አርቲስት ታማኝ በየነ ወዴት አሉ? ጃዋር መሐመድ ይፈልጎታል፡

ግልጹን ለመናገር ያክል ታማኝ በየኔ አሁን ያለህበትና የደረስክበት ደረጃ ያለ መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር እርዳታ የማይታሰብ ነው። አንዳንድ ጊዜም የመዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ወደ ምኒሊክ ቤተ መንግስት መግባትና ያንተ ዝነኝነት ነጣጥሎ ማየት ይቸግረኛል። በሄድክበት ምድር ሁሉም ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መወሳሰብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠያቂ ስታደርግና እንደ መጥፎ ሰውም እየሳልክ ተናግረህ ወደ ቤትህ ስትመለስም በባዶ እጄ ነው ወደ ቤቴ የምመለሰው ብትል ከእኔ ከራሴ ጀምሮ የሚያምንህ ሰው አይኖርም። ከጸሐይ በታች እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ (መዋቹ) ያለ ከፍለህ የማትጨርሰው ውለታ የዋለልህ ሰው አለ ብዬም ራሴን አላታልልም።

ከሰሜን አሜሪካ እስከ ደቡብ አፍሪካ፣ በአውሮፓ ከሎንዶን እስከ ስዊድን ስቶክሆልም፣ ከኖርወይ ኦስሎ እስከ ጀርመን ሙኒክ ሰማይ ሰማይ እያበረረ ዓለም ያዞርህና ያስተዋወቀህ ማን ቢሆን? ማንን ይዘህ? የማን ስም ተሸክመህ? የኢየሱስ እንደማትለኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እንግድያውስ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ ይቅርና የኑሮ ነገርህንም እጠራጠራለሁ በማለቴ እንደማትቀየመኝ አሁንም ተስፋ አደርጋለሁ። ውይ! ለካ አውስትራሊያም ሄደሃል።

ዕለተ ሞታቸው የሰማህ ዕለትም የተሰማህ ስሜት የገለጽከው “ሰውነቴ መቆጣጠር አቃተኝ” ስትል ነበር። በበኩሌ ይህም ስያንሳቸው ነው ባይ ነኝ። እንዴት? እኮ እንዴት? ትለኝ ይሆናል። “ግርም!” አንድ፡ ቀደም ስል እንደገለጽኩት የሳቸውን ያክል ያደረገልህ፣ ውለታ የዋለልህ፣ ዕድል ፈንታህም የሆነ በቀንም በሌሊትም ልትረሳቸው የማይገባ (በጸሎትህ) እንደ መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ያለ ሌላ ማን ቢኖር ነውና? ሁለት፡ ከማንም በላይ የህይወት አጋርህ፣ አለኝታህ፣ ድጋፍና መከታህ አልነበሩም ወይ ብቻ ሳይሆን አሁንም በመንፈሳቸው በሄድክበት ስፍራ ሁሉ ከምላስ ሲተርፉና ሲገላልገሉ አይደል? ተው እንጅ ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ። ታማኝ በየነ አለ ጠቅላይ ሚኒስተር? የሚመራውን ህይወት ሁላ ታየኝ እኮ። እናማ አይደለም መደንገጥና ማዘን ሞታቸውን አስመልክተህ አፍህ ብትዘጋላቸው (ሌላ ቢዝነስ ውስጥ ብትሰማራ) ያንሳቸው እንደሆነ እንጅ ይበዛባቸዋል ብለህ ነው? ለነገሩ እሳቸውም ያለ ዓሳ እንዲሁ አውላላ ሜዳ ላይ ጥለውህ አልሄዱም። ምንም እንኳ የማይቀር ሞት በድንገት ቢወስዳቸው አሁንም ስለ አንተ ማሰባቸውን ግን አልተዉም። ጠቅላይ ሚኒስተሩ በሞታቸውም ቢሆን የህይወት አጋራቸው መንከባከብ: ማክበርና ማንገስ ያውቁበታል። ታድያ ናፍቆት አከሳኝ፣ ቀርቧል ሊገድለኝ፣ በናቅቆታቸው አለቅኩ ደቀቅኩ፣ ናፍቆታቸው ገደለኝ፣ ያለ እሳቸው ነግቶ አይመሽልኝም፣ እህል ውሃ አልጥም አለኝ፣ ቆረጠኝ፣ ፈለጠኝ፣ ጭር አለኝ ማለትህን ተውና “ሰኮናቸውን ይዞ የወጣ” ዓሳ አጥምደህ ህይወትህን ከስብራት ቢዝነስህንም ከኪሳራ ጠብቅ ለማለት እወዳለሁ። (ጨወታው ባመነበት ለወሰነ፡ ወስኖ ለሚሰራ፡ ለሚሰራው የማይፈራ፡ ሲያወራ እምምምም [ቀልድና ፖለቲካ ለየቅል ናቸውና “ከእውነት ጋራ” የምትለዋን እንኳን ስለማትዋጥልኝ ከመቀስ ጋራ በሚል ተክቻታለሁ] አርቲስት ታማኝ በየነ ብቻ ይመለከታል)።

ወደ ቁምነገራችን ስንመለስ አርቲስት ታማኝ በየነ በሞያህ ማለትም በመድረክ መሪነትህ፣ በአዝናኝነት፣ በተጫዋችነትህ፣ በአስተባባሪነትህ፣ በፍጥነትህ አንዳንድ ጊዜም በቅንነትህና በግልጽነትህ አከብርሃለሁ። እኔና አንተ እንደ የአንዲት ሀገር ዜጎች በመጠባበቅ በፍቅርና በተረጋጋ መንፈስ ለመነጋገርና ለመወያየት ምክንያት ወደ ሆነው የሀገር ጉዳይ ያመራን እንደሆነ ቁም ነገሬን አጠር አጠር ባለ መልኩ እንደሚከተለው አቀርባለሁ። በማስቀደም በእርግጠኝነት ላረጋግጥለህ የምፈልገው ቁምነገር ቢኖር ለሳቅና ለጨዋታ፣ በቀልድ መልክም ያቀረብካቸውና የምታቀርባቸው ዋዛዎችህ አዝናኝነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ ጊዜያት በቁምነገር እንደ መከራከሪያ ያነሳሃቸውና የምታነሳቸው፤ ሌሎችንም አምርረህ የምትቃወምበትና አንተም በዋናነት ለበርካታ ዓመታት የምትታወቅባቸው ታሪካዊና ፓለቲካዊ ነጥቦችህ ግን ጊዜው ደርሰዋልና ከብዙ በጥቂቱ ጥቂቶቹ በዛሬው ዕለት ለምርመራ ቀርበዋል። እንደ አስፈላጊነቱ እየታየም ቀሪው ወቅቱና ሰዓቱ በጠበቀ መልኩ ምርመራ ማካሄዱ ይቀጥላል። ሌላው የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ አጀንዳ እስኬ ሌለኝ ድረስ ንግግሮቼ ከዓውዳቸው ውጭ ይተረጉምብኛል ብለህ አንዳትሰጋም ቃሌን እሰጥህ ዘንድ እወዳለሁ።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱትና አንተም ራስህ በተለያዩ ጊዜያት እንደገለጽከው ስልጣን ላይ ያለው/የሚገኘው የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ መንግስት መቃወም የጀመርከው ታጋዮቹ ወደ ከተማ ሳይገቡና ገናም የመንግስትነት በትረ ስልጣን ሳይጨብጡ እንደነበር ነው። ለዚህ አቋምህም በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ምክንያቶችህ ለአድማጮችህ አሰምተሃል። ምክንያትህ ስታስረዳም እንዲህ ብለህ ነበር።

  1. (ሀ) “TPLF የምንቃወመው እኮ እኔ ብቻ አይደለሁም እናንተ ብቻ አይደላችሁም። ከትግራይ የወጡ ኢትዮጵያውያንም’ኮ ይሄ ድርጅት ይዞት የተነሳ ኢትዮጵያን ያጠፋታል ብለው የሚታገሉ የትግራይ ልጆች አሉ። ኤርትራ ሄዳለች እንግዲህ ሄደች ምን እናድርግ። ግን እነሱ (ህወሐት አመራሮች) የሚሉት በኢትዮጵያ ኮሎናዝድ ነበረች ነው የሚሉን። በቅኝ ተይዛ ነበር ነው የሚሉት። ይሄ የTPLF ፕሮግራም ማየት ትችላላችሁ። ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ብለው ነው የታገሉት። (ለ) ቅኝ ግዛት በእኔ በአዝማሪው እውቀት ቅኝ ግዛት ማለት በዛ የሚኖረውን ሕዝብ ከነዋሪው ሕዝብ በታች አድርጎ መግዛት ማለት ነው። ጣሊያን ኤርራትን በያዘ ጊዜ ከ4ኛ ክፍል በላይ መማር አይችሉም ነበር። አይደለም እንዴ? ጣሊያን በሚሄድበት መንገድ መሄድ አይቻልም ነበር። ጣሊያን የሚገባበት ምግቤት ውስጥ አይገባም ነበር። የጃንሆይ ጊዜ ትተነውን በደርግ ጊዜ እኮ ጀነራል ሚካኤል አምዶም የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሆነዋል ለአንድ ወር ይሁን ለ አምስት ቀን ይሁን። ሰው በኮለኒ የያዘውን ሰው ፕሬዝዳንት ያደርጋል እንዴ? አቶ አማን አምደሚካ ኤል እኮ የኮለኔል መንግስቱ ምክትል ነበሩ። ኮሎናዝ ምን ማለት ነው? እንዲህ ዓይነት የታሪክ ብትቶ የሚጽፈው ህወሐት ገና እንቃወመዋለን። (ንግግሩ ያደረግክበት ቦታ በአሜሪካ የካሊፎርኒያ ግዛት በሎስ አንጀለስ ከተማ ሲሆን በዙሪያህም “በኢትዮጵያ ምድር ሰላም ሊመጣ የሚችለው በጠመንጃና በጠመንጃ ብቻ ነው” ብሎ በሚያምን አወዛጋቢ ስብዕና ያለው ግንቦት 7 በመባል የሚታወቀው ጉጅሌ መሪ ከሆነ ግለሰብ ጋር ተገኝተህ ነበር)

በንግግርህ የመጀመሪያ ክፍል የሆነው (ሀ) ስል ያስቀመጥኩት እንመልከት። በዚህ የንግግርህ ክፍል ጠቅለል ባለ መልኩ የተመለከትነው እንደሆነ አንደኛ፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነበረች የሚለውን አባባል አንተ በግልህ እንደማትቀበለውና አለመቀበልም ብቻ ሳይሆን የህወሐት አዲስ ታሪክ እንደሆነ [(ለ) የመጨረሻ መስመር ይመልከቱ]። ሁለተኛ፤ ይህ የህወሐት እምነት ለአንተ ህወሐት በአገር ገንጣይነትና አስገንጣይነት ፈርጀህ ሆኖም ስለታየህ ተቃውሞህን ለማሰማት ተገደሃል። በነገራችን ላይ “ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት” የሚለው እምነት ህወሐት ወደ በርሀ ከመውጣቱ በፊት የነበረና ቀድመው የወጡ የኤርትራ ተወላጅ ታጋዮች እምነት መሆኑን ማወቁ በራሱ ከብዙ ስህተት ይጠብቃል። እያልኩ ያለኹተይ ህወሐት ከሱ በፊት ቀድመው ወደ በርሃ የወጡትን የኤርትራ የፖለቲካ መሪዎች/የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሉትን ተቀብሎ ማስተጋባቱና ለተግባራዊነቱ መረባረቡ ስህተት ሊሆን ይችላል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን  የጥንስሱ ዋና ባለቤትና የታሪክ ጸሐፊ ሆኖ መቅረቡ ግን ከቀድሞ ስህተት ይልቅ የከፋ ስህተት ነው ብዬ ነው የማምነው። ይሁንና ከ 50 ዓመታት በፊት የተነሳ ጥያቄ ነው ወደ ተባለው ወደ ዋና ነጥቢ እናምራ። ጀዋር መሐመድ ይባላል ካልተሳሳትኩ አብረኸው በርካታ መድረኮች ቆመሃል። ግለሰቡ ስለበቀለበት አከባቢ እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያ ታሪካዊ አመጣጥ ሲናገር እንደሚከተለው ይገልጸዋል፥

“ኢትዮጵያ አሁን ያለችው የጋራ ኢትዮጵያ የአንድ መቶ ዓመት ታሪክ ብቻ ነው። ከዛ ሊያልፍ አይችልም። ከዛ በፊት ኦሮሞ የ5000 ሺህ ታሪክ አለው። ወላይታ የ5000/7000 ሺህ ታሪክ አለው። አማራው የዛን ዓይነት ታሪክ አለው። ትግሬው የራሱ ታሪክ አለው። በጋራ ግን ህብረ ብሔር የሆነችው የዛሬዋ ኢትዮጵያ የጋራ ታሪክ አሁን የምናውቃት ኢትዮጵያ ያላት የዚህ የመቶ ዓመት ምናምን ብቻ ነው። አሁንም ቢሆን ያለው ብሔሮችና የተጨቆኑት ሕዝቦች የራሳቸው ማንነት የገነቡበት ሁኔታ ነው ያለው። ምኒልክ ሲመጣ ያደረገው ምንድ ነው ያንን ለየብቻ ያለ ማንነት ንዶ አንድ የአማራ ባህል ነው በሕዝቡ ላይ የጨነው።” ታማኝ፡ ለዚህ መልስህ ምንድ ነው?

ከመቶ ምናምን ዓመታት በፊት ይህቺ አሁን የምናውቃት የብሔር ብሔረሰቦች ድምር/ውጤት የሆነችው ኢትዮጵያ የምትባል አገር ካልነበረች፤ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ የምትባል አገር ደግሞ እንደ ጀዋር አባባልና እምነት ከአማራ ወገን በሆነ በምኒሊክ ለዛውም ስምምነትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን በኃይልና በጉልበት የሌሎች ሕዝቦች ባህላዊ ምንነት በመግፈፍ በጠመንጃ የተገነባች አገር ከሆነች አንተ ህወሐት ብቻ የምትቃወምበት ምክንያት ምንድ ነው? እስከ አሁን ድረስም አንተም ሆንክ ባልደረቦችህ የጀዋርን እምነት/አመለካከት በመቃወም በይፋ ያሰማችሁት የውጣ ቃል የለም ለምን? ግለሰቡ ትክክል ነው ብለህ ስለምታምን ነው ወይስ ሌላ ያልተገለጠልን እንድናውቀውም ያልተፈለገ ምክንያት አለ? ቢኖር ነው እንጅ።

አንተ ስለ ኤርትራ መሄድ አበሳጭቶሃል። ህወሐት “ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት” ብለው መታገላቸውም ለተቃውሞ አብቅቶሃል። ታድያ “ጀዋር በማንነቱ ኦሮሞ እንጅ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም” የሚለው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በምኒሊክ ጡንቻ የተሰራች አገር ናት ብሎ ስለሚያምን ነው። በቀላል አማርኛ ኦሮሞ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት እያለ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የአማራ በተወሰነ መልኩም የትግራይ ማንነት መገለጫ እንጅ ኦሮሞን አይወክልም ብለዋል። ከዚህ በላይ ማብራሪ ለመስጠት መሞከር አንባቢ የመሳደብ ያህል ስለሚሆን ወደ ጥያቄ ልለፍ። እንግዲህ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት አልነበረችም ስትል በምሳሌ እንዳስረዳህ ሁሉ “የለም! ኦሮሞ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት አይደለችም።” በማለት ግለሰቡን (ጀዋር) ለማስተማር ለመከራከርና ለመሞገት ወደኋላ ያልክበት ያቀረቀርክበትና ድምጽህ ያጠፋህበት ምክንያት ምንድ ነው?  የስትንፎርድ ጥይት ፈርተህ ነው? [ጨወታ ሁለት]።

በጠረጴዛ ዙሪያ ወይም በሚድያ በአደባባይ ፊት ለፊት ፕሮግራም ከግለሰቡ ጋር መከራከሩንና መሞገቱን ካላመንክበትና ካልተዋጠልህም መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ታጠቃበትና ትተኩስበት በነበረው አሁንም ባለችው ላፕቶፕ ጀዋርን ለመቃወም ለምን አልደፈርክም? ህወሐትን የተቃወምከው ያክል ይህ ግለሰብ ለምን አልተቃወምከውም? የጀዋር አመለካከትና እምነት የታሪክ ብትቶ ነው ብለህ ታምናለህ አታምንም? የTPLF ሃሳብ ኢትዮጵያን ያጠፋታል ብለህ በማመንህ ብቻ ህወሐት ለመቃወም ከተነሳህ የጀዋር እምነት ደግሞ ኢትዮጵያን አንድ ስለሚያደርግና ስለሚያለማት ይሆን ዝምታን የመረጥከው? አንተም ሆንክ ባለደረቦችህ በዙሪያ ያሉት የጓዳ አርበኞች በዝምታ ዓለም የተዋጣችሁት ምክንያት ምንድ ነው? ተዉ እንጅ ሰው ይታዘበናል ማለትምኮ ጥበብ ነው። ታማኝ “ጸረ የትግራይ ሕዝብ ነው!” ተብሎ ለሚታወቀው ነገር ይህ አጋጣሚ አለ መሆንህን በከፊል የምታረጋግጥበት ዕድል ነው ብዬ ነው የማምነው። ካልሆነ ግን “ታማኝ ጸረ የትግራይ ሕዝብ ነው!” ብለው የሚያምኑ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅት የሚናገሩበት ዕድሉ ቢሰጣቸው ጭብጦቻቸውን ይዘው አባባላቸውን በምስክርነት አስደግፈው የሚያረጋግጡበት አጋጣሚ አለ ማለት ነው።

2. ሌላው ወደ ተቃውሞ ያመጣህ ምክንያት እንደሚከተለው ገልጸኸዋል፥

“የአቶ መለስ ስርዓትና ህወሐት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው እንትን (አመለካከት) መነሻው አንድን ሕዝብ ታርጌት ያደረገ (ያነጣጠረ) በተለይ አማራ የሚባለውን ሕዝብ በጠላትነት የሚፈርጅ ነው።” ደቡብ አፍሪካ ጉዞህ ያደረግከው ንግግርም በተመሳሳይ ያልከው ይህን ነበር “በየትኛው መለኪያ አንድን ሕዝብ እንደ ጠላት ፈርጆ የሚነሳ ድርጅት ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ልንታገለው ይገባል። እኛ በሕዝብ ላይ ጥላቻ ያለውን መቃወም ብቻ ሳይሆን እንታገለዋለን።”

አሁን ደግሞ አቶ ጀዋር መሐመድ የተባለ የኦሮሞ ተወላጅ ግለሰብ ለአማራ ያለውን ፍቅር አብረን አንመልከት፥

“አሁን የምናውቃት ዘመናዊ ኢትዮጵያ የዛሬ መቶ ዓመት ምናምን ነው በምኒሊክ ነው የተገነባችው። ምኒልክ ደግሞ ማን እንደሆነ: የማን ቤዝ ይዞ እንደመጣ: የማን ጦር ይዞ እንደመጣ የታወቀ ነው። … ከህወሃት በፊት የነበሩ መንግስታት ሕዝቡን በመጨፍለቅ አንድ ወጥ የሆነ በአማራ የበላይነት ስር የተገነባ ሀገር ነው መገንባት የፈለጉት ኤክስትራክት ሲያደርጉትም የነበረው አማራውን በዬ ቦታው በመላክ ሕዝብን እያስተዳደረ ሪሶርስ ኤክስትራክት እያደረገ ወደ ማዕከላይ መንግስት ገቢ እንዲያደርግ ነበር የፈለጉት። … አሁን ባለው እኔ ኦሮሞ ነኝ። እኔ መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ አሁንም። አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ የኔን ዓይነት ሰዎችና የኔን ማንነት ኢንተርተይን ሊያደግ የሚችል ዓይነት አይደለም። ራሴን በዛ ውስጥ ማየት አልችልም። በማንነት ደረጃ ከመጣህ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ማንነት ተብሎ የሚቀርበው ነገር እኔን ሊወክለኝ አይችልም። ሁለተኛ ማንነት እስከሌለ ድረስ ዛሬም ነገም ወደፊትም የኔ ማንነት ኦሮሞ ነው።”

ማብራሪያ መስጠት የሚያስፈልገው አነጋገር አይመስለኝም። ግለሰቡ ኢትዮጵያዊነት እንዲህ እንደ መርገም ጨርቅ የተጸየፈበት ምክንያት ምንድ ነው? ብለህ የጠየቅከኝ እንደሆነ ግን ግለሰቡ የኢትዮጵያ ስምና ስመ ዝክርዋ ሲነሳ እንዲህ የሚያመናጭቀው የሚቀፈውና የሚከነክነው አማራ ከመውደዱ የተነሳና በከፊል ደግሞ ለትግራይ ሕዝብ ካለው ፍጹም ፍቅር የመነጨ ለመሆኑ ትስተዋለህ ብዬ አልጠረጥርም። ጥያቄው መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተርና በሊቀ መንበርነት ይመሩት የነበረው ህወሐት ብቻ ለመታገል የመረጥክበት ምክንያት ምንድ ነው? “ይሄ የጠበበ የጎጥ ሃሳብ ይዞ መጥቶ ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ አገር በጎጥ ሂሳብ መመንዘርና ማጥበብ እንዴት ሊሆን ይችላል?” (ከንግግሮችህ የተወሰደ) እንግዲህ ይችላል አይችልም የማለት ስልጣኑ በአንተ እጅ ነው ያለው። በዚ ንግግርህ መሰረት የአንተ ጎጠኝነት ከጀዋር ቀበሌ ተኮር አስተሳሰብ በምን ተለየ? የገረመኝም ይሄ ነው ለሕወሐት “አይቻልም!” እያልክ እዚህ የደረስክ ሰው አሁን ግን የባሰ ሲመጣ ድምጽህ ያጠፋህበት ምክንያት ነው እኔም ያሳዘነኝ። ወይስ ትግሉ አቁመሃል ልበል? ባይሆን መዋቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ሆነ ህወሐት ዕረፍት የነሳሃቸው ምክንያት ንገረን? በሬድዮ እሰማህ ሰው ይህን ያህል ከጠላህ አፍህ ላይ መጥቶ ሲሸናብህ ደግሞ “ተው!” ማለት አቅቶት ስመለከት የዓመታት ልፋትህ አጠራጠረኝ። ጊዜ ይሰጠኝ ከሆነ ደግሞ ጥሩ እስከ መቼ እንደምንጠብቅ ባላውቅም መጠበቃችን ነው።

ይቀጥላል

የጽሑፉ አዘጋጅ እምነትና አቋም በግርድፉ፥

በጃንሆይም ዘውዳዊ አገዛዝ አልተወልድኩም፤ በወታደራዊ የደርግ ዘመነ መንግስትም ነፍሴ አላወቅኩም (ደርግ ሲወድቅ 5/6 ዓመት ልጅ ነበርኩ)። ይህን ግን አምናለሁ፥ በአመጽ፣ በግርግር፣ በሽፍጥ፣ በቆርጠህ ቀጥል፣ በጥላቻ ፕሮፖጋንዳ፣ በሐሰት ምስክርነት፣ ሕዝብን በፈጠራ ዜናዎችና ሐተታዎች በማሰራጨት በማደናገር፣ ውዥንብር ውስጥ በመክተት፣ በማዋከብና በማታለል የሚደረገው ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ የከፋ አዘቅት ውስጥ ይከተን እንደሆነ ነው እንጅ  የሚመጣ ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የሚመልስ ሰላምና ዕረፍት ያለው የብልጽግና ለውጥ  አለ ብዬ አላምን። ትግላችን ሀገርን ለመገንባት ትውልድም ለማነጽ እስከሆነ ድረስና በምድሪቱ እንዲመጣ የምንፈልገውም ለውጥ በዘመናችን እውን ሆኖ ለማየት ባንችልም/ባንታደልም ለለውጥ ከተነሳን ያልቀረ ግን የለውጥ መንገድ የሚያስከፍለው ዋጋ ለመክፈል በተከፈለ ልብ ሳይሆን በሙሉ ልብ፣ ጥቅም ፍለጋ ሳይሆን ፍላጎታችንና ግለ ጥቅሞቻችን መስዋዕት በማድረግ ለመጪው ትውልድ መልካም አርአያ ሆነን ጥሩ ዘርም ዘርተን እንለፍ ነው የእኔ እምነት። ኢሳት በመባል የሚታወቀው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ታጥቆ የተነሳ ጸረ ሀገርና ጸረ ትውልድ የሳይበር ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የምቃወምበት ምክንያትም ይህ ነው።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

E-mail: yetdgnayalehe@gmail.com

United States of America

August 12, 2013

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s