት ነው አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ከተማ ወጥተው መንሸራሸርና አንድ ሁለት ማለት ባማራቸው ቁጥር ከፊትና ከኋላ በሞተር ሳይክል ታጅበው መሄድ የሚያምርባቸው? ኤርትራ ስንዴ ለማግኘት የተባበሩት መንግሥታት ደጅ እየጸናች በምትገኝበት አጣብቂኝ ሰዓት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ይህን ብያደርጉ የግፍ ግፍ አይሆንም ወይ? ወይንስ ሰውዬው ድፍን ዓለም የሚያውቃቸው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ መሆናቸው ቀርቶ ፕሬዝዳንት “ምን ተስኖት በምላሱ” በዘፈን የሚሄዱ መኪኖች አስመራ ውስጥ ማምረት ጀምረዋል ነው ጨወታው? በሰው ቁስል እንጨት መስደድ ይሉት ይህ ነው። ጎበዝ ከተማ ለሽርሽር በተወጣ ቁጥር ከፊትና ከኋላ በሞተር ሳይክል በምናምን ታጅበህ ለሜሄድም እኮ አቅርቦት ይጠይቃል። እንዴት? ሞተሮቹም ሆነ መኪናቹ በነዳጅ እንጅ “በዋርሳይ ይከአሎ” በዘፈን አይሄዱምና። ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የውሃ አቅርቦት የሌላት አገር ደግሞ በነዳጅ ብትጫወት ቀልድ አይሆንም ወይ? ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ?! አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይህ ሁሉ ሲለፍፉ “ምስራቃዊትዋ አፍሪካ ኤርትራ ናት ወይስ ሌላ ዓለም የማያውቃት 52ኛ የአሜሪካ ጠቅላይ ግዛት ኤርትራ ብትኖር ነው?” በማለት ራስዎን ካልጠየቁ ችግር አለ ማለት ነው።

እስቲ “እግዚሃር” ያሳያችሁ ሕዝቦችዋ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ ያለችው አገር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሰው አገር ሰዎች ሰብስባ ከባለ አምስቱ ኮከብ ከኢንተር ኮንቲነንታል ሆቴል ባልተናነሰ መልኩ ተንከባክባ ስትቀልብና ስታደልብ። ታየኝ እኮ! ኢትዮጵያ ውስጥ እንጀራ መብላት የሰለቸው ወጣት አፈር ለመብላት አፈር ላይ ለመተኛት ተሰብስቦ ወደ አስመራ ሲፈልስና በኢንተር ኮንቲነንታል ሆቴል ብላልኝ ጠጣልኝ እየተባለ ወጣቱም ጣመኝ ድገመኝ እያለ ሲቀለብ። ወይ አስመራ! ድሃ በአቅሙ በልቶ ጠጥቶ የሚያድርበት ሰማይ የተከፈተላት አገር እንዳልነበረች ዛሬ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲህ ይሳቁባት? እኔስ ምንም አልልም ቢሆንም ግን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምጸት የተሞላበት ንግግር የሰሙ በውስጥም በውጭም የሚኖሩ ኤርትራውያን ምን ይሉ ይሆን?

እውነቱ ለመናገር ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ከፊትና ከኋላ በሞተር ሳይክል ታጅበው መሄዱ ቀርቶባቸው “አንዷ” መኪናቸው ሽጠው የአንድ ከምግብ ዕጦት የተነሳ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ የሞት አፋፍ ላይ የሚገኝ ኤርትራዊ ዜጋ ነፍስ ቢያተርፉምስ ምን ይደንቃል? “ጥሮታ ብሎ ነገር የለም! ቢዋጥልህም ባይዋጥልህም በህይወት እስካለሁ ድረስ ኢሳይያስ የኤርትራ ፕሬዝዳንት ነው!” በማለት በአደባባይ መግለጫ የሰጡት እኮ ዜጎችን ለመታደግ ለመጠበቅና በአግባቡ ለማስተዳደር እንጅ ኤርትራውያን ለመበተን፣ ቁም ስቅሉን ለማሳየትና ለመግደል አይመስለኝም።

 ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Sep. 19, 2013

Advertisements