የአስተሳሰብ እንጅ የዓመት አዲስና አሮጌ የለውም!

በቅድስት ሥላሴ መንፈስዊ ኮሌጅ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ነበር ስሙ ሲሳይ ይባላል። ሲሳይ በማለዳ ቢያገኞት በውድቅት ሌሊት “እንደ ምን አደሩ?፣ እንደ ምን አመሹ?” ብሎ ነገር አልፈጠረበትም። ቀድመው “ወንድም ዓለም ሲሳይ እንደ ምን አደርክ? እንደ ምን አመሸህ?” ያሉት እንደሆነ “እግዚአብሔር ይመስገን!” በማለት ሰላምታ መለዋወጡ የታወቀ ነው። የዚህ ያክል ደግሞ ቀድሞ ሰላም ያለ እንደሆነ ግን ተማሪ ቢሆን አስተማሪ፣ ተባዕት ቢሆን አንስት፣ ሊቀ ጻጻስ ይሁን ምእምን፣ የሚያውቀው ሆነ ለማያውቀው እንግዳ ሰው “እንኳን አደረሰን!” በማለት በታላቅ ትህትና ሰላም ማለቱ የታወቀ ነው። በዚህ ልዩ ማንነቱ፣ በትህትናው፣ በትምህርት ብልጫው፣ በርካታ የሆኑ የግሉ ቃላች በመናገር  በኮሌጁ ማህበረሰብ ዘንድ ጎልቶ የሚታወቅ የሚወደድና የሚከበር ሰውም ነበር።

ከሲሳይ ጋር የተግባባነውና የተዋወቅነው ገና እግሬ ኮሌጁ እንደ ረገጠ ሰሞን ነበር። ያስተዋወቀን ተቀራርበንም እንድንነጋገር ያደረገን ይህች የሰላምታ ልውውጥ ፍልስፍናው ነበረች። በወርሀ ጥቅምት በዕለት ማክሰኞ ከረፋዱ 12 ሰዓት አገባቢ እንደው የማላውቀው ሰው ከመሬት ተነስቶ “እንኳን አደረሰን!” ሲለኝ እንዴት ግር አይለኝም። ለመተዋወቅ መንገድ እያለሳለሰ ያለ መስሎኝ “እንኳን አብሮ አደረሰን” አላልኩም ፈገግ እያልኩ የሰጠሁት ምላሽ “ለምኑ መምህር?!” የሚል ነበር። ሲሳይ “ለዛሬው ዕለት!” የሚል መልስ ይሰጠኛል። ከፊቱ ምንም ዓይነት የሚነበብ የቀልድ መንፈስ ባላይበትም አሁንም እየቀለደ ያለ መስሎኝ እኔም “አምና በዚህ ዕለት ስጋ ነበር እንዴ የሚመገቡ?!” በማለት እመልሳለሁ። ከዚህ በኋላ ወንድም ዓለም ሲሳይ ለማለት የፈለገውን ቁምነገር በሚገባኝ መንገድ ለመግለጽ ጊዜ አልፈጀበትም። እኔም ሲሳይን ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም። ፍልስፍናው፣ ሥነ መለኮቱ፣ ታሪክ አልቀረ ሥነ ተፈጥሮ እስኪበቃኝ ድረስ አስኮምኩሞ ሲሰናበተኝ እኔም “እንኳን አብሮ አደረሰን!” በማለት ተለያየን።

የጽሑፉ ውሱንነት፥ 

ጽሑፉ በይዘቱ ከዓመት በዓል (አዲስ ዓመት) የተያያዘ ያለንን የተሳታተ አመለካከትና አስተሳሰብ ያነጣጠረ ትንተና እንጅ ጽሑፉ ስለ በዓል አስፋላጊነትና አላስፈላጊነት አንስቶ የሚለው ነገር የለውም።

ሐተታ፥

በዓመት በዓል “ይህን አደርጋለሁ ይህን እተዋለሁ፣ በዚህ ገብቼ በዛ እወጣለሁ፣ ለማየት ያብቃችሁ ህይወቴ ትለወጣለች!” በማለት ተስፋ የሚያደርግና የሚመጻደቅ ፍጥረት ይቆጠር ቢባል ከዚህ ህልምና ቅዥት ነጻ የሆነ ሰው ያለ እንደሆነ መፈለግ ነው የሚቀለው።

በአዲስ ዓመት የኃይማኖት፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ የብሔር ልዩነትቶች፣ ድህነት፣ ሁከት፣ ጦርነት፣ ስደት፣ ምቀኝነት፣ ጭንቀትና ልመና ተወግደው ሰላም፣ ጤና፣ ህብረት፣ እኩልነት፣ ነጻነት፣ ብልጽግና፣ ዕድገት፣ ለውጥና ደስታ አዲስ ይሆንለት ዘንድ ተስፋ የማያደርግና የማይመኝ የለም። በምኞት የሚሆን ነገር የለም እንጅ ቢሆን እኔም ደስ ባለኝ። በእርግጥ  አዲስ መንፈስ/አዲስ ህልም አዲስ ዓመት እየተባለ ከሚከበረው በዓል ጋር ምንም ግኑኝነት የለውም። ይህ ብቻም አይደለም አርጅቶ የሚያልፍ አዲስ ሆኖ የሚወልድ ዘመን የለም። እንደ ሣር እንደ ዱር አበባም እንዲሁ አብቦ ነፋስ በነፈሰበት ጊዜም የሚያልፈው የሰው ልጅ ብቻ ነው (መዝሙረ ዳዊት 103፥ 15)። ታድያ ለሰው ተፈጥሮ የማይደሉ፣ የማይመቹና የማይፈለጉ አሽክላዎች ከግል ህይወታችን ሆነ ከሀገራችን ተነቅለው የሚሄዱና በምትኩ የሚያስፈልገንና የምንናፍቀው የምናገኘው እውን ሆኖ የምናየው እንዴት ነው? በማለት ጥያቄ ያነሱ እንደሆነ መልሱ – ቀደም ብለው የተዘረዘሩ በግል ህይወታችን ሆነ በሀገራችን የማንፈልጋቸው “አሮጌ አመት” ተከትለው ጥርግርግ ብለው በምትሃት የሚጠፉ ሳይሆኑ ያመጣቸው/የወለዳቸው አእምሮ ሲፈወስ ብቻ ይሆናል የሚያስፈልጉንና የምንናፍቃቸው በዙሪያችን እንደ ደመና ሊከቡን ጥላ ከለላ ሊሆኑን የሚችሉ። በተረፈ ግን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደራቁብን በምኞች ብቻ በሩቅ መሳለም ዕጣ ፈንታችን ይሆናል።

ዓመት “ስለ ሄደ” ዓመት “ስለ ስለመጣ” የሚለወጥ አንዳች ነገር የለም። ቁልፉ/መፍትሔው ያለው ኮንትራታችን ጨርሰን እስክንሸበለል ድረስ አንዱን ‘እየሸኘን” ሌላውን “እየተቀበልን” በምንገኘው በእኔና በእናንተ እጅ ነው ያለው።  እውነቱን ለመናገር አንዱ እየተቀበለ አንዱን የሚሸኝ ዘመን እንጅ ሰው ዘመን ተቀብሎ ዘመንን አይሸንም። የአቅጣጫ ለውጥ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ እንደሆነ ከዓመት “መባቻ” ሆነ ከዓመት “መጨረሻ” ምንም የሚያገናኝ ዓመትም የምያስጠብቅ  አንዳች ምክንያት የለንም። አይመስሎትም?

“ደስታችሁ በዓመት አንድ ጊዜ ነው፤ መደሰት፣ ድሃን ማሰብና መዘከር የምትችሉም በዓመት አንዲት ቀን  ብቻ ናት” ብሎ የማይቆረስ የማይሸረፍ መመሪያ አውጥቶ የሰጠን ገደብ ያበጀልንና ሹክ ያለንስ ማን ነው? ራሳችን ካልሆነ በስተቀር። የዓመት “መባቻ” ምክንያት በማድረግ እንዲሰማን የምንፈልገው ደስታና የምናሳየው ጥረትና ፍላጎት በሌላ ጊዜ (ቀን) እኩል ይህን ማድረግ አይቻልም ያለ ኃይልስ ማን ነው? “እግዚሃር” ያሳያችሁ ለዚህም ወያኔ የሚወነጅል ነፈዝ አይታጣም። ወረደም ወጣ ዕለት ዕለት ራሳችንን እየመረመርን ካለፈው ስህተታችን እየተማርን ጠንካራ ጎናችን ደግሞ እያጎለበትን ህይወታችንን የምንለውጥበትና ሰው የደረሰበትን ለመድረስ ነው ጥረት ማድረግ፣ መፍጨርጨር፣ መንቃት መታጠቅና መታገል፣ ዓይናችንን ከፍተን ማየት ማሰብና መሰላሰል፣ ዕንቅልፍ ማጣት ጥርስ መንከስና በቁጭት መነሳት የሚገባን እንጅ ቀን እየጠበቅን ፍሬ የማያፈራ ዘር በመበትን አንባክን ለማለት እወዳለሁ።

ወደድንም ጠላንም እግዚአብሔር የሚሰራው ለቅዠት መከላከያ ሳይሆን ለህይወት ህ መመሪያ ይሆንህ ዘንድ በሰጠህ፣ የደም ዋጋ የተከፈለበት በቅዱስ ቃሉ ሁን  ብሎ አንደነገረህ እንዲሁ በመሆን፣ ፍቅር የሆነውን ሕግና ስርዓቱን በመጠበቅ፣ በማክበር፣ ክርስቶስ ኢየሱስን በመልበስ፣ በዕለት ዕለት ህይወትህም የልጁን ምስል በመግለጥ በማሳየትና ለሌሎች ምስክር በመሆን ብቻ እንጅ ከዚህ ውጭ “… ምድርን ያለ መሰረት – ሰማይ ያለ ባለ ያነጠፍክና ያቆምክ …” በማለት እጥፍ ዝርግት እያልክ በቃላት ጋጋታ ብትማልልና ውለህ ብታድር ጠብ የምትል ዝናብ ከሰማይ አታወርድም። ጥጉ በቁዘማና በማላዘን ዘንበል የምታደርገው እግዚአብሔር የለም ነው መልዕክቴ።

ለወዳጅ መልካም ምኖት መመኘት፥ ከቀድሞ መናኛ ህይወት በመላቀቅ በአዲስ የህይወት ጎዳና አዲስ ኑሮ ለመጀመር ማሳብና ድሃን መዘከር ዓመት እየጠበቅን የምናደርጋቸውና የምንሆናቸው መታሰቢያዎች ሳይሆኑ እንዲህ ያለ ስብዕና በዕለት ዕለት የኑሮ ጉዞአችን ልንለማመደውና ተግባራዊ ልናደርገው የሚገባ ግዴታችን መሆኑን ልብ ብሏል? እኔ እስከማቀው ድረስ ለበሽታቸው መድኃኒት ፍለጋ ወደ ቤተ ሳይዳ የማጥመቂያ ስፍራ ይወርዱና የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ ይንቦጫረቁ የነበሩ የኢየሩሳሌም ዕውሮች፣ አንካሶች፣ ሰውነታቸውም የሰለለ ነው። የእርስዎስ? ከሰው በታች ያደረገን የአእምሮ ፈውስ ያስፈልገናል ነው የምሎት።

ይህን ያውቁ ኖራል!

  • የራሳችን ማለትም የውስጣችን ችግር ሳናውቅ ሳንፈታና ሳንመለክት ውጫዊ ችግሮችን ለመፍታት የምናደርገው መፍጨጨርስ ትርፉ መላላጥና ራስን በራስ መግደል ማለት እንደሆነ ያውቁ ኖሯል ወይ?
  • ዓመት በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ ዓመት በዓሉ ነው ብሎ የሚያምን ቁጥር ቀላል አይደለም። ችግሩ እኛ ስላለን፣ በልተንና ጠጥተን ስለረካንና ጠግበንም ስላደርን ብቻ ሌላው እንዲሁ በልቶና ጠጥቶ  የሚያድር ነው የሚመስለን። ዳሩ ግን አንዱ በግና ዶሮ አርዶ፣ ጠጅና ጠላም ጥሎና ጠምቆ ውክክል ሲል ድግሱ ቀርቶበት ንጹሕ የሚጠጣ ውሃ አጥቶ ጉሮሮው ደርቆበት በረሃብ አለንጋ የሚገረፍም መኖሩን ያውቁ ኖሯል? እንግዲያውስ በዓል (በተለይ በድግስ ደምቀው የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት) “በባህሪው” አንጻራዊ ነው። ይህ ማለት ላለው ሰው ወርሀ ጥር ከውርሀ ሰኔ፤ መስከረም አንድ ከመጋቢት፣ ሚያዚያና ግንቦት … አንድ፤ ቅዳሜና እሁድ ከሮብና ዓርብ ማንም ዓይነት ልዩነት የላቸው የደስታ፣ የፌስታ፣ የምርጫ ዓመታት ወራትንና ቀናት ናቸው። የነጣ አንገተ ጎባጣ ለድሃ ወገኔ ደግሞ በአንጻሩ ዓመቱም ወራቱና ቀናቱ እኩል የችጋር፣ የእጦት፣ የልመና የቁምጥ፣ የሐዘንና የለቅሶ፣ የጭንቅና የጨለማ ወቅቶች ናቸው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

Sep. 12, 2013

Advertisements