አፋልጉኝ! ታማኝ በየነን ያያችሁ፡

ባሳለፍነው ሳምንት “አርቲስት ታማኝ በየነ ወዴት አሉ? ጃዋር መሐመድ ይፈልጎታል” በሚል ርዕስ ከቀረበ ጽሑፍ የቀጠለ።

ታማኝ ሆይ! ህወሐትና መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር የምታጠቃበት የተለየ ምክንያት ከሌለህ በስተቀር (ጸረ አማራ ናቸው የሚለው እምነትህ እንደተጠበቀ ሆኖ) ኢትዮጵያ ማን ናት? መቼና በማን ተመሰረተች? ኢትዮጵያዊነትስ ምንድ ነው? ኢትዮጵያዊስ ማን ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ጃዋር መሐመድ የተባለ ግልሰብ ፊት ቀርበህ መልስ እስካልሰጠህ ድረስ በግልሰቡ እምነትና አመለካከት እንደ ተስማማህ ነው የሚገባኝ። ኢትዮጵያ ተብላ ስለምትታወቀው ሀገር እኛ አዲሱ ትውልድ የትኛው ትርጉምና ትንታኔ እንቀበል? የህወሐት እንዳንቀበል “ህወሐት ሀገር ለመበታተን የፈጠረው አዲስ ታሪክ ነው” አልከንና ምንም እንኳ ንግግርህ በመረጃ ወይም ጭብጥ ላይ የተደገፈ ባይሆንም ብቻ ግን የሀገሬ ሰው “ሰው ሲታጣ ይመለመላል ጎባጣ” እንዲል አንተን አምነን ተቀበልን።

ከጎንህ ተሰልፈን ህወሐትን ስንዋጋ ደግሞ ዛሬ ላይ ደረስን። አሁን ደግሞ ከመዓድህ የተካፈለ ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ ተነስቶ “የለም! ኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት ታሪክ ያለፈ ታሪክ የላትም። ኢትዮጵያ ቀደም ብለው ራሳቸውን ችለው ራሳቸው በራሳቸው ያስተዳድሩ የነበሩ ሕዝቦች (መንግስታት) በመጨፍለቅ ከአማራ ወገን የሆነ ምኒሊክ በጉልበቱ የፈጠራት የአማራ መገለጫ ናት። አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ በከፊል የትግራይ። ኢትዮጵያ ኦሮሞን አትወክልም። ኦሮሞ ራሱ የቻለ መንግስትና ስርዓት የነበረው ሉዓላዊ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ኦሮሞም ሆነ ወላታ ከምባታም ሆነ ሀዲያን አትወክልም። የኦሮሞ ጉዳይ ከ ፶ ዓመት በፊት የተነሳ ጥያቄ ነው።” እያለ ሲባርቅብን አይ! ለዚህ ለዚህማ ታሪክ ባይማርም፣ ፖለቲካ ባያውቅም፣ የኮሌጅ ዲግሪ ባይኖረውም፣ ባመነበት ለወሰነ፡ ወስኖ ለሚሰራ፡ ለሚሰራው እምምምም “የማይፈራ” የምትለዋን እንኳን ስለማትዋጥልኝ “በምርጫ” በሚል ተክቻታለሁ፡ ሲያወራ ከመቀስ ጋራ የመድረክ ሰው አርቲስ ታማኝ በየነ ፍቱን መድኃኒት አለን በማለት ስንጠብቅ የገባህበትም ለማወቅ አልተቻለም። ያንተ መጥፋት ብቻም ሳይሆን “የኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይንና ጆሮ ነኝ” ባዩ ሀገር በታኝ ትውልድ ገዳይ የሳይበር ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ጭጭ ብሎ መጥፋቱም የስታንፎርድ ጥይት ማን ሰራሽ ቢሆን ነው? አስብለዋል።

ለመሆኑ ታማኝ ይህን ሁሉ ዓመታት መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር በረገጥክበት ምድር ስትረግማቸው የኖርከው “የት ያገኙኛል እኔ የምኖረው አሜሪካ እሳቸው ያሉ ኢትዮጵያ” ነበር ብልሃቱ? ቢሆን ነው እንጅ ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ ጆሮህ ላይ ቆሞ ይህን ሁሉ ሲል በአማራ ጠላትነት ፈርጀህ “ምን አልክ አንተ … ” በማለት ቃል ለመተንፈስ አልደፈርክም። አሁን አንተ የተፈለግክበት ዋና ምክንያት ማንን እንስማ? ለሚለው የእኛ የአዲሱ ትውልድ ጥያቄ መልስ እንድትሰጥ ነው። በነገራችን ላይ ሙሑራዊ ትንታኔ እንድትሰጥም ሆነ ጥናታዊ ጽሑፍ እንድታቀርብ የሚጠብቅ ሰው ያለ አይመስለኝም። እኛም እንደሆን ያልሆንከውን ሁን በማለት ይህን ታደርግ ዘንድ አናስገድድህም ቢሆንም ግን በሞዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተርና በሊቀ መንበርነት ይመሩት የነበርውን ህወሐት ያየነው፣ የምናውቀው፣ “ያንጨበጨብንለትና አድናቆታችንን የቸርንለት” ታማኝ በየነ አሁን ደግሞ አሮሞ ነኝ በሚል በጀዋር መሐመድ ማየት ስለሚፈለግ ነው። እንግዲያውስ ማንን እንስማ? አርቲስት ታማኝ ዓቅምህን መዝነህ ተወኝ የለሁበትም ካልክ ዘንዳ ታድያ ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ እንስማ ወይስ ሌላ የሚመጣ ሰው አለ? 

ወደ ቀጣዩ ክፍል ከማለፌ በፊት ለፈገግታ ያክል ከቀልዶችህ መካከል ለዛሬ አንድ ለአንባቢያን ላቅርብ።

“በአንድ ወቅት አዲስ አበባ ስቴድየም አንድ “ሾው” አዘጋጅተን ስንሰራ እነሱ በየጊዜው ገደልን የሚሉትን ቁጥር ደምሬ አረ ይሄ ነገር ከሚቀጥለው ትውልድ ሁሉ ተበድረን ሞተናል ብዬ ቀልድ ሰርቼ ነበር።”

ቀልዱ ያልገባቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ብዬ ስለምገምት ቀልዱ በጨወታ መልክ አብራራው ዘንድ ይፈቀድልኝ። አንድ ሰራተኛ የስራ ድርሻውን በአግባቡ ካልተወጣና በሰዓቱ በስራ ገበታው ካልተገኘ/የማይገኝ ከሆነ ማግኘት የሚገባውን እንደማያገኝ ሁሉ ቀልድ መቀለድ ለታማኝ በየነ ጎሮሮው እንጀራውም ነውና እዚህ ላይ ጥያቄ ያለው ሰው ያለ አይመስለኝም። የህይወት ጉራማይሌነት ያልገባው ደጉ ሳምራዊ ካልሆነ በስተቀር።

በእርግጥ ታማኝ ይህን ቀልድ የቀለደበት ዓመተ ምህረት አልነገረንም። ያልተናገረበትም በምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ። ቀልዱን የቀለድከው ከመታሰቤ በፊት ሊሆን ይችላል። ወላጆቼ ከተጋቡ በኋላ የሆነ እንደሆነም ከመወለዴ በፊት ሊሆን ይችላል። ከተወልድኩ በኋላ የሆነ እንደሆነም ከመጠመቄ በፊት ይሆናል ካልሆነም እግር ከመትከሌ/አፌን ከመክፈቴ በፊት ሊሆን ይችላል። ቀልዱን የቀለድከው ፊደል ከመቁጠሬ/መዋዕለ ህጻናት ከመሄዴ በፊት እንደሆነ ግን በእርግጠኝነት ለመናገር ይቻላል (ዝርዝር ውስጥ መግባት ያስፈለገኝ ወደኋላ አከባቢ ለማነሳቸው ጥያቄዎች አንተስ የት ነበርክ? እንደምትለኝ ስለማልጠራጠር ነው።)

አንድ ደስ የሚለኝ ጸባይ አለህ። ይኸውም፥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አስበህበትም ሆነ እንዲሁ ከአፍህ አምልጦህ ሳታስበው የሚሆን ለመሆኑ በእርግጠኝነት ለመናገር ባልደፍርም እንዲሁ ግን አንዳንድ ጊዜ ማንነትህን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ (የማንነትህ መገለጫ) ከመናገር ራስህን አትቆጥብም። በደርግ ዘመነ መንግስት “ዝመት በለው ሲባል በደንብ እስክስታ እየወረድን በለው አይዞህ ብለናል” ስትል በዚያን የጨለማ ዘመን የስራ ድርሻህ ምን አንደነበር ተናግረኸል። በበኩሌ በደርግ ዘመን የነበረህ የስራ ድርሻም ሆነ ስለማንነትህ ከራስህ አንደበት ባልሰማ ኖሮ ሌላ ሰው ቢነግረኝ እውነት ነው ብዬ ያለማመንም ያለመቀበልም አቅሙ አለኝ። የገረመኝ ግን (አንተ ራስህም አንደምትለው) በአሁን ሰዓት በፖለቲካ እውቀትህ ሳይሆን በተጫዋችነትህ ብቻ ሕዝብን ማስተባበር ዓለምንም መዞር ከቻልክ በዚያን ዘመን ገዳዮችን ከማዝናናት ይልቅ ሞያህ “ግፍ በቃ!” ለማለት የደርግ መንግስት በማውገዝ ሰብዓዊነትህ ለተገፊዎች ሳታሳይ በመቅረትህ በቀላሉ የሚታለፍ ጥያቄ አይሆንም። በነገራችን ላይ፦

  • የደርግ መንግስት ሕዝብ ሲጨፈጭፍ፣ ሲያርድና የሰው ነፍስ አንደ ድንች በፈላ ዘይት ሲቀቅል የደርግ መንግስት አቋም በመደገፍ የሆንከውን የሆንከው እየተቃወምኩ አይደለሁም። መብትህ ነው!
  • የደርግ ወታደር አንድን ሕዝብ እንደ ሲጋራ ሲያጨሰው ቀልድ መቀለድ እንጀራህ ነበርና አንተ ቀልድ ትቀልድ ነበር። መብትህ ነው! 
  • የደርግ መንግስት ሰለባ የነበረ ሕዝብ የደም ዕንባ እያነባ ሲያለቅስና ሲጮህ ቀለብ የሚሰፈርልህ ነፍሰ ገዳዮችን በማዝናናት ነበርና  አንተ ደግሞ ያን ጊዜ ቀልድ በመቀለድ  እንጀራህን ትጋግር ነበር። መብትህ ነው! 
  • ታማኝ በዚያን ጊዜ ከሚያዝኑ ማዘንን ከሚያለቅሱ ደግሞ ማልቀስን ያልወደድከው ተገፊዎቹ ከአንተ ጋር ምንም ዓይነት የደምና የስጋ ዝምድና ስሌላቸው፣ በቋንቋ፣ በባህልና በወግ ስለማይመስሉህ ከሆነ መብትህ ነው! 

 ቀልዱን እዚህ ልግታውና ወደ ቁም ነገሬ ልለፍ። በደቡብ አፍሪካ ጉዞህ እንዲህ ብለህ ነበር “ዛሬ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም ሊሉን የሚፈልጉት ታሪካችን እንዳናይና በጥላቻ ብቻ እንድንተሳሰብ ስለ አደረጉን ነው” አክለህም “አዲስ የተዘራ የዘር ፖለቲካ ያጣላናል እንዴ?” በማለትም ትጠይቃለህ።

እስቲ አሁን ደግሞ ጀዋር መሐመድ የተባለ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ግለሰብ በቅርቡ ከኢትዮ ቲዩብ ባደረገው ቃለ ምልልስ ባነሳኸው ጉዳይ ላይ የሚለውን አብረን እንመልከት።

የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ጀዋር መሐመድ እንዲህ ይላል “የኦሮሞ ማንነት ኦሮሞ ነው። ኦሮሞ የራሱ ባህል አለው የራሱ ታሪክ አለው የራሱ የሚገለጽበት ስነ ልቦና አለው ማለት ነው በተለየ የራሱ የሆነ በቂ መገለጫ ማንነት አለው። አሁን የምናውቃት ዘመናዊ ኢትዮጵያ የዛሬ መቶ ዓመት ምናምን ነው በምኒሊክ ነው የተገነባችው። ምኒልክ ደግሞ ማን እንደሆነ: የማን ቤዝ ይዞ እንደመጣ: የማን ጦር ይዞ እንደመጣ የታወቀ ነው።” አክሎም “አሁን ባለው እኔ ኦሮሞ ነኝ። እኔ መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ አሁንም። አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ የኔን ዓይነት ሰዎችና የኔን ማንነት ኢንተርተይን ሊያደግ የሚችል ዓይነት አይደለም። ራሴን በዛ ውስጥ ማየት አልችልም። በማንነት ደረጃ ከመጣህ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ማንነት ተብሎ የሚቀርበው ነገር እኔን ሊወክለኝ አይችልም። ሁለተኛ ማንነት እስከሌለ ድረስ ዛሬም ነገም ወደፊትም የኔ ማንነት ኦሮሞ ነው።” ታማኝ በየነ ጽሑፉ በደንድ የሚነበብልህ ከሆነ “ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ አይደለም! እኔ ኦሮሞ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም!” አያለ ያለው የአማራ ወይንም ደግሞ የትግራይ ተወላጅ ካድሬ ሳይሆን የኦሮሞ ተወላጅ ግለሰብ ነው።

አንደው የመድረክ ሰው ታማኝ በየነ ከእስላምም በላይ እስላም ከኤርትራዊውም በላይ ኤርትራዊ መሆን ስለሚቃጣህና ስለሚቀናህ ነው እንጅ ታሪካችንም ካስፈለገ ይሄው ይህን ይመስላል እያለ ነው የኦሮሞ ተወላጅ ግለሰብ ጃዋር መሐመድ “ኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብና በተለይ የአማራና የትግሬ ኃይል ለአምስት መቶ ዓመት ሲዋጋና ሲጋጭ የነበረ ነው። በእነዚህ ግጭቶች ውስጥ የተገነቡ በጣም ጸረ ኦሮሞ የሆኑ አመለካከቶች አሉ። መጀመሪያ ካውንተር ላይ አስራ ስድስተኛ ክፍለ ዘመን ኦሮሞን እንደ አረመኔ እንደ አውሬ የማየት ሂደት ነበር። ከዛ የኦሮሞ ኃይል ከተሸነፈ በኋላ ደግሞ ኦሮሞ በቃ በጣም ኢንፊሬር በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ የሚያቀርብ ሊትረቸር ታያለህ።”

“አዲስ የተዘራ የዘር ፖለቲካ ያጣላናል እንዴ?” በማለት ላነሳኸው ጥያቄም ይህ ግልሰብ ለአንተ መልስ አለው  “እነዚህ ዛሬ የምናነሳቸው ጥያቄዎች የዛሬ የዛሬ ፶ ዓመት የተነሱ ናቸው” ይላል። ይህ ማለት ህወሐት ወደ በርሀ ከመውጣቱ ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት መሆኑ ነው። በነገራችን ላይ ሰዉ ቅዳሴ ሰምቶ ወደ ቤቱ የመመለስ ያህል የሰማውን የሚጠይቅ ሰው ባለመኖሩ በስህተት ላይ ስህተት በበደል ላይ በደል ስትፈጽም ከስተቶችህ ለመማር ዕድል አላገኘህም። አይመስልህም?

ሌላው መዋቹ ጠቅላይ ሚስተሩም ሆነ ህወሐት የምትቃወምበት ምክንያት ስትገልጽ “ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት አፍርሰን እንሰራታለን ይሉ ነበር” ጀዋር መሐመድ የተባለ ግለሰብ ደግሞ ፈርሳ ካልተሰራች ዛሬም ነገም ኦሮሞ ነኝ! ኢትዮጵያዊነት እኔን ጀዋር አይወክልም! ኦሮሞም በባዕድ አትገዛም እያለ ነው። እንዲህ ካልሆነ ደግሞ የራሴ የምላትን ሀገር ለመፍጠር እታገለለሁ እያለ ነው። ለዚህ ሰው መልስህ ምንድ ነው? አትላንታ ተገኝተህም እንዲህ ብለህ ነበር “እነ አቶ መለስ ሲናገሩ ምኒሊክን ሲከስዋቸው በሃይል ጨፍልቀው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት እኮ ነው የሚሉት” ጀዋር መሐመድ ደግሞ እንዲህ ይላል “አሁንም ቢሆን ያለው ብሔሮችና የተጨቆኑት ሕዝቦች የራሳቸው ማንነት የገነቡበት ሁኔታ ነው ያለው። ምኒልክ ሲመጣ ያደረገው ምንድ ነው ያንን ለየብቻ ያለ ማንነት ንዶ አንድ የአማራ ባህል ነው በሕዝቡ ላይ የጨነው።”  በዳለስም እንዲህ ብለህ ተናግረህ ነበር “ጥፋትን በመጎተት ቅድምያውን መስመር የያዙት አቶ መልስ ናቸው አሁን ወደሳቸው ልሂድ እኔ የሚመቸኝ ስለሳቸው ስናገር ነው” ጃዋርን ዝም ያልከው ታድያ የጀዋር እምነትና አመለካከት በጋራ የሚያኖረን ሀገር ይገነባል ብለህ ነዋ?

“We are all sufferers from history, but the paranoid is a double sufferer, since he is afflicted not only by the real world, with the rest of us, but by his fantasies as well.”  የታሪክ ተማራማሪ ሪቻርድ ሆፍስታድተር

ይቀጥላል

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልድገብርኤል

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s