ጀዋርም አለ፡ ኢሳት ስራህ ምንድ ነው ቢሉት ኢቲቪ ልማታዊ ነው አለ!

የኢሳት እንጀራ በዋናንት ካበሰሉ መካከል የቀድሞ የኢ.ፌ.ድ.ሪ መንግስት መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አሉም አላሉም በስማቸው “እንዲህ አሉ” እየተባለ በቆርጠህ ቀጥል ከሚሰራጭ ፕሮፖጋንዳ ቀዳሚ ስፍራ ይይዛሉ (አንባቢ ሆይ! ብዕር አጣጣሌን ረጋ ልብ ብለው ይመለከቱ አላሉም አላልኩም)።

 • አንደኛ: ቢሉ እንኳን ከአውዱ ውጭ በመውሰድ የሚተረጎሙ ለመሆናቸው፤
 • ሁለተኛ: “አሉ” ተብሎ የሚነዛው ተራ ወሬ ደረቅ መረጃ የማይቀርብበት ለመሆኑ፤ 
 • ሦስተኛና የጽሑፉ አዘጋጅ ዋና ትኩረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት በርካታ ዓመታት “አሉ” እየተባለ የተነገረና መነገሩን በተቀናጀ መልኩ እየቀጠለበት የሚገኘው ነገር ዛሬ ደግሞ ቃል በቃል አቶ ጀዋር መሃመድ በመባል የሚታወቅ ግለሰብ በድጋሜ ስንሰማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክል ነበሩ ማለት ይሆን? በማለት የጽሑፉ አዘጋጅ ያልገባቸውን ይጠይቃሉ? 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኑ በሊቀ መንበርነት ይመሩት የነበረው ህወሐት “አሉ” የሚባለው ቃል የጠላት ሃሳብ ከሆነ ቃላቸው ሳያዛንፍ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያለመታከትና ያለ መሰላቸት እየደገመና እያስተጋባ የሚገኘው ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ በኢሳት ዘንድ ለምን በዝምታ ታለፈ? ኢሳቶች ያለውንና የሌለውን፥ የሚገባውንና የማይገባውን፥ የሆነውንና ያልሆነውን ስም እየሰጡና ይደልዎ! በማለትም ያስተዋወቁት ግልሰብ ካወጡት ከፍታ ለመፈጥፈጥና ለማውረድ የሚናገሩት አጥተው ይህን? የኢሳት ዝምታ ቃላት የማጣታት ችግር ይሆን? ወይስ የነካነው እንደሆነ ስመ ዝክራችን ያጠፋናል በሚል ፍራቻ ነው?

እንዲህም እላለሁ ጀዋር መሐመድ ኢትዮጵያ በሚመልከት የተናገረው ሁሉ ኢሳቶች ጀዋር አንዳች ስህተት የለውም የተናገረው ሁሉ ትክክል ነው ብለው ስለሚያምኑ ይሆን እንዴም እላለሁ? ከሆነስ መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ለምን በእንደ እነ ኢሳት ያሉ የግንቦት 7 ድምጽ ማጉልያ ተቋም ያለ ስማቸው ስም እየተለጠፈባቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በጠላትነት ፈርጆ በሳቸው ላይ ይነሳ ዘንድ የጥላቻ ዘመቻ ተከፈተባቸው? ለምን የነፈዞችና ስራ ፈት ግለሰቦች ሰለባ ሆኑ?  ወይስ የኢሳት ጠላትነት ከወገኖቻችን ከትግራይ ተወላጆችና ከትግራይ ሕዝብ ብቻ ስለ ሆነ ነው?

መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ለኢሳት ብቻም አይደሉም ለአንዳንድ እንደ ማንኛውም ዜጋ ስራ ሰርተው በላባቸው ኑሮአቸውና የቤተ ሰቦቻቸውን ህይወት በአግባቡ መምራት ላልታደሉ ግለሰቦች ጭምር በአቋራጭ ከሰው በላይ ሆነው ይታዩ ዘንድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክተዋል። በሞታቸውም እያበረከቱ ይገኛሉ።

መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሙቀት እንደነበሩ በየትኛውም የፖለቲካ ካምፕ በሚገኙ ሰዎች ዘንድም የሚካድ አይደለም። ከዚህ ዓለም ሲሰናበቱም ከግለሰብ እስከ ፖለቲካ ፓርቲ ወደ መቃብራቸው ይዘውት ያልወረዱት ፈልገህ ለማግኘት አዳጋች ነው። አመል ሆኖባቸው አልፎ አልፎ ቀዳዳ እየፈለጉና እየፈጠሩ ብቅ ከሚሉ በስተቀርም የሚሰደብ/የሚጮህበት ሰው ሲጠፋ ብዙዎች “ብዕሮቻቸው” ሰቅለዋል ገጸ ምሳላቸውም ጠፍተዋል።

አብርሃም ሊንከን (16ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት) ከሚታወቅበትና ከተናገረው ቃል ልነሳ። ሊንከን በስልጣን በነበረበት ዘመናት በተጫዋችነቱ በቀልደኛነቱና ከአንደበቱ በሚጡ አስተማሪና በተለይ አስቂን ቀልዶቹ ይታወቃል። ከዕለታት አንድ ቀን ሊንከን የዚህ ተወዳጅ ስብእናው ሚስጢር ሲናገር ያለው ይህንን ነበር። ይሄ የሚያስቃችሁና የሚያዝናናችሁ ንግግር እኮ ከእኔ ከራሴ ፈጥሬ የምናገረው ሳይሆን ይልቁንስ ከሰዎች የሰማሁትን ነው ለእናንተ ደግሜ የምናገርው ሲል መናገሩን የታሪክ ሰዎችና መጻህፍት ይተርካሉ።

የጎሳ ዜማ አቀንቃኝ (Racial Activist) ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ ቀደም ሲል በሚኒሶታ ሚኒአፕለስ ከተማ በእምነት የሚመስሉትን የአከባቢው ተወላጆች ሰብስቦ ያደረገውን ንግግር፤ ቀጥሎም በአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ በስትሪም ፕሮግራም ያደረገውን ኮንፈረንስ ከአንደበቱ ፍሬ የተነሳ ለብዙዎቻችን እንደ ሊንከን ባያስቅም ብዙሐኑ ኢትዮጵያውያን ያስቆጣ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱን ይታወቃል።

ግለሰቡ ባሳለፍነው ሳምንት “ኢትዮ ቲዩብ” (ድረ-ገጽ ይሁን ቴሌቪዥን ጣቢያ የጠራ መረጃ የለኝም) ባደረገው ቃለ ምልልስ ግልጽ እንዳደረገው ቀደም ሲል ባደረጋቸው ንግግሮች እንደማይጸጸትና ያደረገው ንግግርም ምንም ቢሆን ከራሱ አንዳች አዲስ ነገር ይዞ እንዳልመጣ ይልቁንስ ጥያቄው ከሃምሳ ዓመታት በፊት በአባቶቹ የተነሳ ጥያቄ እንደሆነና እንደነበር  እስምሮበት አልፈዋል።

በእርግጥ እኔ ይህ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቅኩት አሁን ካለው የእስልምና ግርግር በተያያዘ ከአንድ ዓመት የማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ነው። ለዛውም ዛሬ እንዲህ አናታቸው ሊሸናባቸው ይህን ግለሰብ የማወቅ ዕድሉ ያገኘሁት በኢሳት አማካኝነት ሲሆን ኢሳት “ወጣት ኢትዮጵያዊ ምሁር”፥ “የፖለቲካ ተንታኝ”፥ “የኮሎምቢያ ዘበኛ” ወዘተ በሚሉ ተቀጽላዎች ሲያስተዋውቁትና ጣራ ሲያነኩት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ “ምን እንደሚመስልም” በቴሌቪዥን መስኮት ያየሁት። ሰውዬው አፉን ከፍቶ ከመናገሩ በፊትም በፕሮግራሙ መሪ ቀደም ብለው የተወረወሩ ተቀጽላዎች – ሰው እስከ መቼ “በጃንሆይ ዘመን ዶሮ 15 ሳንቲም ትሽጥ ነበር” እያሉ በሚያላዝኑ “ፖለቲካ እስከ መቃብር” ባዮች እንጠበሳለን ስል ተስፋ ሰንቄ አሰፍስፌ መጠበቄ ነበር።

ቃለ ምልልሱ ተጀመረ። የመጀመሪያ ቀን በትዕግስትና በጥሞና ንግግሩ ያደመጥኩ ዕለት ግለሰቡ መጠነኛ የማንነት ቀውስ እንደሚንጸባረቅበትና ከሞላ ጎደልም ጤና እንደሚጎድልበት ለማወቅ ጊዜ አልፈጀብኝም። ይህ በእንዲህ እንዳለ  ሙሉ በሙሉ ይሄ ነው ለማለትም ሆነ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ግን አልተቻኮልኩም ነበር። ቤተ ክህነት እንዳደገ ሰውም “ጥቁሩ – መልአከ ጸሐይ/ብርሃናት”፣ “አካለ ጎደለውን – መልዓከ ሃይል”፣ “መንዳቢውን – መጋቤ ካህናት”፥ “መሰሪውን – መልዓከ ህይወት” ሲባል እያየሁ እየሰማሁ ያደግኩ ሰው እንደ መሆኔ መጠን በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ፖለቲካም እንዲሁ “ካታሊስቱ – አክቲቪስት”፥ “የጋዜጠኝነት ጠረን የሌላው ወረኛ ሁላ ጋዜጠኛ”፣ “ተረተኛውን – ተንታኝ” … የማለት ተመሳሳይ በሽታ ለመኖሩ ማስተዋል ስለቻልኩ ያሰፈሰፈ ልቤ ረጋ እንዲል ትልቅ አስተዋጽዖ አበርከተዋል። ጥጉ ሰውዬ ተጋኖ ባይቀርብ እኔም ልብ ባልጣልኩበት ነበር።

በሌላ ጊዜም በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ሲናገር አሁንም የተሻለ ነገር ባላገኝበትም ከአንደበቱ ለሚወጡ ቃላቶችና የግለሰቡ አስተሳሰብ ግን ልብ ማለት እንደሚገባኝ ተማርኩ። ይህን ተከትሎ ያደረግኩት መጠነኛ ፍለጋዎችም የፈራሁት አልቀረም የሰውዬው ህልውናውን ያወቁበት ዕለት ያደረብኝኝ ጥርጣሬ እውነት ሁኖ አገኘሁት። ታድያ አንዳንድ ጊዜ የሚያደርቸው መልካም ንግግሮችና የሚሰጣቸው አስተያየቶች ደግሞ ከሌላኛው ገጽታው የሚጣረስ ሆነው ሳገኘው ይባስ ጥርጣሬዬ አጎለበተው። አንዳንድ ንግግሮቹም አምኖባቸው ሳይሆን ከአንገት በላይ ለመሆናቸው የሌንን የፖለቲካዊ ሂደት በተለይ ከስደት መልስ በኃላ የነበረውን ገጽታ ያጠና ሰው ይህ ሰው ማን እንደሆነ አይስተውም። እኔም አልሳትኩትም ያወቁትም አሁን አነጋጋሪ ሆኖው የተገኙ ንግግሮቹን በይፋ ከመገለጣቸው በፊት ያኔ ነበር።

ታድያ በወቅቱ ይህን ግለሰብ የሚያራምደው እምነትና ፖለቲካዊ አቋሙ በማስመልከት ብጽፍ አንድ ጽሑፌን የሚለጥፍልኝ የለም በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ታቦት ተቀርጾለት አምልኮ ብቻ በቀረው ግለሰብ ጭብጥ ላይ የተንተራሰ ጽሑፍ መጻፍ ሃሳብህን መግለጽ ማለት ሌላ ስም ይሰጠኝ ዘንድ በገዛ እጄ ነገር መጫርና አጀንዳ ማስከፈት ነው የሚሆነው   በማለት  በወቅቱ አስተያየቴን ማካፈል ሳልችል ቀርቻለሁ።

በመግቢያዬ እንደ ገለጽኩት ኢሳት ከሚታወቅባቸው ስራዎች መካከል አንዱ ሕዝብ ከመንግስት፥ አንደኛውን ጎሳ ከሌላቸው ጎሳ፥ አንዱን የመንግስት ሹም ከሌላኛው እኩያው ለማጋጨት፥ ለማለያየትና ለማላተም በሚያደርጋቸው ብርቱ ጥረት ለመሆኑ በሀገር ወዳድ  ኢትዮጵያውያን ዜጎች ዘንድ የታወቀ ነው/ይታወቃል። ሕዝብ ከመንግስት? እኮ እንዴት? በማለት ይጠይቁ ይሆናል። በዚህ ረገድ መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ግንባር ቀደም ገጸ ባህሪም የኢሳት ሰለባም ነበሩ።

አንደኛ፡ ኢሳቶች “ህወሐት ወደ በርሃ የወጣው ትግራይን ከአማራ ጭቆናንና ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ነው” ብሎው ያምናሉ። ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮም ይህን ሲያስተጋቡ ሲያመላልሱና ሲያትቱ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ይህ የኢሳት እምነትና የዕለት ዕለት ዜና የተረጎምነው እንደሆነ ዜናው በቀላሉ ሁለት መልዕክቶችን ያስተላልፋል።

 1. ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ጸረ አማራ ነው! የሚል ሲሆን፤
 2. ህወሐት የአማራ ሕዝብ ጨቋኝ ነው ብለው ያምናሉ የሚሉት አንድምታዎች ያዘለ ነው።

ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ ደግሞ እንዲህ ይላል “ከህወሃት በፊት የነበሩ መንግስታት (የደርግ መንግስት ጨምሮ ማለት ነው) ሕዝቡን በመጨፍለቅ አንድ ወጥ የሆነ በአማራ የበላይነት ስር የተገነባ ሀገር ነው መገንባት የፈለጉት።” አክሎም “ኤክስትራክት” ሲያደርጉትም የነበረው አማራውን በዬ ቦታው በመላክ ሕዝብን እያስተዳደረ “ሪሶርስ” ኤክስትራክት እያደረገ ወደ ማዕከላይ መንግስት ገቢ እንዲያደርግ ነበር የፈለጉት” ይላል።

ሁለተኛ፡ ኢሳቶች “አቶ መለስ/ህወሃት ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ ያላትና በአጼ ምኒሊክ የተቆረቆረች ሀገር ናት ብለው ያምናሉ።” ብሎው ተናግረዋል በማለት ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ይህን ሲያስተጋቡ ሲያመላልሱና ሲያትቱ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ይህ የኢሳት የዕለት ዕለት ዜና የተረጎምነው እንደሆነ ዜናው በቀላሉ ሦስት መልዕክቶችን ያስተላልፋል።

 1. መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ጸረ ሀገር፤
 2. ጸረ ታሪክ፤
 3. ጸረ ምኒሊክ (ጸረ አማራ) ናቸው። የሚል አንድምታ ሲኖረው፦

ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ ደግሞ እንዲህ ይላል “አሁን የምናውቃት ዘመናዊ ኢትዮጵያ የዛሬ መቶ ዓመት ምናምን ነው በምኒሊክ ነው የተገነባችው። ኢትዮጵያ የመጣችው የዛሬ መቶ ምናምን ዓመት ነው። ከዛ በፊት አልነበረችም። አሁን ያለችው የጋራ ኢትዮጵያ የአንድ መቶ የአንደ መቶ ዓመት ታሪክ ብቻ ነው ከዛ ሊያልፍ አይችልም” ይላል።

ሦስተኛ፡ ኢሳቶች አቶ መለስ “ለወላይታው አክሱም ምኑ ነው” ብሎው ተናግረዋል በማለት ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ይህን ሲያስተጋቡ ሲያመላልሱና ሲያትቱ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ይህ የኢሳት የዕለት ዕለት ዜና የተረጎምነው እንደሆነ ዜናው በቀላሉ ሦስት መልዕክቶችን ያስተላልፋል።

 1. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥላቻ የተሞሉ የጥላቻ ሰው ናቸው፤
 2. ራሳቸውንና የትውልድ አካባቢያቸው (ጎሳቸውን) አልቀው ያያሉ፤
 3. ጎጠኛና ከፋፋይም ናቸው። የሚል አንድምታ ሲኖረው፦

ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ ደግሞ እንዲህ ይላል “አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ የኔን ዓይነት ሰዎችና የኔን ማንነት ኢንተርተይን ሊያደግ የሚችል ዓይነት አይደለም። ራሴን በዛ ውስጥ ማየት አልችልም። በማንነት ደረጃ ከመጣህ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ማንነት ተብሎ የሚቀርበው ነገር እኔን ሊወክለኝ አይችልም። ሁለተኛ ማንነት እስከሌለ ድረስ ዛሬም ነገም ወደፊትም የኔ ማንነት ኦሮሞ ነው። … ምኒልክ ደግሞ ማን እንደሆነ: የማን ቤዝ ይዞ እንደመጣ: የማን ጦር ይዞ እንደመጣ የታወቀ ነው።” ይላል። በሌላ አነጋገር “ኢትዮጵያዊነት ብሎ ነገር ለእኔ ለኦሮሞ ምኔ ነው? አይመለከተኝም።” በማለት እምነቱን በአራት ነጥብ ዘግተዋል።

አራተኛ፡ ኢሳቶችአቶ መለስ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነች” ብሎው ተናግረዋል በማለት ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ይህን ሲያስተጋቡ ሲያመላልሱና ሲያትቱ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ይህ የኢሳት የዕለት ዕለት ዜና የተረጎምነው እንደሆነ ዜናው በቀላሉ: መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ሀገር ገንጣይ አስገንጣይም ናቸው ለማለት የተፈለገ ሲሆን:

ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ ደግሞ እንዲህ ይላል “ኢትዮጵያ አሁን ያለችው የጋራ ኢትዮጵያ የአንድ መቶ የአንደ መቶ ዓመት ታሪክ ብቻ ነው። ከዛ ሊያልፍ አይችልም። ከዛ በፊት ኦሮሞ የ 5000 ሺህ ታሪክ አለው ወላይታ የ5000/7000 ሺህ ታሪክ አለው አማራው የዛን ዓይነት ታሪክ አለው ትግሬው የራሱ ታሪክ አለው። በጋራ ግን ህብረ ብሔር የሆነችው የዛሬዋ ኢትዮጵያ የጋራ ታሪክ አሁን የምናውቃት ኢትዮጵያ ያላት የዚህ የመቶ ዓመት ምናምን ብቻ ነው። … ምኒልክ ሲመጣ ያደረገው ምንድ ነው ያንን ለየብቻ ያለ ማንነት ንዶ አንድ የአማራ ባህል ነው በሕዝቡ ላይ የጫነው” ሰውዬው እያለ ያለው ኦሮሞ የሚባል ሕዝብም ሆነ ኦሮሚያ በመባል የሚታወቀው ክልል ኢትዮጵያ በምትባለው የምኒልክ ቅጥቅጥ  የአማራ ማንነት መገለጫ የሆነችው አገር ቅኝ አገዛዝ ስር ያለች ሀገርና ያለ ሕዝብ ነው አያለ ነው።

አምስተኛ፡ ኢሳቶች “አቶ መለስ እንኳን ከእናንተ ተፈጠርን” ብሎው ተናግረዋል በማለት ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ይህን ሲያስተጋቡ ሲያመላልሱና ሲያትቱ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ይህ የኢሳት የዕለት ዕለት ዜና የተረጎምነው እንደሆነ ዜናው በቀላሉ መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ዘረኛ ናቸው በማለት ንግዱን አጧጥፏል።

ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ ደግሞ እንዲህ ይላል “ሁለተኛ ማንነት እስከሌለ ድረስ ዛሬም ነገም ወደፊትም የኔ ማንነት ኦሮሞ ነው።” በማለት የኦሮሞ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ የሚሰማውን ወሰን የሌለው ደስታ ገልጸዋል።

አሁን ለማየት የጓጓሁት ነገር ቢኖር ሌላ ምንም ሳይሆን ለኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያ እየተባለ የየዋኅን ዜጎች ኪስ ለመቦርበር በሚዘጋጁ መድረኮች ተረኛ መለመኛ ማን ይሆን የሚለውን ነው። የለመደች ምላስ በማን ስም ትነግድ ይሆን? ከእንግዲህ ወዲህስ የማን ክሊፕ እናይ ይሆን? እንደ ተለመደ መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር እንዲህና እንዲያ ይሉ ነበር እየተባለ እምቡር ማለቱ ይቀጥል ይሆን ወይስ ተረኛው ጀዋር ሆኖ የጀዋር ስም በተራው መለመኛ ይሆናል?

ግለሰቡ የሚድያ ያለህ! ሲል ተደምጠዋል። የኢሳት ዝምታ አሳስቦትም መድረክ ይዘጋጅና ደም ያለው ሰው ይግጠመኝ/ይሞግተኝ ሲልም በጠረጴዛ ዙሪያ ለመከራከር ዝግጅነቱን አረጋግጠዋል ጥሪውንም አቅርበዋል። ከነተረቱ “በቅሎ አባትህ ማን ነው ቢሉት አህያ አጎቴ ነው አለ” እንደሚባለው እንዲህ ባለ ሰዓት ኢሳቶች ደግሞ ሰምተው እንዳልሰሙ አይተውም እንዳላዩ በመምሰል በአንጻሩ ራሳቸውን ባልተገባ ስራ አጥምደው ቆባቸውን ቀደው እየሰፉ ይገኛሉ። ይህን  የኢሳት ግራ መጋባትና የመቀላቀል ነገር ያስተዋሉ የጽሑፉ አዘጋጅ ደግሞ የቅጥረኞች ቅሌት ለመግለጽ ያክል “ኢሳት ስራህ ምንድነው ቢሉት ኢቲቪ ልማታዊ ነው አለ!” በማለት  አንባቢያን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ጥያቄአቸው ለማቅረብ ተገደዋል።

በመጨረሻ፡ “መሐራ እግዚኦ ለነፍሰ መራሔ መንግሥትነ ገ/ማርያም!” ገብረ ማርያም ማለት የመዋቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስመ ክርስትናቸው ሲሆን “መሐራ እግዚኦ ለነፍሰ መራሔ መንግሥትነ ገ/ማርያም” የሚለውን የግዕዝ ቋንቋ ወደ አማርኛ የመለስነው እንደሆነ ደግሞ “አቤቱ የመራሔ መንግሥታችንን የገብረ ማርያምን ነፍስ ማር” የሚል ትርጉም ይኖረዋል።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s