ኢሳት፦ ገጸ ኢትዮጵያውያን፡ ግብረ አረማውያን ወአስመራውያን!

“ከዕለታት አንድ ቀን ዛፎች ከያሉበት ተጠራርተው ስብሰባ ያደርጋሉ አሉ። ጉዳዩም በርካታ ወገኖቻቸው ቆርጦ ቆራርጦ የፈጀ፣ የቀረነውንም ለመጨረስ በሚተጋ በምሳር/መጥረቢያ ዙሪያ ላይ ለመምከር ነበር። ስብሰባው ተጀመረ። ሃሳብ ያለው ሁሉም ተራውን እየጠበቀ እንዲህ ቢሆን የሚለውን አስተያየቱን መስጠት ቀጠለ። ታድያ በዚህ መኸል አንድ ጭምት ጉባኤተኛ “ጌቶች! ምሳሩ ምን አደረገ? የእኛው ጠማማ እጄታ ነው መሳሪያ ሆኖ የምያስቆርጠን: የምያስፈጀንና የምያስጨርሰን ያለ” ሲል በሰነዘረው በሳል አስተያየት ጉባኤው ተስማምቶ በጠማሞች ላይ ውሳኔ በማስተላለፍ ተበተነ” ይላሉ።

ባለፈው ሳምንት በዜጎች መካከል አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው ዳሩ ግን የጥፋት ኃይል መልእክተኛ የሆነ ሽብርተኛ ልሳን ኢሳት በተመለከተ “ኢሳት፡ አማራጭ ወይስ ምላጭ?” በሚል ርዕስ ስር የኢሳት አውዳሚ ማንነት፥ ራዕይ፥ ግብና ዓላማ እንዲሁም ግብዝነት የተሞላበት የግብር ይውጣ ድርጊቶቹ አንስተን በሰፊው መዳሰሳችና የቀረ ደግሞ በቀጠሮ በይደር መለያየታችን የሚታወስ ነው። በዛሬው ዕለት ደግሞ ቀደም ብሎ በክፍል አንድ አንደተጠቀሰ “ኢሳት፦ ገጸ ኢትዮጵያውያን፡ ግብረ አረማውያን ወአስመራውያን!” በሚል ርእስ ስር ሦስት ዓበይት ነጥቦች አተኩረን እንወያያለን። መልካም ንባብ!

ካለፈው የቀጠለ …

ሰውም ሰይጣንም የሚያውቀው የአስመራ መንግስት በእኛ በኢትዮጵያውያን/በሀገራች በኢትዮጵያ ላይ (ስልጣን ላይ ከሚገኘው በኢትዮጵያ መንግስት አላልኩም) ያለው አጀንዳ ይህን ይመላል፦

  • አንደኛ፥ ፖለቲካዊ መረጋጋት የራቀባት በፈንታው ሁከትና ትርምስ የነገሱባት በደም የጨቀየች ሀገር ማድረግ፤
  • ሁለተኛ፥ በኢኮኖሚ ረገድ የደቀቀች፡ ደካማ፡ ድሃና ተመጽዋች ሀገር በማድረግ በኪሳራ ጉድጓድ ውስጥ መጨመር፤
  • ሦስተኛ፥ ሕዝቦችዋ እንደ አንድ ሰው አንድ ልብ ሆነው አንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዳይቆሙ በቋንቋ፥ በነገድ፥ በባህልና በወግ ተለያይተው ከዚህም የተነሳ አፍሪካዊት ማዕከላይ ምስራቅ ማድረግ ከብዙ በጥቂቱ የአስመራ መንግስት ህልምና አጀንዳ ሲሆን ይህን አኩይ ተግባር ተፈጻሚ ለማድረግ/ከግብ ለማድረስ ደግሞ እናት ሀገራቸው ለግለ ጥቅማቸው የሸጡና ለሆዳቸው ባደሩ በኢትዮጵያ ታሪክ የጨለማ ዘመን በመባል የሚታወቀው ወታደራዊ የደርግ ዘመነ መንግስት በካድሬነትና በውትድርና ተቀጥረውና ተሰልፈው ትናንት ሀገርና ሕዝብን ሲያወድሙና ሲያደሙ የነበሩ ጆቢራዎች (የኢሳት ቅጥረኞች) ተግቶ እየሰራ ይገኛል።

የዛሬ “ተንታኞች”፣ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች”፣ “ጋዜጠኞች”፣ “የነጻ ፕሬስ ጠበቆችና የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመገለጽ መብት ጠባቂዎች” ሆይ! እኔምለው ዜጎች የአባታቸው የአያታቸውና የቅምም አያታቸው ስም እየተያየና እየተጠየቁም በወጡበት ሲቀሩ፤ ዜጎች አይደለም የመሰላቸውን ተናግረው ወደ ቤታቸው በሰላም ሊሄዱ ይቅርና “ቤተስኪያን” ለመሳም የፈቃድ ወረቀት ጠይቀው በሚሄዱበት ዘመን፤ ወታደራዊ የደርግ መንግስት ለ17 ዓመታት ኢትዮጵያውያን ደም እያስለቀሰና እያስተፋ ሲገዛው በምን ዓይነት የስራ መስክ ተሰማርታችሁ ኑሮአችሁን ትገፉ ነበር? የት ነበራችሁ? ጥያቄዬ ግልጽ ከሆነ በምን ዓይነት የስራ መስክ ተሰማርታችሁ ጉሮራችሁን ትደፍኑ ነበር? በኢትዮጵያ ስለ ሰብዓዊ መብት መረገጥ ስትናገሩ፣ ስለ ነጻ ፕሬስ መታፈን የደርግ መንግስትን ስትሞግቱ? ወይስ የገዛ ወገናችሁ እንዴት ማሰቃየት፡ አንገቱን ማስደፋትና ከዚህ ያለፈ ደግሞ እንደ ፋሲካ በግ ያለ ርህራሄ ደሙን ለማፍሰስ የሚያችል የካድሬ

ትምህርትና ስልጠና ወስዳችሁ ስትገድሉና ስታስገድሉ፣ ስታርዱና ስታሳርዱ ነበር? በነገራችን ላይ ወታደር መሆን ማለት በራሱ ምንም ዓይነት ነውር የለውም። ጥያቄው የለበሳችሁት ካኪና የታጠቃችሁት መሳሪያ በወቅቱ ማን አተረፋችሁበት? ለማን ቆማችሁ? የኢትዮጵያ ሕዝብ አተረፋችሁበት ወይስ … ? ነው ጥያቄው። ረዥሙን ታሪክ ለማሳጠር ያክል የኢሳት ቅጥረኞች ትናንት የኢትዮጵያውያን ነፍስ እንደ ድንች በፈላ ዘይት ሲቀቅሉ የነበሩ ግለሰቦች ዛሬ ደግሞ አሜሪካና አውሮፓ መሽገው የኢትዮጵያ ሕዝብ በወሬ ቢቀቅሉት ምን ይደንቃል?

እስቲ ይታያችሁ፦

  • በእጁ ደም ያለበት ሰው ስለ ዲሞክራሲ፡ ስለ ፍትህ፡ ስለ ነጻነትና ስለ እኩልነት አፉ ሞልቶ ሲናገር።
  • ይታያችሁ የደርግ ወታደርና ካድሬ ነበር ስለ ሰብአዊ መብት አያያዝ ሲሞገት፤ ሌሎችንም ሲያወግዝና ሲኮንን። የሰው ያለህ!

በዚህ አጋጣሚ ራሳቸው በተቃዋሚ ጎራ መድበው በመሪነት ስለምናውቃቸው አንዳንድ ተዋቂ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከመጋረጃ በስተጀርባ ተደብቀው ስለሚጫወቱት የፖለቲካ ቁማር አንድ ነገር ልበል። ይኸውም፦ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች (ሁሉን በደፈናው አላልኩም) ታዋቂነት መነሻው ግለሰቦቹ የላቀ ፓለቲካዊ አስተሳሰብና አመለካከት ኑሮአቸው ሳይሆን ሰዎቹ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ አፍስሰው ቢጤዎቻቸው በማሰማራት የሌላቸው ማንነትና አቅም እንዳላቸው በማስመሰል ስለ ራሳቸው በሚያስነፉት መለከትና በተጨማሪም በተቀናጀ መልኩ በኢሳት በኩል በሚያሰራጩት ፕሮፖጋንዳ ለመሆኑ ያውቁ ኖሯል? እስቲ ራስዎን እንዲህ በማለት ይጠይቁ “ወንደሩ ላይ የተቀመጡ የኢህአዴግ ባለ ስልጣናት ያልተማሩና መሃይማን ከሆኑ ራሳቸውን እንደ አዋቂዎች የሚቆጥሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች በአንድ የሙሉ ሰው ዕድሜ ውስጥ (በሃያ ዓመት ውስጥ) የደንቆሮውን ወንበር መገልበጥ እንዴት ተሳናቸው?” በማለት ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ? በእርግጥም የእኛዎቹ “አዋቂዎች” በነጋ በጠባ ቁጥር አስቸኳይ የስብሰባ ጥሪ ከመጥራትና ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠት ያለፈ ፋይዳ ያለው ስራ መስራት ተስኖአቸው ሲልፈሰፈሱ ሲመለከቱና ይባስ ብሎም ፖለቲካዊ ምሪትና መመሪያም ከሕዝብ ሲጠብቁ ሲያዩ “ነገሩ እንዴት ነው የእኛዎቹ ምሁራን ትምህርት “ከደንቆሮዎቹ” የኢህአዴግ ባለ ስልጣናት ድንቁርና በምን ተሻለ? በማለትስ የሚሰሙትን ሁሉ ለመመርመር ሞክረው ያውቃሉ ወይ? ያለፈ አልፈዋል ከእንግዲህ ወዲህ ግን ከነፈሰ ጋር ላለመንፈስ ሀገርዎንና ሕዝብዎን ከሐሰተኞችና በላተኛ አውሬዎች ለመጠበቅ ምን ያህል ዝግጁ ኖት? ሦስት የኢሳት የስራ ድርሻና ግዴታዎች በአጭሩ ላስቀምጥና ጽሑፌን ልቋጭ።

ሦስት የኢሳት የስራ ድርሻና ግዴታዎች፦

  • አንደኛ፥ ከበላይ ተቀምጦ ተቋሙን የሚዘውረው አካል በጠላትነት የሚፈርጃቸው የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች ስም ማጉደፍና ማጥፋት፤
  • ሁለተኛ፥ ጨርሶ የሀገሪትዋ ነባራዊ ሁኔታ ባገለለ መልኩ ሆነ ተብለው ሕዝብን ለማሳሳት በቀመር ተሰልተው በሚፈበረኩ ዜናዎችና ሐተታዎች ሕዝብን በፈጠራ ወሬ ማወክ፡ ማደናገርና ውዥንብር ውስጥ መክተት፤
  • ሦስተኛና የከፋው የዚህ የፕሮፖጋንዳ ማዕከል ዋና ተግባር ቀደም ሲል እንደተመለከትነው አንዳች የረባና ውጤታማ ስራ ሰርተውም ሆነ አከናውነው የማያውቁ ግለሰቦች የሌላቸውን አቅም ስማና ችሎታ አየሰጠ: አየለጠፈና አየሾመ ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ማስተዋወቅና መሸጥ የኢሳት የዕለት ተዕለት የስራ ድርሻና ግዴታዎች ናቸው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s