ህወሐት የደም ዋጋ የተከፈለበት የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ነው!

ከዚህ ቀደም በዚህ መልኩ ያስቀመጥኩት አይመስለኝም። እስከ ቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለራሴም ቢሆን አሁን የደረስኩበት በተለይ በዛሬው ዕለት “ህወሐት” እና “ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ባለ ሥልጣናት ግለሰቦች” በማለት በሁለት ለየቅል የሆኑ ጎራዎች በመክፈል በሁለቱም መካከል ያለው ትልቅ ገደልና መጠነ ሰፊ የሆነ ልዩነት የዳደበረ አመለካከት ወይም መረዳት አልነበረኝም። ሁኔታዎች አስገዳጅ እየሆኑ ከመምጣታቸው የተነሳ ግን በተለይ በኢሳት በኩል ሆነ ተብሎ አንድን ሕዝብ ያነጣጠረ የሚሰራጭ የፕሮፖጋንዳ ማለትም ሕዝብ እርስ በርሱ ለማላተምና ለማጋጨት በሕዝቦች መካከልም ግጭቶችን ለመቀስቀስ ታስቦ ትግራይ ተኮር ለሚናፈሰው መሰረተ ቢስ የጥላቻ ፖለቲካና በዚህ ዙሪያም አለ አግባብ የሚነገሩ ቃላቶች አጠቃቀማቸውና ከአነጋገር ተከትሎም ለተፈጠሩና ለሚፈጠሩ ችግሮች መቋጫ ለማበጀት በዛሬው ዕለት ሦስት ዓበይት መጠሪያ ስሞች ይኸውም፥ (1) የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፣ (2) ህወሐትና (3) “ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች” ባለ ሥልጣናት ግለሰቦች የሚሉ በተናጠል/በክፍል በክፍል በስፋትና በጥልቀት አብረን እንተረትረዋለን እናትተዋለንም።

የጽሑፉ ዓላማ፥

በኢሳት የሳይበር ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ፊት አውራሪነት የሀገራችን አንድነት ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ በትግራይ ሕዝብ የተቃጣው የመነጠል፣ የማግለልና የማስመታት የኢሳት መሰሪ አጀንዳ ለማክሸፍ፤ እንዲሁም የትግራይ ክልል ሕዝብ በኢትዮጵያ ምድር በሰላማዊ መንገድ ለሚደረገው የሥርዓት ለውጥ ትግል ተሳታፊነቱን አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ተጻፈ።

(1) የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ፥ 

ለአንድ ክፍለ ዘመን ያክል በእንግሊዝ ቀኝ አገዛዝ  የባርነት ቀንበር ስትዳክርና ስትደቅ የነበረችው ሩቅ ምስራቂትዋ  ህንድ የምድሪቱ ፍሬ በሆነው በማህተማ ጋንዲ መሪነትና አስተባባሪነት ዜጎችዋ በጨቋኙ በእንግሊዝ መንግሥት ባደረጉት ያላሰለሰ ሰላማዊ ትግልና ተቃውሞ ህንድ ነጻ አገር ለመሆን ብትበቃም ህንድ በሰላማዊ ትግል ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ እንደወጣች በስምንት ወር ውስጥ ነበር የህንድ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰላማዊ ትግል ህገ ወጥ ድርጊት መሆኑን በማወጅ ሰላማዊ ትግል በሕግ ወንጀል መሆኑን የደነገገው። ልብ ይበሉ! በሰለማዊ ትግል ወደ ሥልጣን የወጣ አካል በትረ ስልጣኑን እንደጨበጠ ዓመት እንኳን ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ሰለማዊ ትግል ወንጀል ነው ብሎ አረፈ።

በተመሳሳይ በአሜሪካ የማንቹስተስ ጠቅላይ ግዛት ተወላጅ የሆነው የእንግሊዝ የታክስ ሕግ በመቃወም የሚታወቀውና የአሜሪካ አብዮት በመምራትም ጉልህ ሚና የተጫወተ ሳሙኤል አዳምስም እንዲሁ ከአብዮቱ ድል በኋላ በተለይ ጦርነቱ ተከትሎ የተከሰተ የኢኮኖሚ ቀውስና አለመረጋጋት ተዳምረው በተፈጠሩ ችግሮች ከአብዮቱ ጎን ተሰልፈው ድል ያደረጉ አርበኞች ጨምሮ በክልላዊ መንግሥት ላይ ባሰሙት ተቃውሞ ክልላዊ መንግስቱ ተቃዋሚዎች በአግባቡ በማስተናገድ ለጥያቄአቸው መፍትሔ በመስጠት ፈንታ ተቃውሞውን ያስተባበሩና የመሩ መሪዎች ማሰሩን ተከትሎ ክልላዊ መንግሥቱ የወሰደው እርምጃ ክፉኛ ያስቆጣቸው ተቃዋሚዎች ድጋሜ መሳሪያ አንስተው ለመታገል በመገደዳቸው በቀድሞ የአብዮቱ ጦርነት ተዋጊ የነበረ አርበኛ በዳንኤል ሻይ የሚመራ “የሻይ አማጽያን” (Shays’Rebellion) በመባል የሚታወቁ በማዕከላይና ምዕራባዊ ማንቹስተስ አከባቢ ይንቀሳቀሱ እንደ ነበሩና ሳሙኤል አዳምስ ይህን የሻይ አማጽያን ተቀላቅለው ያመጹት አሜሪካውያን በስቅላት ይቀጣ እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። ልብ ይበሉ! አብዮትን የመሰረተና የመራ ስሙ ወፍ የምታውቀው አብዮተኛ  ከድል በኋላ አብዮትን በማውገዝ የአብዮተኞች አንገት ከገመድ ጋር በማገናኘት ሥራ ላይ ሲጠመድ።  

እነዚህ ሁለት የምዕራባውያንና የሩቅ ምስራቃውያን ታሪካዊ ምስክሮች ያወሳሁበት ምክንያት ከሞላ ጎደል ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ። ወደ ፍሬ ነገራችን የተመለስን እንደሆነ የትናንት ታጋዮች የዛሬ የሥልጣን ባለ ቤቶች ታግሎ ያታገላቸው፣ ስንቅ ቋጥሮ፣ እግርህ የረገጠው መሬት ውርሻ ይሁንልህ ብሎ መርቆ የሸኛቸው የትግራይ ሕዝብ የትናት ታጋዮች የዛሬ ባለ ስልጣኖች በትግራይ ሕዝብ በከፋ መልኩ እየወሰዱት ያለው እርምጃም ሆነ የትግራይ ሕዝብ ሰቆቋ የሞላበት የግፍ ኑሮ ነባራዊ ሁኔታ ከላይ ከፍ ሲል የተመለከትናቸው ታሪኮች ይመስላል።

 • የትግራይ ሕዝብ ከማንም በላይ የልጆቹን ደም ገብሮ ሲያበቃ ዛሬም ደም እያለቀሰና የደም እንባ እያነባ ያለው ሰሚና ተመልካች ያጣ ሕዝብ ነው። 
 • የትግራይ ሕዝብ ሰንዴ ዘርቶ እንክርዳድ እያጨደ ያለው ረዳት አልባ ሕዝብ ነው። 
 • የትግራይ ሕዝብ ጭቆና በዛ፣ ባርነት በቃ! ብሎ ሽንቱን ጠጥቶ እንደ ፍዬል ቅጠል በልቶ እያደረ የታገለ፣ ደሙ ያፈሰሰ፣ የሞተና የቆሰለ ሕዝብ ሆኖ ሳለ ዛሬም በከፋ መልኩ በትግርኛ ተናጋሪ ደርጎች በጭቆና እየማቀቀ፣ በባርነት ብዛት የደከመ፣ በነጻነት እጦት እየሞተና እየተሰደደ ያለው ሕዝብ ነው።
 • የትግራይ ሕዝብ ሌላው ይቅር የደሴና የአንቦ ከተማ ነዋሪዎች ያላቸውን ነጻነት ያክል አንድ ሦስተኛ ለማየት ያልታደለ ድምጹን የሚያሰማለት የሌለው ሕዝብ ነው።
 • ይህ ሕዝብ ነው እንግዲህ በነጋ በጣባ ቁጥር በኢሳት አንደበት በጠላትነት ተፈርጆ የጥላ ሸት እየተቀባ ያለና ያለ ስሙ ስም እየተሰጠበትና እየተለጠፈበት አለ አግባብ እየተሰደበ፣ እየተዋረደ፣ እየዘነጠለ፣ እየተወረፈ፣ እየተዘለፈና ስሙ እየጠፋ የሚገኝ።
 • ይህ ሕዝብ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ቀርቶ ያለ አንዳች ጭብጥ “በኢትዮጵያ ሀብት ላይ ተዘልሎ የተቀመጠ ሕዝብ ነው” እየተባለ በኢሳት ልሳን ዘሩን ለማጥፋት እየተዶለተለት ያለው።
 • ይህ ሕዝብ ነው እንግዲህ ኢሳት “ኢትዮጵያን ቀኝ ግዢ አድርጎ እየገዛ ነው” በማለት ሌሎች በአመጽ እንዲነሱበት አመጽ እየቀሰቀሰበትና ተመልሶ ራሱን የሚበላ እሳት እያነደደበት የሚገኘው።

አንባቢ ሆይ! ሀገር የምትለማም የምትጠፋም በዜጎችዋ ምርጫ ነውና እርስዎስ ምን ይላሉ?

 • በጎሳ በሽታ የተለከፈ፣
 • ሞያዊ ሥነ ምግባር የሌለው፣
 • በቅሌት የተዘፈቀ፣
 • ቅጥፈት ሐሰትን መናገርና ወንጀላን መንዛት ክብርና የሞገስ ካባ የሆነለት፣
 • ኢትዮጵያን ለመበታተንና የሕዝባችን ሰላም ለመንሳት የሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች አፍ በመሆን የኢትዮጵያውያን ዓይንና ጆሮ እያጠፋና እየደፈነ የሚገኘው አቡሃ ለሐሰት ኢሳት ያለውንና የተናገረውን በመድገም ሀገር ይበትናሉ? ወይስ ውሸትና ቅጥፈት ይብቃ! ሕዝብን መለያየትና ማባላት ይብቃ! ኢሳት በትግራይ ሕዝብ የከፈተው የጥላቻና የጦርነት ዘመቻ ያቁም በማለት ኢሳትን ለመቅጣት ይነሳሉ?

ይቀጥላል

በክፍል ሁለት፥

(2) ህወሐት 

ህወሐት እነዚህ አሁን የምናውቃቸው በጣት የሚቆጠሩ ምቾት ያሰከራቸው፣ የደላቸውና የሰቡ ግለሰቦች የጽዋ ማህበር ሳይሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልጆች ለነጻነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ መስዋዕትነት የከፈሉበት የትግራይ ሕዝብ የታሪክ ማህደር ነው። ህወሐት የትግራይ ሕዝብ የልጆቹን ደም ገብሮ የመሰረተው ታሪኩ ነው። ህወሐት አለ የለም? ለሚለው ያልሰከነ ሙግት ህወሐት አክስዮን ማህበር አይደለም ከስሮ የሚዘጋው። ወደድንም ጠላንም ህወሐት የደም ዋጋ የተከፈለበት የትግራይ ሕዝብ ታሪክ ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Sep. 18, 2013

Advertisements