ትግራይ ሆነ የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ አይደለም! ሲሳይ አጌና

ባሳለፍነው ሳምንት “አበበ ገላው ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሰጡት መልስ” በሚለው ርዕስ የመዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ወንድምና እህት “Vs.” የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ወንዶችና ሴት ልጃቸው ነባራዊ ሁኔታ የሚያጠነጥን የኢሳት ቅጥረኞች የእርስ በርስ ተፋለሶችና አዳፍኔ ምሥክርነቶች አንስተን መወያየታችን የሚታወስ ነው። አቶ አበበ ገላው ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ በተስተዋሉበት ቪድዮ ሌላው አዳማቂ መሳይ ከበደ እዛው በዛው ላነሳው የቤቱ የፈጠራ ጥያቄ አቶ ሲሳይ አጌና የሰጡት እርስ በርሱ የሚጋጭና የተመታታ መልስ እንዲሁም አቶ ሲሳይ አጌና ባሳለፍነው ሳምንት ከበላይ አዛዣቸው ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በነበራቸው የሞቅታ ቆይታ አቶ ሲሳይ አጌና ሻዕቢያን በማወደስና በመቀደስ እንደ ወትሮው ደግሞ ግልጽና በማያሻማ አነጋገር “ትግራይ ሆነ የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ አይደለም!” በማለት የትግራይ ሕዝብ የዘለፉበት፣ በሕዝቡም ያላቸው ምክንያታዊ ያልሆነ ስር የሰደደ ጠላትነትና መሰረተ ቢስ ጥላቻ የገለጹበት ዓረፍተ ነገር እንደምናይ ነበር በቀጠሮ በይደር የተለያየነው እነሆ።

የጽሑፉ ውሱኑነት፥

በጽሑፉ ክፍል አንድ እንደተገለጸ በተመሳሳይ ይህ ጽሑፍ ተናጋሪዎቹ በተናገሩት ቃል ተንተርሶ ተናጋሪዎቹ ዙሪያ ጥምጥም በሆነ አነጋገራቸው ሊያስተላልፉት የፈለጉት መሰሪ ፖለቲካዊ መልዕክት ፈልቅቆ በማውጣት ግልጽ በሆነ መልኩ ለአንባቢ ለማቅረብ የተዘጋጀ ጽሑፍ እንጅ የጽሑፉ አዘጋጅ ምንም ዓይነት የሃሳብ አስተዋጽዖ የላቸውም። በድጋሜ የጽሑፉ አዘጋጅ በዚህ ስራቸው አንዱን በመደገፍ ሌላውን ደግሞ በመቃወም እውነትን የሚሸጡበት ምክንያት እንደሌላቸው ሲገልጹም በታልቅ አክብሮት ነው። 

ሐተታ፥

መሳይ ከበደ ያነሳው ቀድሞ የተቦካ የጓዳ ጥያቄ ይህን ይመስል ነበር፥

“የአቶ መልስ ዜናዊ ልቦና ይጠና የሚሉ ሰዎችም ብቅ ብለው ነበር። በተለይ የአሁን የወጣውን ቪድዮ ይህን የሚያሳይ ይመስለኛል። ለእህትም ለወንድምም የማይራሩ ቢያንስ እንኳን በተወሰነ ደረጃ እሳቸው ወ/ሮ መስፍን ያገኛሉ ያሉት ስድስት ሺሕ ብር እንኳን ቤተሰብ መርዳት የሚቻልበት ሁኔታ አለና እሳቸው ምናልባት ስነ ልቦናቸው ቢጠና እንዲህ ዓይነት በቤተሰብ የመጨከን ሁኔታ የታየበት ነው ይላሉ። አንተ በዛ ትስማማለህ ወይስ የአቶ መልስ ዜናዊ እውነተኛ ማንነት ነው አቶ መልስ እውነተኛ መሆናቸውን ከሙስና ከሚባለው ነገር የጸዱ ለመሆናቸውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዳሰበው አሳክተዋል ብለህ ታስባለህ?” የሚል ነበር

ኢሳት በትግራይ ሕዝብ የተከፈተው መጠነ ሰፊ የጦርነት ዘመቻ በመምራት ረገድ በአጥቂ መስመር ላይ ተሰልፈው ጥሩንባቸው ከሚነፉ ግልሰቦች መካከል አንዱ የሆኑ የደርግ ወታደር ነበር መሆናቸው የሚነገርላቸው አቶ ሲሳይ አጌና ቀደም ብለው ከባለደረባቸው ከመጋረጃ በስተጀርባ አብረው ያቦኩት ጥያቄ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ለጥያቄው የሰጡት ምላሽ የሚከተለው ነበር።

“በደንብ ያሰቡበትማ አይደለም። ለምንድ ነው አንድ ቀላል ነገር እኮ ውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሁሉም ተመችቶች አይደለም። ይነስም ይብዛ ለፍቶ ጥሮ ግሮ ሌላው ቀርቶ ዓረብ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያን እንኳን አገር ቤት ያለውን ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱበት ነገር በቀላሉ ማስታወስ የሚቻለውና (1) አንድ ሰው መጀመሪያ ለቤተሰቡ ካልሆነ ለሌላው ሊተርፍ ይችላል የሚለው ነገር በጣም ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ነገር ነው (2)። ዘርፈዋል አልዘረፉም እሱ በሁለተኛ ደረጃ ይቀመጥ ግን ሰው ካለውም የቅርብ ነው ለሚባለው ሰው መደገፍ ካልቻለ ወንድምየው አንድ ቦታ ላይ የሚነሱት አለ አቶ ጸጋዬ ዜናዊ ባገኘሁት ወቅት ገንዘብን  እንዲረዳኝ ጠይቄው ነበር የለኝም አለኝ ይላሉ እንግዲህ ለቅርብ ለወንድም ያንን ማድረግ ካልተቻለ ለሌላ ሰው ምን ዓይነት ሰው ሊሆን ይቻላል (3) እሱ ራሱ ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ነገር ነው።”

  1. ይህ የአቶ ሲሳይ አነጋገር/ሙግት ቀለል ባለ አማርኛ ያስቀመጥነው እንደሆነ “አይደለም ኢትዮጵያን የምታክል አገር የሚመራ ሰው ወንድምና እህቱ እንዲህ ሲቸገሩ ማየትና መስማት ይቅርና ሰው አረብ አገር የሰው ሳህን እያጠበ በሚያገኛት ነገር እንኳን ቤተሰቡን ይረዳል ስለሆነም መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚያገኝዋት ወርሃዊ ደመወዝ እንኳ ይህን ማድረግ ባይቻላቸው ዘርፈውም ሆነ ገድለው ወንድምና እህታቸው የመርዳት ግዴት አለባቸው። ይህን ባለ ማድረጋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንጀለኛ ናቸው።” ሲሉ ሽንጣቸውን ገትረው ይሞግታሉ። አቶ ሲሳይ አጌና እኔ ብሆን ወደሚል አንድምታ ሲመጡ “ለወንድምና ለእህቴ ያልሆነ ሥልጣን ለምኔ! ለምን አገር አትበተንም! ለምን የፈለገውን አይቀርም! የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ይዤማ ወንድሜ ሳንቡሳ እህቴ ደግሞ ጠላ ሽጣ አይኖርም አትኖርም።” አክለውም “አይደለም የመንግሥት ካዝና የግለሰብ ኪስ ገብቼም ቢሆን ወንድምና እህቶቼን አበለጽጋለሁ” ባይም ናቸው።
  2. “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” በሚል ሞፈክር ድጋሜ ተጠፍጥፈው ለተሰሩ አቶ ሲሳይ አጌና የህግ የበላይ ብሎ ነገር ቀልድ ነው። አቶ ሲሳይ “አንድ ሰው መጀመሪያ ለቤተሰቡ ካልሆነ ለሌላው ሊተርፍ ይችላል የሚለው ነገር በጣም ግምት ውስጥ መግባት ያለበት ነገር ነው” በማለት አፋቸው ሞልተው ሲናገሩ፥

አንደኛ፡ አቶ ሲሳይ አጌና “እንዴት?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ሳይሰጡበት ነው ያለፉ። ዘርፎም ቢሆን ገድሎ የሚለውን ውስጥ ወይራ እንደተጠበቀ ሆኖ። ለመሆኑ ሳንቡሳ መሸጥም ሆነ ጠላ መጥመቅ ምንድ ነው ነውሩ? ሳንቡሳ መሸጥ ሆነ ጠላ መጥመቅ ሥራ አይደለም ወይ? ለሚለው ጥያቄ የአቶ ሲሳይ አጌና መልስ “ለምን እንደ ሳዳም ወንድሞች በሚኒስትርነት ማዕረግ አልተሾሙም?” የሚል ክርክር ሊሆን እንደሚችል አንስተውም። መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቡሳ ሸያጩ ወንድማቸውና ጠላ ጠምቀው ኑሮአቸውን የሚመሩ እህታቸው ባይማሩም በመንግሥት ሥልጣን በሚኒስትርነት ማዕረግ አለመሾማቸው አቶ ሲሳይ አጌናን  ክፉኛ አበሳጭተዋል። አቶ ሲሳይ አጌና በባሌም በቦሌም በኢትዮጵያ የመንግሥት ስልጣን ላይ የመቀመጥ ዕድሉ ቢገጥማቸው ይህን ከማድረግ እንደማይመለሱ እየነገሩን ነው። የሥነ ባህሪ ሊቃውንት እንደሚሉት ሰዎች በወዳጅ ዘመድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተገኝተው ስቅስቅ ብለው የሚያለቅሱ ለሞተው ሰው ሳይሆን ብዙ ጊዜ ራሳቸውን በዛ ቦታ በማስቀመጥ ነው።  እንዲሉ ከዚህ አንጻር የአቶ ሲሳይ እምቡር ማለት መንስኤው ምን ሊሆን እንደሚችል ትስቱታላችሁ የሚል እምነት የለኝም።

ሁለተኛ፡ አቶ ሲሳይ መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ወንድምና እህታቸው ባለመርዳታቸው በቁጣ ሲናገሩና በኢቲቪ ተለቀቀ የተባለው የመዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ወንድምና እህት ነባራዊ ሁኔታ የሚያስቃኝ በምስል የተደገፈ ምስክርነት “መቶ በመቶ እውነት ነው!” ብለው ከመቀበላቸውና ከማመናቸው በተጨማሪ መዋቹ ጠቅላይ ሚስትርሩም ከሙስና ንጹህ ነበሩ ናቸውም! በማለት እየመሰከሩ ነው።

ሦስተኛ፡ እዚህ ቦታ ላይ ሁለት ወንድ ልጆችና አንድ ሴት ልጅ በሚገባ ማሳደግና ማስተማር ተስኖአቸው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ማለፍ አቅቷቸው በወር አስር ዶላር እየተከፈላቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ነው የሚኖሩ ተብሎ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የቤተ መንግሥት ምሥጢራቸው የባከነባቸው የፕሬዝዳንት ኢሳይያስና ልጆቹ ሁኔታ አምጥተን ያመሳከርን እንደሆነ – ወድ አንባቢ! ፕሬዝዳንቱ እንደ አባት ይግለጽዋቸው በማለት ጥያቄ ባቀርብሎት ምን እንደሚሉና ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን እንዴት እንደሚገልጽዋቸው ለሁሉም ግልጽ ነው። የአቶ ሲሳይ መልስ ግን እርስዎ እንደሚገልጹት ወይም እንደሚያስቡትም አይደለም። ልጆቹ በአግባቡ ቀርጾ ማሳደግ፣ ማስተማርና ለቁምነገር ማብቃት የተሳናቸው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ማለት ለአቶ ሲሳይ ለታገሉለት ዓላማ የሚኖሩ፣ የቃል ኪዳን ሰው፣ የጀግኖችም ጀግና ናቸው።

አራተኛ፡ አቶ ሲሳይ መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አገር ለመምራትም ሆነ ለሌላ ሊተርፉ አይችሉም በማለት የሚሞግቱበት ዋና ምክንያት ወንድምና እህታቸው ባለመርዳታቸው  ሲሆን ልጆቹ ማስተማር ስለ ተሳነው የሀገር መሪ ደግሞ አቶ ሲሳይ እንዴት ባለ ሙገሳ እንደሚያወድስዋቸው በሚቀጥለው ክፍል በሰፊው እንመለከታለን።

          3. መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ወንድም እህታቸው ባለ መርዳታቸው “ለቅርብ ለወንድም ያንን ማድረግ ካልተቻለ ለሌላ ሰው ምን ዓይነት ሰው ሊሆን ይቻላል” ተብለዋል። ለነገሩ አይደለም ወጥተው መግባትና ሰርተው መኖር የሚችሉ ሙሉ አካል ያላቸው ወንድምና እህቱ በገንዘብ የማይደጉም ሰው ለልጆቹ የማይራራ፣ ልጆቹ በቅጡ ለማሳደግም ሆነ ለቁምነገር ማብቃት ተስኖት ልጆቹ ሜዳ ላይ በትኖ የሚያውደለድል በካና ወላጅ ምን ዓይነት ሰው ሊሆን እንደሚችልም ሌሎቻችን መልስ መስጠት አይጠበቅብንም። አቶ ሲሳይ ልጆቹ ማስተማርና ለቁምነገር ማብቃት ያልታደሉ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ስብእና በማስመልከት ዱላ ቢያስይዙት እርስ በርሱ የሚከሻከሽ መልስ አላቸው። እዚህ ላይ አቶ ሲሳይ አጌና በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ወጥ አቋም ማሳየትና ማንጸባረቅ ተስኖአቸው በሚገርም ሁኔታ አንዱ በማወደስ ሌላኛው ደግሞ በማንኳሰስ የተካኑ ዋጋ የማያወጣ ባለሞያ ሆነው ነው የምናገኛቸው።

ወጣም ወረደ አቶ ሲሳይ አጌና ቀለብ የሚሰፈርላቸው በአስተሳብ ከሳቸው የማይሻል ሰው ለማምታታትና ለማደናገር እስከ ሆነ ድረስ ነገሩ ለትዕዝብት እስኪዳርጋቸው ድረስ እንዲህ ቢቆላምጡና ቢምታታባቸው ሊደንቀን አይገባም እያልኩ ወደ ቀጣዩ ዝልፍያቸው ልለፍ።

. . .

የአቶ ሲሳይ “ሻዕቢያዎች የታገሉለትን ዓላማ ስላሳኩ (1) ወይ ደግሞ ለታገሉለት ሕዝብ የሚፈልጉትን ስላገኙ የሆኑትን ያለሙትን ሆነው ተገኝተው (2) በህወሐቶች በኩል ግን የታገሉትን ለትግራይ ሕዝብ ሆነው ወደ መላ ኢትዮጵያ ሲመጡ የሆነ የዓላማ መምታታት ስለገጠማቸው ከፍላጎታቸው ውጭ ስለሄዱ ዓላማቸውን ስለሳቱ እያደረጉት ይሆን ወይ ማናልባት ለትግራይ ሕዝብ ትግራይን ብቻ ይዞ ቢሆን ኖሮ እነሱም እንዲህ ዓይነት ዘረፋ ውስጥ አይገቡም ነበር የሚል ነገር ከዛ አንጻር ልናየው እንችላለን (3)።”

አቶ ሲሳይ አጌና ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ባሉ ቁጥር ሌላው ቢቀር ምንም የሚያገናኝ ጉዳይ በሌለው ርዕስ ሳይቀር ሀኪም ለበሽታቸው ያዘዘላቸው መድኃኒት እስከሚያስመስልባቸው ድረስ አስር ሰኮንድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ “ትግራይ  -ትግራይ – ትግራይ” የሚለው ቋንቋ በመደጋገም በአድማጭ አእምሮ ውስጥ በማስረጽ ይህ ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በመነጠል ለአደጋ እንዲጋለጥ የፈልጉበት ምክንያት ምንድ ነው? በማለት ሳይጠይቁ አይቀሩም። መልሱ ቀላል ነው። ከዚህ ቀደም አቶ ሲሳይ ሆኑ ባለደረቦቻቸው በሰፊው “የትግራይ ገዢ መደብ” በማለት ሲጮሁ እንደነበርና “በትግራይ ቀኝ ግዢ ነን ያለነው” ብለው እንደሚያምኑም ግልጽ ነው። ታድያ ይህ የአእምሮ ዝግመት የወለደው አስተሳሰብ ምን ያህል ከሐቅ የራቀ ለመሆኑና ሌላ ፖለቲካዊ አጀንዳ እንዳለው ለማሳየት “የትግራይ ገዢ መደብ ብሎ ቋንቋ የለም!” በሚል ርዕስ በሰፊው ማተቴንና መልስ መስጠቴ የሚታወስ ሆኖ አቶ ሲሳይ በቅርቡ ከበላይ አለቃቸው ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በነበራቸው ቆይታ ህወሐት እያስታከኩ የትግራይ ሕዝብ  የዘለፉበትና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ነጥቦችን በአጭሩ እንመለከታለን።

ለመንደርደሪያ ያክል አቶ ሲሳይ ሻዕቢያ ውሉደ ኤርትራውያን እንደሆነ ሁሉ ህወሐት ደግሞ በተመሳሳይ ከትግራይ ሕዝብ የወጣ እንደሆነ አትተው ሲያበቁ አቶ ኢሳይያስ ልጆቹን አለማስተማሩ ሻዕቢያ ያለሙትን ሆነው ተግኝተዋል አስብሏቸዋል። መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምሮ ሌሎች በስም ተጠቅሰው በምሳሌነት የቀረቡ ባለሰልጣናት ደግሞ ልጆቻቸው እንግሊዝና ቻይና ልከው ማስተማራቸው ግለሰቦቹ ሌላ ስም ከሰጡ በኋላ (እዚህ ላይ ችግር የለኝም) አቶ ሲሳይ ግለሰቦቹ በዝርፍያ የመሰማራታቸው ምክንያት ስያስረዱ በአጭር ቋንቋ የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ እንደሆነና ከምንም በላይ ደግሞ ህወሐት የታገለው ትግራይን ለማበልጸግ እንደሆነ በአሁን ሰዓትም እነዚህ የህወሐት ባለስልጣናት ኢትዮጵያን በመዝረፍ የትግራይ ሕዝብ ልዩ ተጠቃሚ እንዳደረጉት ዙሪያ ጥምጥም ከሆነ አነጋገራቸው በቀላሉ ለመረዳት ይቻላል።

  1. “ሻዕቢያዎች የታገሉለትን ዓላማ ስላሳኩ” እኔምለው ሻዕቢያዎች የታገሉ ልጆቻቸው በአግባቡ ላለማሳደግ፣ ላለማስተማርና ለቁምነገር ላለመብቃት ነበር የታገሉ? ስኬት ይሄ ነው? አቶ ሲሳይ “ሻዕቢያዎች የታገሉ ልጆቻቸው በብዕር ፈንታ ጠመንጃ አስይዘው በድንቁርና ለማቆራመድ፣ ሰላማቸውን አጥተው የሰው አገር ሰላም ለመንሳት፣ ሕዝባቸውን እንደ ጨው በመላ ዓለም ለመበተን፣ አረጋውያን ያለ ጧሪ ቀባሪ ሀገር የወላድ መካን ለማድረግ፣ ስኳር በቀበሌ በወረፋ የሚታደልባት፣ ምግብ በፈረቃ የሚበላባት፣ ውሃ በቦቴ መኪና የሚከፋፈልባት ሀገር ለመገንባት ነው/ነበር የታገሉት። ይህን የተቀደሰ ዓላማቸው ደግሞ በሚገባ አሳክተዋልና ሻዕቢያዎች ክብር ምሥጋና ይገባቸዋል”  እያሉን እኮ ነው። አበስገበርኩ!
  2. “ለታገሉለት ሕዝብ የሚፈልጉትን ስላገኙ የሆኑትን ያለሙትን ሆነው ተገኝተው” ለመሆኑ ሻዕቢያዎች ሆኑ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ወደ በርሃ የወጡና ለ ፴ ዓመታት የታገሉ ሕዝባቸው በርሃ ለማንከራተት፣ ኮንቴይኔር ውስጥ ቆልፈው ለማሰቃየትና ከመሬት በታች ጉድጓድ ቆፍረው ለማሰርና ቁም ስቁሉን ለማሳየት ነበር እንዴ? AI USA, AI London, HMW, CPJ … የሚያወጡት ወቅታዊም ሆነ ዓመታዊ ዘገባና ሪፖርት እየተተረጎመ በሚቀርብላቸው ሥራዎች “.. ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ አለ” በማለት በማስተጋባት ረገድ አቶ ሲሳይ የሚስተካከላቸው የለም። አቶ ሲሳይ እነዚህ ምዕራባውያን ድርጅቶች ስለ ኢትዮጵያ የሚያወጡት ዘገባ እውነት ነው ብለው የሚያምኑ ከሆነ ድርጅቶቹ “አፍሪካዊት ኩባ” በማለት የሚገልጽዋት የኤርትራ ነባራዊ ሁኔታም ሆነ የአቶ ኢሳይያስ አስተዳደር በተመለከተ የሚሉትንና የሚያወጡት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዘገባዎችና ሪፖርቶች አቶ ሲሳይ ምን ነው ማየት የተሳናቸው? “ፍቅር ዕውር ነው” ይሉት ይሄውሎታ። አቶ ሲሳይም ለፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ያላቸው ስሙ የማይጠራ ልዩ ፍቅር ሚዛናቸው ስተው እንዲንገዳገዱ ከማድረጉ አልፎ አፈር ለመላስ አብቅታቿል።
  3. የእኚህ ቀበሌ ተኮር ተናጋሪ ግልሰብ (አቶ ሲሳይ) ውሎ ማቋጠሪያ ያበጀንለት እንደሆነ ግልጽ በሆነ አማርኛ ሊያስተላልፉት የፈለጉት መልዕክት “ትግራይም ሆነች የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ አይደልም ነው! ይልቁንስ “ለእኛ” የሚቀርበን ኤርትራና ኤርትራውያን ናቸው” ነው ሙግታቸው። ቀደም ብየ በመንደርደሪያዬ እንደገለጽኩት የአቶ ሲሳይ አጌና ጎጠኛ ጦር ግለሰቦች ሆነ ህወሐት በማስታከክ የተወረወረው ጦር ያነጣጠረው በሌላ በማንም ላይ ሳይሆን በትግራይ ሕዝብ ያነጣጠረ መሰረተ ቢስ ክስና ጥላቻ ለመሆኑ ቃላቶቹ ብቻ ሳይሆን መንፈሱ ጭምር ማሽተት ይጠበቅብናል። ፖለቲካ እንደ ሂሳብ ሲሰላ ሳይንስ ነውና የሰዎች ንግግር ዓውዱና መንበፈሱ ጠብቆ ቦርቀቅ ተደርጎ በከፍተኛ ጥንቃቄ የተፈታ፣ የተተነተነ፣ የታተተ፣ የተዘርዘረና የተመነዘረ እንደሆነም በዋናነት መልዕክቱ አንድና አንድ ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

United States of America

Sep. 16, 2013

Advertisements