ይሄ ነው የሚጮህለት ኢትዮጵያዊነት? ምን ነው በሞትኩ!

የኤርትራ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ባሳለፍነው ሳምንት ከሀገር ውስጥ (ከኤርትራ) የዜና አውታሮችና የመገናኛ ብዙሐን የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት በማስመልከት የሀገራችን የኢትዮጵያ ታሪካዊ አመጣጥና አመሰራረት አስመልክተው ይህን ብለው ነበር፥

“ኢትዮጵያ ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ተከትሎ የተፈጠረች ሀገር ናት። ያም ሆነ ይህ ሌላ ሰው የፈልገው ሊል ይችላል ይህች ኢትዮጵያ በመባል የምትታወቀው ሀገር ግን ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ተከትሎ የመጣ የዓለም ሥርዓት ሥርዓቱ ራሱ በሚመርጣቸው ገዢዎች ይጠቀምባት ዘንድ የፈጠራት ኃይል ናት።” 

በማለት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን ሲገሸልጡና ሲያዋርዱ ሕዝቦችዋም ሲሸልቱና ሲዘልፉ፤ አገር ይህ ሁሉ ውርጅብኝ ሲወርድባትና ስትቀበል አጣሞም ቢሆን ከአውዱ ነጥሎ “እንኳዕ ካባኻትኩም ተፈጠርና” የተረጎመ፣ ይህን ቃል መሰረት አድርጎም ብዙና ጥቂት የተናገረ፣ የጻፈ፣ ያተተና የጠነቆለ “ተቆርቋሪ” ፍጥረት ዛሬ ምን ዋጠው? የት ገባ? እኔ በግሌ ዜግነታዊ ግዴታዬን ተወጥቻለሁ ገናም እገፋበታለሁ። አርቲስት ታማኝ በየነ  እንደሆኑም የስታንፎርድ ጥይት በሳስቶ እንደጣለው እንደተኙ መሆናቸው መልዕክት ደርሶኛል። ሌሎቹስ?

  • በረባ ባልረባ እንደ ነሐሴ ዝናብ ሲያለቃቅሱ የምናውቃቸው እነ ዶክተር እገሌ፣ ፕሮፌሰር እገሌ የት ገቡ?
  • ታዋቂ፣ አዋቂ፣ ያገር ልጅ፣ ለቅላቂ፣ ብርቅዬ፣ ተንታኝ፣ ትልቅ፣ ክቡር፣ ንኡድ፣ ምሁር፣ አብራሪ፣ በራሪ የት ገቡ?
  • እስክንድር ነጋ ቢሰማ አንዱዓለም አራጌ ቃለ ኢሳይያስ አፈወቂ ቢያደምጥ አስችሏቸው ዝም ይሉ ነበር ወይ? ወደ እስር የተወረወሩበት ምክንያት የሰው አጥር ሲዘሉ ተይዘው እስካልሆኑ ድረስ ማለቴ ነው።
  • ሽግግር እንበለው ግርግር፣ ሰማያዊ እንበለው ምድራዊ፣ አንድነት እንበለው ልዩነት/ምቀኝነት፣ ጥምረት እንበለው ጭንቀት  በአጠቃላይ ሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት በመክሰስ የሚታወቁ የፖለቲካ ፓርቲዎቹና ጉጅሌዎችስ ምን አሉ? “በኤርትራ የሚኖሩ ኢሳይያስ አባታችን እንዳሉት እንዲሁ ነው ታሪካችን!” አሉ? ዝምታው ከዚህ አልፎ ሌላ ሊሆን አይችልም። እኔምለው ግን በቃ ይሄ ነው ዲሞክራሲ? ይሄ ነው ፍትሐዊነት? ይህች ናት በየኢምባሲው በር እንደ ብቅል የምንሰጣላት ኢትዮጵያ? ይሄ ነው ወይ ምላሳችን ከትናጋችን እስኪጣበቅ ድረስ የሚጮህለት ኢትዮጵያዊነት? ምን ነው በሞትኩ! ይህን ሳይሰሙ ያለፉ ኢትዮጵያውያን ፈጣሪያቸው እንዴት ቢወዳቸው ነው በጊዜ የሰበሰባቸው። ታድለው!

በምንም ዓይነት ምክንያት አንድ የሀገር መሪ ያለ ተጨባጭ ታሪካዊ መርጃና ማስረጃ ሌላ ሉዓላዊት ሀገር የሚዘልፍበትና የሚያቃልልበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችል ማናችንም ብንሆን የምንስተው ጉዳይ አይደልም። አባቶቻችንም ስለ ሀገራች ስለ ኢትዮጵያ የነገሩን ታሪክ ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት አልነበረምና የፕሬዝዳንቱ ቃል በመቃወም ድምጼን ሳሰማ መሰንበቴን የሚታወቅ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ታሪካዊ አመጣጥና አመሰራረት በተመለከተ የተናገሩት ቃል ሳላዛንፍ ቃል በቃል በመተርጎም በኢትዮጵያ ስም ለተቋቋሙና “ኢትዮጵያውያን” ነን ለሚሉ ኢሳትን ጨምሮ የተለያዩ ጽሑፎች በማስነበብ ስራ ላይ የተሰማሩ ድረ ገጾች የተናገሩበት መንፈስ ሳይቀር ሞያዊ ሐተታዬን አስደግፌ ልኬ ነበር። ጽሑፌን በማስተናገድ ረገድ ከ Tigrai Online, Ethiopia Zare, Ethiopian Media Forum (EMF) በቀር ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች በአንድራሻቸው ጽሑፌ የተላከላቸው መካነ ድሮች አንዳቸውም ለማስተናገድና ግዴታቸውን ለመወጣት ፈቃደኞች አልሆኑም። ለምን? ለሚለው ጥያቄ ወቅቱ ሲደርስ መልስ የምሰጥበት ይሆናል። በስድብ የሚቆም ያለ እንደሆነም የአንድ “ኢትዮጵያዊ” ድረ ገጽ ባለቤት ይህን ለምን ጻፍክ? ለምን አጋለጥክ? ለምን ተረጎምክ? ብለው ከመበሳጨታቸውም የተነሳ ያልተገራ አፋቸው ሁላ አላቅቀውብኛል።

የሆነ እስኪሆን ድረስ ግን አሁን የምናውቃት ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዳቀፈች ይህን ስም (ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ማለቴ ነው) ይዛ እስከቀጠለች ድረስ ስለ ኢትዮጵያ መቆምና ይህች ምድር ሀገሬ ብዬ መጥራት ምንም የማላፍር ሰው መሆኔን በአክብሮት እየገለጽኩ በዚህ አጋጣሚ የጃንሆይና የደርግ የነቀዘ አጀንዳ/አመለካከት አነግበው የሚክለፈለፉና ህልማቸውንም እውን ለማድረግ ዕንቅልፍ ላጡ ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ ላቃታቸው ጆቢራዎች አጭር መልዕክት አለኝ። ከእንግዲህ ወዲህ ያለፈውን የልዩነት ዘመን ተመልሶ የሚመጣበት፣ አንዱን ሌላውን በበላይነት ረግጦ፣ አፍኖና ጨቁኖ የሚገዛበት በምንም ዓይነት መንገድ እውን ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ይሆን ዘንድ እወዳለሁ። በአማርኛ ቋንቋ ሲጻፍ፥ ወይ ተያይዘን እንለማለን ወይንም ደግሞ ተያይዘን እንጠፋለን። ይህ ትውልድ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚያምን የራሱ የሆነ አመራርና አስተዳደር አጥብቆ ይሻል። ከዚህ ያለፈ “በጃንሆይ ዘመን አስር እንቁላል በአምስት ሳንቲም፣ ኩንታል ጤፍ በብር 25 ይሸጥና ይሸመት ነበር” የሚል ከቅርስነት አልፎ በዚህ አዲስ ትውልድ የፖለቲካ አስተዳደር ቦታ የለውም። 

ጎበዝ! ለምን ደም ይፈሳል? ለምን የሰው ነፍስ አለ አግባብ ይጠፋል? ለምን? – ለምን? የሕዝብና የአገር ሀብት ይወድማል? ሐዘን ለምን? ለቅሶና ዋይታ ለምን? ለምን?። የቋንቋ፣ የባህል፣ የነገድ፣ የወግ፣ የልማድና የአመጋገብ ልዩነቶቻችን እውቅና መስጠትና ማየት ተስኖን፤ እርስ በርስ ተከባብረን፣ ተጠባብቀን፣ ተቀባብለን፣ ተዋደንና ተፈቃቅረን መኖር ካቃተን ደም ሳይፋሰስ በሰላምና በስምምነት ተመራርቀን በቋንቋ የሚመስለን የራሳችን የምንለውን ሕዝብ ይዘን በሰላም አንዱ ሌላውን ይሁንታውን ሰጥቶ መሽኛኘት እንደምንችል ለምን ይዘነጋል? ይህን ማደረግ (በሰላም መለያየት) ይቻላል እኮ። ይህ ደግሞ ሀገርን መግደል ሳይሆን ነፍስን ማትረፍ ነው። ከሰው ነፍስ የከበረ ነገር የለምና። ደግሞም “ሀገር” ናት ለሰው የተሰራችው እንጅ ሰው አይደልም “ለሀገር” የተፈጠረ። ከዚያ በኋላ በሕግ አግባብነት ይኑሮው አይኑሮው አላውቅም ግን “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም ሆነ “የኢትዮጵያ ባንዴራ” ይዞ መቀጠል የሚፈልግ ብሔር ካለ ደግሞ ይሁንለት።

በመጨረሻ ይህ ከጠላት ግንባር ፈጥረህ የገዛ ራስህን ሕዝብ ለማድማት ለማጥቃትና ለመጉዳት መዶለት የጋራ የሆነች ሀገር መበደል ግን የጤና አይደለም። ወንጀልም ነው። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከአውሮፓና ከአሜሪካ ድረስ የዘመተ በአስር ሺሕ የሚቆጠር ሠራዊት “አለን” አሉ። ደግ! እንደ አፋቸው ያርግላቸውና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይህ “አለኝ” የሚሉትን  ወታደር መርተው እግራቸውን ያነሱ ዕለት ግን አቶ አንዳርጋቸው በነፍስ ከተረፈ በቁሙ ውርደትን እንደሚያይ ቅንጣት ታክል አልጠራረርም። 

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Sep. 13, 2013

Advertisements