ቀለበት ለቆማጣ ሚዶ ለመላጣ

እኔም ለአንተ ጥያቄ አለኝ፥

“በሌላ በኩል የሙስሊሙን መብት ሳነሳ የእኔን ክርስቲያንነት መጠራጠር ምን ማለት ነው? “ፌዬር” እኮ አይደለም። እኔኮ ክርስቲያን ነኝ። እኔኮ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የማምን ክርስቲያን ነኝ።  እኔን ምን ማለት ነው ሌላ የበለጠ ክርስቲያን ሆኖ “ኮሽን” ሲያደርግህ ትክክል ነው እንዴ?” አርቲስት ታማኝ በየነ

ታማኝ ሆይ! ኃይማኖትን በተመከተ በቅርቡ በአደባባይ እያሳየኸው ከመጣኸው እንግዳና ያልተለመደ ጸባይ የተነሳ ሰዎች በነገርህ ግር መሰኘታቸውን አሳስቦህ ከላይ ከፍ ሲል ያሰፈርኩትን ቃል በታላቅ ቁጣ ተናግረኸል። በበኩሌ ታማኝ በየነ ሰልመዋል፣ ክርስቲያን አይደለም፣ ይከፈለዋል ወዘተ የሚል ተራ አስተሳሰብና አመለካከት እንደሌለኝ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ማለቱ በራሱ አግባብነት እንደሌለው “የሙስሊሞች ጥያቄ የፖለቲካና የስልጣን ጥያቄ” ነው በሚል ጽሑፌ ሰፋ ባለ መልኩ የግል አቋሜን ግልጽ ማድረጌ የሚታወስ ነው። እኔ የምለው እንደ አንድ ዜጋ በቅርቡ አንተን ጨምሮ ኢሳትን በመጠየቄ ሌላ ስም የሚያሰጠኝና ከዚህ ቀደምም ጽሑፎቼ በስፋት ይስተናገዱበት የነበሩት ድረ ገጾች እንዳይነበቡ መታገዴስ ምን ይባላል? ለመሆኑ አርቲስት ታማኝ በየነ ከአገር አገር የምትዞረው የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለማፈንና ለማሳፈን የሚያስችል “ኪነ ጥበባዊ” ስልጠና ለመስጠት ሆነ እንዴ? እውነት ለማየት የምትናፍቃት ኢትዮጵያ ይህ ነው የምትመኝላት? ለመሆኑ ኢሳት እንደ “ታቦት” አንተ ደግሞ እንደ “መልዓክ” መንካትና መጠየቅ ያልተቻለበት ምክንያት ምንድ ነው? በውኑ ኢሳትም ሆነ አንተ በግልህ ስህተት አያውቀንም! የለም አናጠፋም! ብላችሁ ነው የምታምኑ? ወይስ ብንሳሳትም ብናጠፋም ማን አባቱ ያበደ ነው የሚጠይቀን ነው ነገሩ?

የጽሐፉ ዓላማ፥ 

አንደኛ፡ “አላህ አክበር ማለት እግዚአብሔር ታላቅ ነው ማለት ነው” ለሚለው የአርቲስት ታማኝ በየነ አፍላ እውቀት “አላህ” ተብሎ የሚታወቀው የቁርዓኑ አምላክ ራሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ከገለጠ ከእግዚአብሔር ጋር ምንም አይነት አንድነትም ሆነ መመሳሰል እንደሌላቸው ለተናጋሪውና ለደጋፊዎቹ መጠነኛ ገለጻ/ማብራሪያ ለመስጠት፤

ሁለተኛ፡ ታማኝ በየነ የክርስትና እምነት አስተምህሮ ከማንኳሰስና መጠቀምያ ከማድረግም እንዲቆጠብ ተጻፈ።

ማሳሰቢያ:

የጽሑፉ አዘጋጅ በኃይማኖት እኩልነት ያምናሉ። የዜጎች ማንኛውም ዓይነት የአምልኮ ስርዓት ወግና ልማድም በተመለከተ ምንም ዓይነት ቅሬታም ሆነ ጥላቻ የላቸውም። የራሱን ሜዳ ትቶ በሰው ሜዳ ለመጫወት የሚሞክር ገፍቶ የሚመጣ የኃይማኖት ተቋም የተስተዋለ  እንደሆነ ግን (ከዚህ ቀደም ሳይኖር ቀርቶ አይደለም) ጸሐፊው እኩልነት የሚያሳዩበት መንገድ አንዱ እምነታቸው ግልጽና ቀጥተኛ በሆነ ቋንቋ በማንጸባረቅ ነውና በዚህም ቅር የሚሰኝ የኃይማኖት ተቋምም ሆነ ኃይማኖተኛ ግለሰብ ይኖራል ብለው አያምኑም።

የጽሑፉ ውስንነት፥ 

“አላህ አክበር ማለት እግዚአብሔር ታላቅ ነው ማለት ነው” ለሚለው የአርቲስት ታማኝ በየነ እምነትና አነጋገር በተናጋሪው የእምነት የመረዳት አቅም ልክና እንዲሁም መድረኩን ማዕከል ያደረገ ትርጓሜና መሰረታዊ (101) ትምህርት ለማስቀመጥ ተሞከረ እንጂ የጠለቀ ምሁራዊ ወይንም ደግሞ ሥነ መለኮታዊ ዝርዝር ትንታኔ አያካትትም።

ሐተታ፥

“አላህ አክበር ማለት እግዚአብሔር ታላቅ ነው ማለት ነው” አርቲስት ታማኝ በየነ

ታማኝ ደጋግመህ “በኢየሱስ አዳኝነት የማምን ክርስቲያን ነኝ” ብለህ ስታበቃ ማይክራፎን በእጅህ በጨበጥክ ቁጥር ደግሞ “ተክቢ! ተክቢ! ተክቢ! አላህ አክበር! አላህ አክበር! አላህ አክበር!” እያልህ በመጮህ ከፍተኛ ታዋቂነት እያተረፍክ መጥተሃል። በዚህ ድርጊትህ ስንቱ የክርስትና እምነት ተከታይ እንደሚደሰትብህ ለማወቅ ከተፈለገ ሕዝብ ድምጹን በነጻነት የሚያሰማበት ነጻ መድረክ ሊያስፈልገን ነው። እኔ የምለው ግን አንተ ለእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች ይህ ሁሉ ውለታ ስትውልላቸው ሼኮቹ ለምንድ ነው አንድ ጊዜም ቢሆን “ኢየሱስ ጌታ ነው!” በማለት መጮኽ የተሳናቸው? መልሱ ግልጽና አጭር ነው ይኸውም፥ ሼኩ እዛው በቆመበት ይሞታታል እንጅ ተሳስቶም “ኢየሱስ ጌታ ነው!” ብሎ በአንደበቱ አይመሰክርም። አይውላትም! አያደርገውም! ታድያ አንተ “ተክቢ! ተክቢ! ተክቢ! አላህ አክበር! አላህ አክበር! አላህ አክበር!” በማለት አፍህን የምትከፍትበት ምክንያት ምንድ ነው? ለመሆኑ “አላህና እግዚአብሔር አንድ ናቸው” ብሎ ያስተማረህ ማን ነው? የትኛው የክርስትና እምነት የመጻህፍት አዋቂ ነው ሹክ ያለህ? ለመሆኑ ይህን ሁሉ ስትል ከጎንህ የማይታጡ ሼኮች ይህን አንተ የምትለው አንድነት ተቀብለው ደግመው የማያስተጋቡበት ምክንያት ለራስህ ጠይቀህ ታውቃለህ? “አንድ ነን” ብለው ቢያምኑ ኑሮ “አንተ የምታምነውን እምነት” ማመንና በአንደበታቸውም መመስከር ዳገት የመውጣት ያክል ባልከበዳቸው ነበር። ዳሩ ግን የሚያምኑት እምነትና የሚሰሩትን ስራ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች በመሆናቸው አንተ መጠቀሚያ ከማድረግ ውጭ ራሳቸው ለአልባሌ ፖለቲካ ሲያጎበድዱ አይስተዋሉም። አንባቢ አይመስሎትም?

እንግዲህ “አላህ አክበር ማለት እግዚአብሔር ታላቅ ነው ማለት ነው” ለሚለው እምነትህ/ትምህርትህ አላህ ተብሎ የሚታወቀው የቁርዓኑ አምላክ ራሱን በመጽሐፍ ቅዱስ ከገለጠ ከእግዚአብሔር ጋር ምንም አይነት አንድነትም ሆነ መመሳሰል እንደሌላቸው ለአንተም ሆነ እምነትህ ለሚጋሩ ለደጋፊዎችህ መጠነኛ ገለጻ/ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።

አላህ ማን ነው? አላህ የሚለው ስም “ኢል አላህ” ከሚል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም “አምላክ” ማለት እንደሆነ ብዙሐኑ የሥነ መለኮት የታሪክ ሊቃውንት ይስማማሉ። የታሪክ ሊቃውንቱ አክለው እንደሚገልጹት “አላህ” የሚለው የዓረብኛ ቃል እግዚአብሔር በሚል ቃል ተክቶ በክርስቲያኖች ዘንድ አገልግሎት ላይ እንዲውል የተደረገ ይላሉ ገና እስልምና ከመምጣቱ በፊት እንደሆነም ያስምሩበታል። “አላህ” የሚለው ስም ቅድመ እስልምና በዓረቦች ዘንድ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የጣዖቶች ስም እንደነበረም የሚታወቅ ነው። ለምሳሌ የእስልምና እምነት መስራችና ነቢይ የሆነው መሐመድ የወላጅ አባቱ ስም አብ ዱላህ ሲሆን “አብ ደላህ” ማለት የአላህ አገልጋይ ማለት ነው። ይህ የሚያመላክተው  አላህ የሚለው ስም ቅድመ እስልምና በጣዖት አምላኪዎች ዘንድ አገልግሎት ይውል አንደነበረ ግልጽ መረጃ ሲሆን ቀደም ስል ለመጥቀስ እንደሞከርኩትም የእስልምና እምነት መስራች የሆነው መሐመድ በወቅቱ በዓረቦች ይመለኩ የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው አምልኮ ባዕድ ወደ አንድ በመጨፍለቅ መሐመድ “አንድ አላህ” ወደሚል ድምዳሜ መምጣቱ እንጅ የቁርዓኑ አላህ በተፈጥሮ፣ በባህሪውም ሆነ በውስጠ ሚስጢሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ከገለጠ የአብርሃም የይስሃቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ጋር የሚያመሳስልም ሆነ የሚያገናኝ አንዳች ሥነ መለኮታዊም ሆነ ታሪካዊ ግኑኝነት እንደሌላቸው ሊታወቅ ይገባል። በቀላል አማርኛ አላህ በዓረብኛ እግዚአብሔር በአማርኛ መሆኑን ሳይሆን ቁርዓን አላህ የሚገልጽበት መንገድና መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የሚገልጽበት መንገድ ሰሜን ከደቡብ ምዕራብም ከምስራቅ እንደሚርቅና አንደማይገናኝ ሁሉ ምንም ዓይነት ግኑኝነት ሆነ አንድነት የላቸውም። ነገሩ በቀላሉ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ አርቲስት ታማኝ በየነ ራሱን ለመግለጽ በተጠቀመበት አገላለጽ በመነሳት መጠነኛ ጥያቄዬን ልሰንዝር።

“እኔ ሬከርድ ሊታይ ይችላል አንድም ቀን እንዲህ ቦታ ላይ እኔ እንዲህ ነኝ አልልም ምክንያቱም አይደለሁም (1) እኔ አሁንም ሲመሽ ሲነጋ የሚጠሉኝ የፈለጉትን ያህል ቢሰድቡኝ (2) እኔ የኪነ ጥበብ የመድረክ ሰው ነኝ (3)” (ከአውስትራሊያ መልስ ሀገር በታኝ ትውልድ ገዳይ ከሆነው ከኢሳት ጋር ከተደረገ ቃለ ምልልስ የተወሰደ)

(1) “እንዲህ ነኝ አልልም ምክንያቱም አይደለሁም” እውነት ነው ደጋግመህ “ታውቁኛላችሁ የተደበቀ ታሪክ የለኝም። ታሪኬ ከመድረክ ተጀምሮ መድረክ ላይ ነው የሚያልቀው። በተለያየ ቦታ እንደገለጽኩላችሁ። እኔ ከጥጦ ቀጥሎ ማይክራፎን ነው የያዝኩት። በቃ በመናገር በመጫወት በማዝናናት ነው የምታወቀው።” ከማለት ውጭ እኔም የህክምና ባለሞያ ነኝ፣ መሃንዲስ ነኝ፣ እንዲህ ነኝ ወዘተ ስትል ሰምቸህ አላውቅም። ይህ ግልጽነትህ የሚመሰገንና እንደ ጠንካራ ጎንህም እንውሰደው ቢባል እንኳ ያለ እውቀት የምታደርጋቸው ኃይማኖት ነክ ንግግሮችህ የሚፈጥሩት ክፍተትና ስህተት ማን ኃላፊነቱ ይውሰድ? “አላህ አክበር ማለት እግዚአብሔር ታላቅ ነው ማለት ነው” በማለት መድረክህን ስታሞቅ እየቀለድኩ ወይንም እየተጫወትኩና እያዝናናሁ ነኝ ብለህ ነው የምታምነው? ወይስ እንዲህ ብሎ መናገር የኪነ ጥበብ ሞያ ነው ብለህ ስለምታምን ነው? በአደባባይ ኃይማኖት የማስተማር አቅሙም ሆነ እውቀቱ እንደሌለህ የምታምን ከሆነ ደግሞ ለምንድ ነው ኃይማኖት ነክ ንግግሮችን ለማድረግ የምትደፍረው? ወጣም ወረደ ከዚህ ቀደም ያደረግካቸው ክርስትና ነክ ንግግሮች ሆነ ብለህ ያደረግከው ነገር ሳይሆን በቅንነትና በቅናት ተነሳስተህ የሆነ እንደሆንነ ሲሰራ የማያጠፋና የማይሳሳት ሰው የለምና ቀድሞ ከሰራኸው ስህተት ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ እንደ አንድ የኪነ ጥበብ ባለሞያ ብቻ እናያሃለን የሚል እምነት አለኝ።

(2) “የሚጠሉኝ የፈለጉትን ያህል ቢሰድቡኝ” ስድብ ስለሚለው ቃል ያለህ አመለካከትና ትርጓሜ ባላውቅም በሰውነት የሚጠላህ ሰው ካለ ግን በእውነቱ ነገር ድርጊቱ በወንጀል ባያስጠይቅም ትክክል ነው ብዬ አላምንም።  ከምንም በላይ ሰው በሰውነቱ አይጠላምና ድርጊቱ ስህተት ነው ባይ ነኝ። ይህ በእንዲህ ሳለ ሰው የሚሰራውን ስራ ተከትሎ ሰዎች ለሰውዬው ስራዎች ያላቸው አመለካከት ግን ወደድንም ጠላንም ነገሩ ምክንያታዊ እስከሆነ ድረስ ከጥላቻ ጋር ምንም ዓይነት ግኑኝነት የለውም። ለምሳሌ እኔን ብትጠይቀኝ ራሴን ለማሞኘት ካልሆነ በስተቀር  ጽሑፎቼን የሚያነብ ሰው ሁሉ ይመርቀኛ የሚል እምነት የለኝም። ጽሑፍ ከተጻፈ ጽሑፉ ደልቶትና ተመችቶች የሚመርቅ ሰው እንዳለ ሁሉ በአንጻሩ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የሚራገም ሰው ደግሞ አይታጣም። ይህ ደግሞ የነበረና ያለ ነው። ስለሆነም እኔ በግሌ በአንተ ላይ ምንም ዓይነት ጥላቻም ሆነ የተለየ አመለካከት የለኝም። ጤናማ ሆኖ ያልታየኝና ያልተሰማኝ አመለካከትና አካሄድህ ግን ለመገምገም ምክንያታዊ እስከሆንኩ ድረስ ሃሳብን በሃሳብ የመቃወምና ድምጼን የማሰማቱ ነገር “ጥላቻ ነው!” ተብሎ ከተተረጎመ በእውነቱ ነገር አዝናለሁ ከማለትና የጀመርኩትን ስራ ሳላስተጓጉል ከመቀጠል ውጭ ምንም ዓይነት አማራጭ የለኝም።

(3) “እኔ የኪነ ጥበብ የመድረክ ሰው ነኝ” አንድ ጊዜ ብቻም አይደለም ይህን ቃል በቆምክበት መድረክ ሁሉ ማለት ይቻላል ደጋግመህ ስትናገረው ትስተዋላለህ። ይህን የምትልበት ምክንያት ደግሞ ከማንም በላይ አንተ ታውቃለህ። እኔ የምጠይቅህ ግን አጭርና ግልጽ ጥያቄ  ሲሆን ይኸውም፥ የኪነ ጥበብ/የመድረክ ሰው ሞያና ግዴታ ምንድ ነው? መቼም ጥበቃ ሲባል ጠበቃ ማለት አይደለምና አንድ ሰው የኪነ ጥበብ ባለ ሞያ ነው ሲባል በእርግጠኝነት የግለሰቡ ሞያና ችሎታ ምንድ ነው? ወይስ ደግሞ ኃይማኖት ለመናገር ምን ትምህርት ያስፈልገዋል ብለህ ነው የምታምነው? ለመሆኑ  የኪነ ጥበብ ትምህርትና ስልጠናዎች ምንድ ምንድ ነው የሚዳስሰው? ሙሉ በኩልሄ እግዚአብሔር ብቻ ነው ብዬ ነው።

“Many people, especially ignorant people, want to punish you for speaking the truth, for being correct, for being you. Never apologize for being correct, or for being years ahead of your time. If you’re right and you know it, speak your mind. Speak your mind. Even if you are a minority of one, the truth is still the truth.”  ጋንዲ

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s