ኢሳት፡ አማራጭ ወይስ ምላጭ?

ምዕራባዊያን መንግስታት በአንድም በሌላም መንገድ ምድራቸው ለተጠለለ ሕጋዊ የውጭ ዜጋ ራሱን ችሎ ይቆም ዘንድ ከሚሰጡት ዕድል መካካል አንዱ ክፍት የስራ በር ሲሆን ይኸውም ስራ ሳያማርጥ፥ ሳይንቅና ማንኛውም ዓይነት ስራ የመስራት ፍላጎት እንዲሁም የልብ ተነሳሽነት ላለው የምድር ዜጋ ሁሉ እንደ ደረጃው ማለትም ትምህርት ያለው በተማረው የትምህርት ደረጃ መሰረት፥ ሞያ ያለው በሞያው፥ ሌላው ደግሞ እንዲሁ አቅሙ በፈቀደው የስራ መስክ ተሰማርቶ ራሱንና ቤተሰቡን ያስተዳድር ዘንድ በሮቻቸው ክፍት ነው። የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ወገኖች የሞት ያክል ዋጋ ከፍለው: ተላልጠውና ተሸራርፈር አሜሪካና አውሮፓ ደርሰው ሲያበቁ አገሮቹ የሚሰጡት ዕድል ለመጠቀም ፍላጎትም ሆነ ተነሳሽነት ሳይኖራቸው ሲቀሩ እጅግ ያሳዝናል። ሰው ስራ ሰርቶ ሙሉ ሰው በሚሆንባቸውና ራሱን በሚለውጥባቸው አገሮች ተቀመጦ ሲያበቃ የዕድሉ ተጠቃሚ ሳይሆን መቅረቱ ብቻ ሳይሆን ስንፍናው ለሌላ ታታሪ ሰራተኛ ዜጋ ጭምር የሚተርፍ በሽታ/ጦስ ሆኖ ከማየት በላይ የልብ ስብራት የለም።

 ያለ ምክንያት ስለ ስራ ክቡርነት አንስቼ አልሞገትኩም። ስራ ክቡር ነው። ምን ይሁን ምን ሰውን ሰው የሚያደርገው፥ የሰው እጅ ከመጠበቅም የሚያተርፈው ስራ ነው። በአንጻሩ ግን ከለንደን እስከ ዋሽንግተን ዲሲ ጸብ፥ ጥፋት፥ እልቂትንና መለያየትን እንጂ አንዳችም የሰውን ህይወት የሚገነባ፥ የሚለውጥ፥ መልክ ያለው፥ የሚያንጽና የሚረባ መልእክት የማይወጣቸው በአንጻሩ አፍራሽ አጥፊና አውዳሚ የነገር መስመር ዘርግተው ወሬ ሲፈትሉና ሲያቀጥኑ ጸሐይ የምትጠልቅባቸው ግለሰቦች የዕለት ዕለት ድርጊቶቻቸው ስመለከት በሰልቃጭ ማላሶቻቸውና መንታ አንደበቶቻቸው የሚሰለበውን ንጹሕ ዜጋ እየታየኝ እያሳሰበኝም በርካታ ጥያቄዎች ወደ አእምሮዬ ስለሚመላለስ ነው።

አንዳንድ ጊዜም እንዲህ እላለሁ: በእውነቱ ነገር ሰዎቹ ዋጋ የሚያወጣ አእምሮ ካላቸው እንዲህ ባለ በታሪክ የሚያስጠይቅና ትውልድ የሚያፍርበት ስራ ተሰማርተው ሀገራቸውን ከሚበድሉና ሕዝባቸውንም ለጊዚያዊ ጥቅም ሲሉ ብቻ የፈጠራ ዜናዎችና ሐተታዎችን በማሰራጨት ሕዝብ ወዳልሆነ አቅጣጫ እንዲያመራ በማድረግ እርስበርስ እንዲተላለቅና እንዲጨራረስ ከማድረግ ይልቅ ምን አለበት አቅማቸው በፈቀደው የስራ መስክ ተሰማርተው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ቢረዱ እላለሁ። ከተሳሳትኩ ከስህተቴ ለመታረም ዝግጁ ነኝ! በተረፈ ግን ጋዜጠኝነት ሞያ መሆኑ ቀርቶ ስራ ሰርተው ኑሮአቸውን መግፋት የማይፈልጉ የስራ ፈቶች መደበቂያ ዋሻ ከሆነና መስራት የማወድ ተለላ ሁሉ በጋዜጠኝነት ስም ያለ እውቀት ምክርን የሚያጨልም ከሆነ ሀገርንና ሕዝብ እስከ መቼ በነፈዞች ይታወካሉ? በማለት የመጠየቅ መብቴ የተጠበቀ ነው።

 • ኢትዮጵያ ለመበታተን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አብረው ሲያበቁ ኢትዮጵያውያን፤
 • የግል አጀንዳ ያላቸው በምኞት የተቃጠሉ ጥመኞች ሳሉ የሕዝብ (ሕዝባውያ)፤
 • ምድሪቱ የደም መሬት ሕዝቦችዋንም በደም ለመቃባት አፋቸው የከፈቱ የበልዓም ምክር አስፈጻሚዎችና ተራጋሚዎች ሆነው ሳሉም ነጻ: ገለልተኛና ፍትሐዊ የሚሉ የሸቀጥ ታፔላዎች ግንባራቸው ላይ ለጥፈው የተሰለፉ ስተው የሚያስቱ የምላስ አርበኞች በኢሳት ቅጥረኞች ላይ ያለኝ ጥያቄ እንደቀጠለ ነው።

ይህ ራሱን “ነጻ፥ ገለልተኛና ፍትሐዊ ኢትዮጵያዊ ሚድያ ነኝ” በማለት የሚጠራ አፈ ለምጽ ለበርካታ ጊዜያት ሀገር ወደ አላስፈላጊ ትርምስና ብጥብጥ ለመክተት ያደረገውና የሚያደርገውን ዘመቻ እንድያቆም ከድርጊቱም እንዲቆጠብ በተደጋጋሚ ጊዜያት በግልም በአደባባይም የቀረበለትን ጥያቄ አሻፈረኝ በማለት በሕዝቦች መካከል ጥላቻንና አመጻን መዝራት እንደገፋበት ይገኛል።

ኢሳት ምንም እንኳ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይንና ጆሮ ነኝ” ከማለት ባይመለስም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ተቋሙ የኢትዮጵያውያን ዓይንና ጆሮ ለማጥፋት ብሎም ለማደንቆር ያሰፈሰፈ የኢትዮጵያ መልካምነት ማየት የማይሆንላቸው ሃይሎች ክንፍ ለመሆኑ ለብዙዎቻችን ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁ።

ሌላ የዚህ ተቋም ጉራማይሌ ገጽታው እንደሚከተለው ይመስላል። የራሱ ማንነትና የተገለጠ ጸረ ዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ አሰራር ለማድበስበስ ኢቲቪ: ፋና ሪድዮ: አዲስ አድማስና ሪፖርተር እያነሳ ሲጥል ኢሳት ማለት ግን በአንጻሩ ቀዳሚና ተከታይ የሌለው ብቸኛ የነጻ ፕሬስ ተሟጋችና ጠበቃ አድርጎ ለማቅረብ የሚያደረው ጥረት ነው። ኢሳት ስለ ነጻ ፕሬስም ሆነ የዜጎች ሃሳብህን በነጻ የመግለጽ መብት በተመለከተ አፉን የመክፈት፥ የመናገር የሞራል ብቃት የለውም። ይህ ብቻም አይደለም ኢሳት የሚወቅሰው አካል የለም! ሊኖርም አይችልም! አይኖርምም። የዜጎችን ሃሳብ በነጻነት የመግለጽ መብት በመገደብና በማሳጣት እንዲሁም የነጻ ፕሬስ አፈና በተመለከተ ከኢሳት የከፋ አፋኝ ጸረ- ነጻነት አለ ብለው ራስዎ አያታልሉ። አለ ብለው የሚያምኑ ከሆነም መቀመጫው ሲዖል ያደረገ ስለ ናዚ (Nazi) ሊቀ መንበር እየተናገሩ እንደሆኑ እርግጠኛ ይሁኑ።

ለመሆኑ ነጻ: ገለልተኛና ሚዛናዊ ሚድያ ማለት ዜጎች በዜግነታቸው (ያለምንም ቅድመ ሁኔታ) ሃሳባቸውን ያለገደብ በነጻነት የሚያነሸራሽሩበት የሕዝብ መድረክ መሆኑ ቀርቶ ግለሰቦች በፈላጭ ቆራጭነት ሌላውን የሚሳለቁበት ማለት ነው ያለ ማን ነው? ማን ነው ኢሳት ነጻ: ገለልተኛና ሚዛናዊ ሚድያ ብሎ ለመናገር የሚደፍር? አእምሮውን ያጣ ግለሰብ ካልሆነ በስተቀር። እንግዲያውስ ኢሳት ማለት ሌላ ማንም ሳይሆን ሀገርንና ሕዝብን ለመበተን አፉ የከፈተ የዘንዶ ምላስ ነው!

ኢሳት ቅንጣት ታክል ኢትዮጵያዊ ራዕይና ዓላማ የሌለው ይልቁንስ የኢትዮጵያ ጠላቶች አፍ እንደሆነም ጭምር በተጨባጭ  ከዚህ ቀደም በበርካታ ጽሑፎቼ በስፋትና በጥልቀት ግንዛቤ ማስጨበጤ የሚታወስ ነው። በእርግጥ የኤርትራ መንግስት ጦር አዝምቼ ኢትዮጵያን እገጥማለሁ አፈራርሳለሁ ብሎ በህልሙም ጭምር እንደማያስበው የሚጠራጠር ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላምንም። ኩሽታ ያሰማ ዕለት እንደሆነ ያለቀባሪ በቆፈረው ጉድጓድ ራሱን እንደሚጨምር የአስመራ ባለስልጣናት ለአፍታ አይስቱትም። ታድያ “ኢትዮጵያዊ አማራጭ ሚድያ” በማለት ራሱን የሚጠራ ኢሳት በመባል የሚታወቀው የሳይበር ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የአቶ ኢሳይያስ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሕልም ተለዋጭ ምላጭ ለመሆኑ የሚጠራጠር ማን ነው?

ምላጭ የሚቆርጥ፥ የሚያደማ፥ የሚለያይ፥ የሚከፋፍል፥ የሚቀድና የሚበሳሳ ስለታም መሳሪያ ሲሆን ኢሳት ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብና ምድር ክብር፦

 • ለመግፈፍ፥
 • ለመላጨት
 • ለማራቆት፥
 • ለማርከስ፥
 • ለማድማት፥
 • አንገት ለማስደፋት፥
 • ለማሸማቀቅ፥
 • ለማዋረድ፥
 • ለማለያየትና ለመከፋፈል በእደ ግንቦት 7 ወኢሳይያስ/ህግደፍ የተዘረጋ ምላጭ ነው። ጥያቄ ያለው ማቴ 7፥ 17 በማንበብ መልሱን ያገኘዋል።

“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።” (ማቴ 7፥ 17)

ወገን፡ መጽሐፍ ሲናገር እውነት ነው! መጽሐፍ ሲናገር ግልጽ ነው! መጽሐፍ ሲናገር ትክክል ነው! ኢሳቶችም ፍሬአቸው፥ ምኞታቸውና ግብራቸው ነው ሞራለ ቢሶች ግብረ አረማውያን ወአስመራውያን እንጅ መልካቸው: ቋንቋቸውና ዜግነታቸውማ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰ የኤርትራ መንግስት እንደሆነ ቃኘው ቁጭ ብሎ በድምጺ ሐፋሽ ኤርትራ የሬድዮ ጣቢያና በERTV በኩል በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የፈለገውን ዜና እየሰራ ሲለፈልፍ ውሎ ቢከርም ማንም የሚሰማው የለም። ማን ይሰማዋል? ማንስ ጆሮ ይሰጠዋል? ማንም። ለምን? የኤርትራ መንግስት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ጥይት አንጂ ዳቦ እንደማይመኝልን ዜጋ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነውዋ። ምንስ እንዲል ይጠበቃል? የኤርትራ መገናኛ ብዙሐን ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መልካም ነገር ይዘግባሉ ብሎ የሚጠብቅስ ማን ያበደ ነው? የኤርትራ መንግስት ግን በዚህ ሁሉ ተስፋ አልቆረጠም። ይህ መንገድ አልሆነልኝም አልተሳካልኝም ብሎም እጁና እግሩ አጣጥፎ አልተቀመጠም። ይልቁንስ በልኩ ያሰፋው አፍ በኢሳት በኩል ሀገራችን ሲወጋ: ሲያደማ: ልዩነትንና ጸብን/ሁከት ሲዘራ እየተመለከትነው ነው። እስከ መቼ? ለሚለው ጥያቄ “ለሀገሪቱ ባለ ስልጣናት” (ለኢትዮጵያ ባለ ስልጣናት) የሚተው ጥያቄ ይሆናል።

እኔምለው ሰው እንዴት ይህን ያህል ይጨልምበታል? እንዴት ይህን ያህል አእምሮ ቢስ ይሆናል? በነጋ በጠባ ቁርጥ እንዴት ሁከትና ረብሻን ለመቀስቀስ እንቅልፍ ያጣል? አንዳንዱማ በህወሐት የውሃ ጥምቀት የተጠመቀ ነው የሚመስለው። ያለ ህወሐት ሌላ አፍ መውጫ ቋንቋ የለውምና። አረ መቼ ነው ኢሳት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያን የሚረባ: የሚገነባ: አንድ የሚያደርግና የሚያንጽ ቃል ከአፉ የሚወጣበት? መቼ ነው ኢሳት ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገር የሚናገረው? አንዲት ቀን ተሳስቶም ኢሳት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ የሚያሳርፍ፥ ሰላማዊና መልካም ዜና ላለመዘገብ ሰዎቹ በልጅ ልጆቻቸው ተማምለዋል ልበል? እንዴት በ 1100 ቀናት ውስጥ አንዲት ቀን አንዲት መልካም ነገር መናገር ይሳናቸዋል? ለነገሩ መጽሐፍ “ከእሾህ ወይን ከኩርንች በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም።” ብሎ የለም። ለነገሩ ኢሳቶች ተሳስተው ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገር የተናገሩ ዕለት ነው የሚደንቀኝ።

ይቀጥላል …

የዛሬ ሳምንት:

 • ሰውም ሰይጣንም የሚያውቀው የአስመራ መንግስት በሀገራች በኢትዮጵያ ላይ ያለው አጀንዳ፤
 • ትናንት የሰው ነፍስ አንደ ድንች በዘይት ሲቀቅሉ የነበሩ የዛሬ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች”፣ “ጋዜጠኞች”፣ “የነጻ ፕሬስ ጠበቆችና የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመገለጽ መብት ጠባቂዎች” በቀድሞ የደርግ ወታደራዊ መንግስት የስራ ድርሻ እንዲሁም
 • ሦስት ዋና ዋና የኢሳት የስራ ድርሻዎችና ግዴታዎች አንስተን በጨለማ ላይ ብርሃን እናበራለን ይጠብቁኝ!

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s