ኢሳት ስለ ሐውዜን ምን አለ?

በደርግ ዘመነ መንግስትም ሆነ ከሻዕብያ ጋር በተደረገ ጦርነት የሐውዜን ሕዝብ ያክል የዘመተ፣ የሞተና አካሉ የጎደለ ለቁጥር የሚጠጋ አንድም የትግራይ ከተሞች የሉም። የሐውዜን ህዝብ አገሩን ከማናቸውም ወረራና በደል ለመከላከል በተደረገው ትግልም ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ተሰልፎ ለአገሩ ሉዓላዊነት የዘመተ ሕዝብ ነው። የሐውዜን ህዝብ ደሙ ቢመረመር የራሱ ለሌላ አሳልፎ የማይሰጥ የሌላውንም የማይፈልግ የትግል ደም ያለው ህዝብ ነው። ትግልና የሐውዜን ሕዝብ ተነጣጥለው አይተረጎሙም። ሴቱም ወንዱም ሲዘመት ሽማግሌ አረጋውያን የቀናት የእግር ጎዞ በመሄድ ስንቅ በማቀበል ግዴታቸውን ተወጥተዋል።

አንድም በአመራር የተቀመጠ የሐውዜን ተወላጅ ባይኖርም ሦስትና አራት ልጆቹን ያልገበረ የሐውዜን ወላጅ ግን ተፈልጎ አይገኝም። የአድዋ ልጆች እንቅፋት ሳይገጥማቸው ለከተማ ሲበቁ የሐውዜን ወጣቶች በበርሀ ቀሩ፤ የአድዋ ልጆች የከተማቸው ስም በዓለም የወርቅ መዝገብ ለማስፈር ሲያሴሩ የሐውዜን ሕዝብ ደም ደግሞ ከውሻና ከአህያ ደም ተቀላቅሎ እንደጎርፍ ፈሰሰ፤ የአድዋ ስመ ታጋዮች በትረ ስልጣኑን ሲያጣብቡ የሐውዜን ወጣቶች መቃብር ታጣላቸው፤ አድዋ ገዢዎችና ከበርቴዎች ስትፈራርስ ሐውዜን ደግሞ ሌላው ቀርቶ ድምጹን የሚሰማ አንድ ሰው ታጣባት፤ የአስመራ ወታደሮች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲላኩ የሐውዜን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ ወደ ውህኒ፤ የአድዋ ወላጆች በልጆቻቸው ወርቅ ሲሸለሙ የሐውዜን ወላጆች ደግሞ መጨረሻቸው እስርና ግርፋት ሆነ። የትድግና ያለህ!

“ሐውዜን ከከተማነት ደረጃ ዝቅ መደረጓ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ” የሚል ዜና ያነበኩት አገር ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ ከሚታተሙ የግል ጋዜጦች አንዱ የሆነው ከሪፖርተር ድረ ገጽ ነበር። ሪፖርተር የተጠቀሰው ርዕስ ይዞ ለንባብ የበቃ እአአ ነሐሴ 11, 2013 ሲሆን ንባቡ አጭር ግልጽና ጠቃሚ መረጃ የያዘ በመሆኑ ማስተላለፍ ወደምፈልገው መልዕክት ከመሄደ በፊት ዜናውን ላላነበባችሁት ሙሉ የዜናውን ይዘት ታነቡት ዘንድ ሳልጨምር ሳልቀንስ እንዲሁ እንዳገኘሁት አስቀምጨዋለሁ መልካም ንባብ።

በአክሱም ዘመነ መንግሥት እንደተመሠረተች የሚነገርላት ጥንታዊቷ ሐውዜን በቅርቡ በክልሉ መንግሥት ከከተማ ደረጃ ዝቅ ብላ በቀበሌ እንድትተዳደር መወሰኑ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ፡፡ ድርጊቱን ለመቃወም በከተማው ነዋሪዎች የተወከሉ ግለሰቦች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ሰኔ 15 ቀን 1980 ዓ.ም. በገበያ ቀን በተካሄደ የአውሮፕላን ድብደባ 3,000 ያህል ገበያተኞች ተገድለውባት በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት በደረሰባቸው ሐውዜን፣ እስካሁን ምንም ዓይነት የመልሶ ግንባታ ሥራ ሳይደረግባት ቆይቷል፡፡ በወቅቱ የፈራረሱ ቤቶች እስካሁን ኦና ሆነው የሚታዩ ሲሆን፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ወደኋላ ከቀሩት መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኗ ይነገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት ባወጣው የከተሞች አዲስ አደረጃጀት ሐውዜንን የራሳቸው አስተዳደር ከሌላቸው ከተሞች መካከል የመደበ ሲሆን፣ አንዳንድ በቀበሌ ሲተዳደሩ የቆዩትን ጨምሮ ከ17 ከተሞች ስምንቱን በማዘጋጃ ቤት ከሚተዳደሩት መካከል አድርጎ መርጧል፡፡ ክልሉ ካስቀመጣቸው 12 መስፈርቶች አብዛኛውን አሟልታለች በሚል ምደባውን የተቃወሙ የከተማው ነዋሪዎች ለከተማው አስተዳደርና ለክልሉ መንግሥት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ጥያቄውን እንዲያቀርቡ በተነገረው መሠረት አሥር ተወካዮች መመረጣቸው ከአካባቢው የተገኙ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ከተወካዮቹ መካከል ቀሪዎቹ ለሦስት ቀናት ታስረው አምስቱ በዋስ ሲፈቱ ሌላ አንድ ተወካይ ወጣት ጨምሮ ቀሪዎቹ በእስር እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ ታስረው ከተፈቱት መካከል ሳሙኤል ገብረ መድኅን (የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተወካይ) ኃይሎሽ ሐጎስ (ወዲ አፍሮ – የባዜን ባንድ ሊቀመንበር) ካልአዩ ሕይወት (የአጋርፋ እርሻ ተማሪ)፣ ወጣት ሐፍቶም ገብረ ሕይወትና ወጣት የማነ ዓለም ይገኙባቸዋል፡፡ በአንዳንዶቹ ላይ ግርፋት እንደተፈጸመባቸው ይናገራሉ፡፡ አሁን በእስር ከሚገኙት መካከል ተክሊት አረጋዊ የተባለ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዓመት ተማሪ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለነሐሴ 9 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀጥሯል፡፡ የታሰረበት ምክንያት ሕዝብን ለአመፅ የሚያነሳሳ ግጥም ጽፏል በሚል ነው፡፡ ከተወካዮቹ ውጪ ሌሎች ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ማስፈራሪያ እየተደረገባቸውና ለእስር እየተደረጉ እንደሆኑም የአካባቢው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በቁጥር አሥር የሆኑ የከተማው ሕዝብ ተወካዮች መቀሌ ድረስ በመሄድ ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም በቂ ምላሽ አለማግኘታቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው፤›› መባሉ የበለጠ ቅሬታውን ያባባሰ በመሆኑ ከተማው ውስጥ በዚህ የተነሳ ውጥረት ተፈጥሯል ይላሉ፡፡ የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የከተሞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ መኩሩ ጉዳዩን አስመልክቶ

ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ሐውዜን በአንደኛ ደረጃ በማደግ ላይ ካሉ ከተሞች መካከል ብትሆንም አሁን ከተመረጡት ስምንት ከተሞች መካከል አልተካተተችም ብለዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ሐውዜን በጥንታዊነትም በሕዝብ ቁጥርም ሆነ በሌሎች መስፈርቶች ካለፉት መካከል የተሻለች ብትሆንም በዚሁ የከተሞች ምድብ አልተካተተችም፡፡ በትግራይ 12 ቋሚ አስተዳደር ያላቸው ትላልቅ ከተሞች ሲኖሩ፣ አሁን የተመረጡት እንደነዚሁ የራሳቸው ቋሚ አስተዳደር እንዲኖራቸው ለሙከራ የተመረጡ እንጂ ምንም የደረጃ ልዩነት የላቸውም ይላሉ፡፡ ይኼ አደረጃጀት የመጣውም፣ አንድ ዓይነት የከተማ አስተዳደር ለመፍጠር ከሚደረግ ሙከራ ውጪ ምንም ዓይነት የበጀት ምደባና ሌላ ትርጉም ያለው ልዩነት የለም ብለዋል፡፡ ይህ የሙከራ ጊዜ ለአንድ ዓመት አካባቢ የሚቆይ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ የሐውዜን አስተዳደር ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ሲሞከር ስልክ በመዝጋት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ የሐውዜን ፖሊስና ፀጥታ ኃላፊ ሻለቃ በርሀ ደስታ ግን በእስር ላይ ናቸው የተባሉ ተወካዮችን በተመለከተ፣ ሰዎቹ መታሰራቸውን ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹ የታሰሩበት ምክንያትም በከተማ ደረጃ ላይ መንግሥት ማብራሪያ ሰጥቶ ሳለ ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው ሲንቀሳቀሱና እስከ ገጠር ድረስ ሕዝብ ለተቃውሞ ሲያነሳሱ ተገኝተዋል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ [11 AUGUST 2013 ተጻፈ በ የማነ ነጋሽ] (http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/2868\)

የትግራይ ሕዝብ ይቅር ከሌላው ሕዝብ የተሻለ ነገር ሊኖረው ከዜናው በተጨናጭ ለመገንዘብ እንደሚቻል የትግራይ ሕዝብ ፍትሐዊነት በሌለው የአገዛዝ ስርዓት ውስጥ አንደሚገኝ ለመረዳት ይቻላል። ቀንበር ከበደብኝ ብሎ የታገለ ህዝብ የከፋ ቀንበር በላዩ ላዩ ተጭኖ ሲንገዳገድ እየተመለከትን ነው። ግፍ በዛ ብሎ የታገለ ሕዝብ ይሄ ነው በማይባል ግፍ ሲንገላታ እያየን ነው። ጭቆና በቃ ብሎ ቤት ንብረቱ ጥሎ በርሀ የወጣ ሕዝብ ዛሬ ደግሞ በገዛ አገሩ የግፍ አገዛዝ ሲያደክመው እየሰማን ነው። ታድያ ለዚህ ሕዝብ ድምጽ የሚሆለት ማን ነው? የትግራይ ሕዝብ ግፍ ሌሎች አይመለከታቸውም? ህመምህ ህመሜ ነው፣ ቁስልህ ቁስሌ ነው፣ ውድቀትህ ውድቀቴ ነው፣ ስብራትህ ስብራቴ ነው፣ ሐዘንህ ሐዘኔ ነው የሚል ኢትዮጵያዊነቱን ግድ ብሎት ለግፉዓንን ድምጽ የሚሆን/የሚያስማ የለም? ኢትዮጵያ ሰውም አልወጣልሽ!!

“የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይንና ጆሮ ነኝ” ባዩ ኢሳት የት ገባ? ኢሳት ስለ ሐውዜን ምን አለ? ሕዝብ ወክሎ የላካቸው ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ ስለ ጠየቁ ብቻ “ሌላ አጀንዳ ያላቸው ናቸው” ተብለው ስለ ተገረፉ ስለ ታሰሩ ዜጎች ምን አለ? ኢሳት ስለ ዜጎች ምን አለ?

ሪፖርተር ጋዜጣ “መንግስት በሐውዜን ከተማ በ … ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የጦር መሳሪያ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት በውል መርቆ ከፈተው።” በማለት ቢዘግብ ኖሮ ኢሳት ደግሞ ሪፖርተር ጋዜጣ ዋቢ በመጥቀስ “ሰበር ዜና፡ ታላቂትዋ የትግራይ ሪፕብሊክ ለመመስረት ወደ በርሀ የወጣው የወያኔ/ህወሐት ቡድን በትግራይ ክልል ሐውዜን ከተማ ከ … ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ያስገነባው የከባድ መሳሪያ መገጣጠሚያና ማምረቻ የጦር መሳሪያ ፋብሪካ በዛሬው ዕለት ማስመረቁን ሪፖርተ ዘግቧል። ዝርዝር ይዘናል ይጠብቁን” በማለት እንደሚዘግበው ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። ምንጭ መጥቀስ ሳያስፈልገው “በኤርትራ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አልተደረገም” በማለት የኤርትራ መንግስት ወክሎ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት/ለማስተባበል ነፋስም አልቀደመውም።
ኢሳት የትግራይ ህዝብ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ መዘገብ የማይፈልገበት ምክንያት ልንገርዎት፥

  • “በህወሐት ዘመነ ስልጣን የትግራይ ከተሞች ዕድገት እየደቀቀና እየተቀጨ ነው” በማለት ሪፖርተር ዋቢ አድርጎ መሬት ላይ ያለውን እውነታ መዘገብ ለኢሳት ትልቅ ፖለቲካዊ ውድቀት ነው።
  • የሐውዜን ሕዝብ ሕገ መንግስታዊ መብቱ ተገፎ ታሰረ ተገረፈ በማለት መዘገብ ለኢሳት ውርደት ነው። እንደው የኢሳት ዝምታ የሚያተላልፈው መልዕክት አይደለም ግርፋትና እስራት ለምን ወፍጮ ቤት ወስደው በወረፋ አይፈጩትም ነው!
  • የሐውዜን ከተማ ነዋሪዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተገፎ ተገረፉ ወደ ዘብጥያ ወረዱ በማለት መዘገብ ትግሉን መካድ ነው። ዝምታውም ለምን ዛፍ ላይ ወስደው አያንጠለጥልዋቸውም ነው!
  • “የህወሐት መሪዎች” በትግራይ ሕዝብ ያላቸውን ንቀትና ደንታ ቢስነት መዘገብ ለኢሳት ውርደት ነው።
  • የትግራይ ሕዝብ በገዛ መሪዎቹ እየደረሰው ያለው አስተዳደራዊ በደል መዘገብ ለኢሳት ቀልድ ነው።
  • ኢሳት እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይ ሕዝብ ጆሮና ዓይን መሆን ማለት ኢትዮጵያን መበደል ነው።
  • በአጠቃላይ “የህወሐት መሪዎች” በትግራይ ሕዝብ እያደረሱት ያለው ግፍ መዘገብ የኢሳት አጀንዳ አይደለም።

በሌላ አነጋገር፥

  • የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ አይደለም ነው (በኢሳት እይታ)። ቢሆን ኖሮማ “የኢትዮጵያዊያን ዓይንና ጆሮ ነኝ” የሚለው ፎጋሪው ኢሳት በደረሰለት ድምጹንም ባሰማለት ነበር። ቀላል!
  • ኢሳት የትግራይ ሕዝብ በተመከተ ምንም እንደማይመለከተው ነው።
  • ኢሳት “ኢትዮጵያ እያደማ ያለው” የትግራይ ደም ያለበት ለመቃወም እንጂ የትግራይ ሕዝብ ሰቆቋና በደል ለማሰማት አለመቋቋሙ ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ የሐውዜን ሁኔታ በኢሳት አለመዘገቡ ኢሳት በትግራይ ሕዝብ ያለው መረኑ የለቀቀ፡ ለክ የሌለውና ያመረረ ጥላቻ የሚሳይ ተጨባጭ መረጃ ነው።

በትግራይ ውስጥ የኢሳት ተወካይ/ሪፖርተር የለም። ለምን? ኢሳት ምስጢራዊ ተወካይ/ዘጋቢ ቢያስቀምጥም ኢሳት ስለ ትግራይ ሕዝብ በዘገበ ቁጥር በተለይ በውጭ የከተምን ዜጎች ስለ ትግራይ ሲወራ እንደምንሰማው ሳይሆን በአንጻሩ የትግራይ ሕዝብ በስርዓቱ ዜሮ አምስት ሳንቲም ተጠቃሚ አለመሆኑ ይልቁንስ በአንባገነናዊ ትግርኛ ተናጋሪ ደርግ አባይ ወልዱ አገዛዝ መማቀቁ፡ መድቀቁ፡ ማፈናፈኛ ማጣቱ፡ መገፋቱ፡ መራቡና መቸገሩ፡ በመሪዎቹ ማቆሚያ የሌላው ዲስኩር መዳከሙና መደንቆሩ ነበር የምሰማው። እንዲህ ዓይነቱ ዜና ደግሞ ኢሳትን የሚያዳክም ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ ውስጥ የሚከት ኢሳትን የሚያንኮታኩት ነው። ኢሳት ምስጢራዊ ዘጋቢ/ተወካይ በትግራይ ውስጥ ያላስቀመጠ አቅሙ ስለሌለው ነው በማለት ራስዎን አያታልሉ። ኢሳት ይህን ማደረግ ያልፈለገበት ዋና ምክንያት ስለ ትግራይ ሕዝብ ሰቆቋ መስማት ስለማይፈልግ ብቻ ነው። ይህን ካደረገማ አገር ነጻ ወጣች ማለት።

ጳጉሜ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና  የጎንደር ህዝብ በአስተዳደሩ መማረሩን ገለጸ” ሲል የዘገበው ዘገባ ሙሉ ይዘት ሊንኩት ተከትለው ያንብቡ 

http://ethsat.com/amharic/%E1%8B%A8%E1%8C%8E%E1%8A%95%E1%8B%B0%E1%88%AD-%E1%88%85%E1%8B%9D%E1%89%A5-%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%88%B5%E1%89%B0%E1%8B%B3%E1%8B%B0%E1%88%A9-%E1%88%98%E1%88%9B%E1%88%A8%E1%88%A9%E1%8A%95-%E1%8C%88/

እውነቱ ይህ ነው!
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s