ወያኔና “እግዚሐሩ” ምን ለያቸው?

ይሁዳ የስሙ ትርጓሜ ምስጋና ማለት ሲሆን ግለሰቡ በማንነቱ ግን የሚመሰገን ስራ ሰርቶ ያለፈ ዘወትር በመልካም ምግባሩ የሚነሳና የሚወሳ ሳይሆን በአንጻሩ ፍጻሜውን ያበላሸ ሰው ነበር። ወያኔ ማለትም እንዲሁ ‘ወየነ” ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን እምቢ ባይ፥ ተዋጊ፥ አዳኝ (ለባርነት፥ ለጭቆና ወዘተ) በአጠቃላይ እምቢተኛ ማለት ነው። ወያኔ የሚለው ቃል የህወሐት ታጋዮች (ዳግማይ ወያኔ) ሌላ መጠሪያ ስም ሲሆን ተቃዋሚ ተብሎ ከሚታወቀው ካምፕ በፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነቶችም ሆነ በሌሎች በርካታ ምክንያቶች የተለየ አቋም የሚያንጸባርቅ፥ የሚያራምድና የሚያምን ሰው ወያኔ ብሎ መጥራትም በኢትዮጵያ ፖለቲካ የተለመደ ነው። አንድን ሰው “ወያኔ” ተብሎ ሲሰደብ ግን ይህን ከላይ ከፍ ሲል በተመለከትነው የቃሉ ፍቺና ትክክለኛ ትርጓሜ ተከትሎ ሳይሆን ነገሩ ተቃራኒ ሆኖ ነው የምናገኘው ነው። ስድቡ የቃሉ ትርጓሜ ግምት ውስጥ ያስገባ ቢሆን ኖሮ “እገሌ’ኮ ወያኔ ነው” ተብሎ መሰደብም ሆነ መጠራት የማይወድ ማንስ ይኖራል ብለው ነው።

በአንዳንድ ወገኖች “የትርጓሜ መጻህፍት” መዝገበ ቃላት፥ ፖለቲካዊ ትንተናና እውቀት ወያኔና እግዚሔሩ በስልጣን፥ በህልውና አልፎ አልፎም በአካል አንድነታቸውን እንጂ ልዩነታቸውን ለማየት አይቻልም። ወያኔ ብሎ እግዚሐሩ ነው እግዚሐሩ ብሎ ወያኔ ነው። በሁለቱም መኸከል ልዩነት ብሎ ነገር የለም። ነገሩን ላብራራው። ፈጣሪ (እግዚአብሔር) ከፍጡር (ከሰውም ከመላዕክትም) ተለይቶ ከሚታወቅባቸው ማንም የማይጋራውና የባህሪው መገለጫ ከሆኑ መካከል ለጊዜው ሦስት ነጥቦች ላንሳ። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሰረት ሁሉን ማወቅ፥ ሁሉን ማድረግ፥ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ መገኘት የሚችል አንድና አንድ ብቻ ሲሆን ስሙም “ብዙዎቻችን” የምናውቀው ወያኔ ሳይሆን ብዙዎቻችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅም የዘነጋነው እግዚአብሔር ይባላል።

አማኞች ገጠመኞቻቸው እንዲሁም አስበውና አቅደው የሰሩት ስራ ሳይቀር ሁሉ በሰይጣን የማሳበብና “ሰይጣን አሳስቶኝ ነው” ማለት የተለመደ ያክል ራሳቸውን በተቃዋሚ ጎራ መድበው የሚንቀሳቀሱ ጉጅሌዎችም እንዲሁ በተመሳሳይ ውድቀቶቻቸውና ሽንፈቶቻቸውን በወያኔ ማላከክ የተለመደ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈጥሩት  ችግር ተጠያቂ ወያኔ ነው አሜሪካና አውሮፓ ለሚፈጥሩት ችግርም ተጠያቂ ወያነ ነው። ኢሳት ስቲድዮ ስር ውስጥ ሲባቆሱም ይህን ያደረግ ወያኔ ነው፥ በስፖርት ፌደረሽን ሜዳ ሲባሉም ተጠያቂው ወያኔ ነው። ብቻ ምን አለፋዎት ላጤዎች ቢጠኑ “አንዳላገባ ዕንቅፋት የሆነኝ፣ ትዳሬን የበተነብኝ፣ እንዳልወልድ ያመከነኝ ወያኔ ነው ብሎ የሚያጉረመርምም አይታጣም። ይህን ያህል ሃይል ያለውና በ እያንዳንዳችን ጓዳ ያሻውን የሚያደርግ ሰው የፈጠረው ፈጣሪ ነው።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሰባሰብም ሆነ እርስ በርስ ተናቁረው መለያየት ተጠያቂው አሁን “ሁሉን ማድረግ የሚችል፥ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ በሙላት መገኘት የሚችልና ሁሉን የሚያውቅ” ወያኔ ነው። ድህረ ምርጫ 97 ወደ እስር የወረዱ መሪዎች መፈታት ተከትሎ የተከሰቱ አስገራሚና አስደንጋጭ ክስተቶች ለሁላችን ግልጽ ይመስለኛል። “መንፈስ ነው” ተብሎ ሲነገርለት የነበረና ተመናፍሶ የብዙሐን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ልብ በሰበረ ጉዳይም ተጠያቂ ወያኔ ነበር። መሪዎቹ ሳያፍሩ “ያፈራረሰን ወያኔ ነው፥ የፈራረስነው በወያኔ ሰርጎ ገብነት ነው፥ ለመፈራረሳችን ምክንያት የሆነው እገሌ ከወያኔ ጋር አብሮ ነው” ተብሎ ሲነገር አሜን ብሎ ከመቀበል ያለፈ አንድም ሰው ተነስቶ እናንተስ የማን ጎፈሬ ስታበጥሩ ነበር? ብሎ የጠየቃቸው የለም። በተፈጠሩ ችግሮች በሙሉ ወያኔን ተጠያቂ ከማድረግ ያለፈ አንድም ቀን ስህተቱ የእኔ ነው በማለት ኃላፊነት የወሰደ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ሰምተንም አይተንም አናውቅም። እውነት ነው ውሸት?

የጽሑፉ ዓለማ፥

የሃሳብ ልዩነት ተከትሎ በዜጎች መካከል እየሰፋ እየመጣ ያለና አሳሳቢነቱ ከምን ጊዜም በላይ እየጨመረ የሚገኘው በተለይ “እኛ የምንለው ካላደረግክና ካላልክ፥ እኛ ባበጃጀነው መንገድ ካልሄድክ፥ እኛ እንደምንፈልገው ካልሆንክና የእኛ ድምጽ ካላስተጋባህ፥ እኛ የምጮኸውን ዓይነት ቅላጼ ካልጮህክ፥ እኛ የደገፍነው/የምንደግፈው ካልደገፍክ፥ እኛ የተቃወምነው/የምንቃወመው ካልተቃወምክ” እየተባለ በዜጎች ሕጋዊ መብትና ስራዎቻቸው ላይ እየደረሰ ያለው ሃሳብህን በነጻነት የመግለጽ አፈና  እንዲሁም የስም ማጥፋት ዘመቻ አቤት ለማለት ተጻፈ።

ሐተታ፥ 

በጽሑፉ መግቢያ በመጠኑም ቢሆን እንደ ተመለከትነው “ተቃዋሚ ነኝ” በማለት ራሳቸው በሚጠሩ ግለሰቦች እምነትና አስተሳሰብ ወያኔ ማለት ዓለምን እንደ ወረቀት ጠቅልሎ ማሳለፍ ከሚችለው መንፈስ ከሆነው ከእግዚአብሔር በምንም ዓይነት መልኩ የማይተናነስ ህልውና ያለው የፖለቲካ ድርጅት ነው። በተቃዋሚዎች መንደር መዝገበ ቃላት ወያኔ ማለት የማያውቀውና የማይችለው ከዕይታዉም የተሰወረ አንዳች ነገር በምድር ክበብ ላይ የተቀመጠ ገዢም ነው። ታድያ እንዲህ ካለ መንደር ሰፈርተኞች አይደለም እንደ ግብጽ በሁለት ዓመት ውስጥ ሁለት መንግስታት ሊቀያይሩ ይቅርና በሃያ  (20) ዓመት ውስጥ አንድ ተብሎ ሁለት የማይባል የሚታይ ስራ ባይሰሩ ምን ይደንቃል?

እንግዲህ እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች ናቸው እንደ አሽክላ ተቀምጠው የሚሰራውን ሰው ጠልፈው ለመጣልና ለማደናቀፍ እንቅልፍ እያጡ የሰውን ስም ሲያጠፉና ያለ ስሙ ስም ሲሰጡ የምናገኛቸው? ግን እስከመቼ? እስከ መቼ ነው  ልዩነትን በልዩነት ተቀብለን ልዩነት ለማጥበብና ለመፍታት ራሳችንን የማንሰጠው? አንድ ሰው የተለየ ሃሳብ የሚያራምድ ሆኖ ከተሰማን እንኳ በሃሳብ የማይመስለን ሰው አለ ስሙ ስም በመስጠት ከማሸማቀቅና ከማሳደድ ተቆጥበን ሃሳብን በሃሳብ ለማሸነፍ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን የምንከራከርበት ዘመን መቼ ነው? የተለየ ሃሳብ ያለው ግለሰብ ሁሉ ወያኔ ነው ተብሎ ከተገለለና ከተነጠለ፥ ሀገሬ ሕዝቤ የሚል ዜጋ ሁሉም ወያኔ ነው እየተባለ በገባበት እየገባን የምናሳድደው ከሆነ ወያኔ ያልሆነ ታድያ ማን ነው? ዓይንህን ጨፍነህ ስትሄድ ያደናቀፈህ ድንጋይም ሁሉ በወያኔነት መፈረጅ ግን መፍትሔ ነው ብዬ አላምንም። ብናስብበት ነው የሚሻለው።

በመሰረቱ ሰው የሚያምንበት መንገድ ተከትሎ ሃሳብ በመስጠቱና በመሰንዘሩ ብቻ ለእሱ የማይገባና ያልተገባ ስም ሊሰጠው ይገባል ብለው ያምናሉ? ወያኔ ራሱስ ቢሆን እንኳን ደህንና መጣ ተብሎ በሚንሸራሸረው ሃሳብና አመለካከቶች ከተሸነፈ ተምሮ አቋሙን እንዲለውጥ ይበረታታል እንጂ እንዴት ነው ሰው እኔ የምለውን ካላልክ፥ እኛ በምንፈልገው መንገድም ካልተሰለፍክ እየተባለ ያለ ስሙ ስም ተሰጥቶት እንዲገለል የሚፈረድበት? ያልሆነ ስም ከመስጠትና ከማፈን ይልቅስ አንጻራዊ ሀሳብ ያለው እኩል ዕድል በመስጠት የዜጎች አመለካከትና ሃሳቦች በማፋጀትና በማፋጨት አሸናፊው የብዙሐን ድምጽ ሆኖ እንዲወጣና እንዲሆን ማድረጉ አይሻልም ነበር? ይህ ሊሆን ያልቻለበት፥ ያልተፈለገበትና የማይፈለግበት ምክንያትስ ምንድ ነው? በአሁን ሰዓት በእስር የሚገኙ ወገኖች ደመወዝ ይህ ነው? ክፍያቸው ይህ ነው? ለዚህ ነው የታገሉት? ለዚህ ነው ወደ እስር የወረዱት? ለዚህ ነው ቤተ ሰቦቻቸው የበተኑ? እየሆነ ያለው የሰሙ እንደሆነስ ምን ይሉ ይሆን? በጣም አዝናለሁ።

በበኩሌ ጽሑፎቼ ለንባብ እንዳይበቁ በድረ ገጾች የተወሰደው እርምጃ ኢሳት ለምን ተነካ ነው። እንዲህ ያለ አሳፋሪ ድርጊት ደግሞ በየትኛው መመዘኛ እርምጃው ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ያልገባኝ ነገር ቢኖር ግን ኢሳት ግድፈቶቹን እንዲያስተካክል ከመምከር ይልቅ የእኔ ጽሑፎች ማፈን እንደ አማራጭ መወሰዱ ነው። ይህ ሁሉ ጭኸትና ግርግር ምኒሊክ ቤተ መንግስት የተገባ ዕለት የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለማፈን ነው እንዴ? ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የዜጎች ሃስብን በነጻነት የመግለጽ መብት አይጠብቅም አምባገነን ነው ተብሎ ብዙ ሲከሰስ እንሰማለን ይህስ ምን እንበለው ጎበዝ? ወይስ “በጥቂቱ ያልታመነ በብዙ አይሾምም” ሲባል አልሰማችሁም?

ደግሞስ ለምን ተነካሁ ብሎ ቋንቋ ምንድ ነው? ኢሳት ለምን ተነካ ማለት ምን ማለት ነው? በኢሳት ዙሪያ የተሰባሰቡ ሰራተኞች ራሳቸውን እህል ውሃ የሚመግቡ ሰዎች አይደሉም ወይ? ወይስ ምስጋና ምግብ የሆናላቸው ከመላዕክት ነገድ መሆናቸው ነው? መነካት የማይፈልግ ሰው ካለ ተካፍላ እኩል የምትደርሰን ሀገር በማስመልከት አፉን አለመክፈት ነው። አይመስሎትም? በአንድም በሌላም አንድ ሰው እንኔን ወክሎ የልቡን አድርሶ ሲያበቃ ግን እኔ ደግሞ እሱን የማልጠይቅበት ምክንያት ምንድ ነው? ኢሳት ባንዴራ እያውለበለበ  በዋኅን ዜጎች ኪስ ውስጥ ሲገባ የማይጠየቅበት፣ ልክ ልኩን የማይነገርበት ምክንያት ምንድ ነው? ማን ነን ብለው ስለሚያስቡ ነው?

ለመሆኑ ኢሳትን አለመደገፍ፥ ስታችሁ እያሳታችሁ ነውና ተዉ ማለት፥ ኢሳት ሆይ! አካሄዳችሁ ማንንም የማይበጅ ግልጽነት የጎደለበትና የማይታይበት መሰሪነት ነውና ነገራችሁን አስተካክሉ ማለትስ እንዴት ቢተረጎም ነው በወያኔነት የሚያስፈርጀው? ኢሳትን መቃወም ማለት እንዴት ነው አንድን ሰው ያለ ስሙ ስም የሚያሰጠው? ለመሆኑ አንድ ዜጋ ወያኔ ላለመባል ምንድ ነው ማድረግ ያለበት? ምን እንዲመስል ነው የሚጠበቅበት? ሰው ወያኔ ላለመባል ሰውኑቱን ለሌላ አሳልፎ መስጠት አለበት ነው? በእውነቱ ነገር ኢሳትን መቃወም ሌላ ስም የሚያስጥ ከሆነ ከተሰጠኝም በላይ ሌላ ስም ቢሰጠኝ መቃወሜን እገፋበታለሁ እንጅ ከሰው አንደበት የሚወጣ ቃላት ፈርቼ ወደኋላ የምልበት አንዳች ምክንያት የለኝም። እስከ አሁን በሰራሁት ስራ ውጤታማ ነኝ። ከነ አባባሉም “የሽ ፍልጥ ማሰርያው ልጥ” እንዲሉ ስትድዮን ለማፍረስ ስትዲድዮን ማቋቋም አይጠበቅብኝም የጽድቅና የእውነት ቃል የሚፈጥረው ተጽዖኖ በመጠቀም ሸፍጠኛ አንድ ቦታ ላይ እስኪያቁም ድረስ አመጸኝነትን መቃወም እገፋበታለሁ።

በተረፈ ሙሉጌታ ይህን የሚያደርገው የጨለማ መንግስት ተወካይ (Agent of Satan) አቦይ ስብሃት፥ መልኩ ጥቁር ተግባሩ ጥቁር ትግርኛ ተናጋሪ ደርግ አባይ ወልዱ፥ እንዲሁም ማንነታቸው በውል የማይታወቅ ስመ ትግርኛ ተናጋሪዎች ደብረ ጽዮን፥ በረከት ስምዖን፥ ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ሌሎችም የአማራና የኦሮሞ ሊሂቃን በመደገፍ ነው የሚል ወይም ደግሞ ብሎ የሚያምን ሰው ካለ አእምሮውን የጣለ አልያም በጥላቻ ልክፍት የተለከፈ ግለሰብ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ከተራ ውንጀላ ያለፈ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።

ሰው ምን ያህል ጥላቻ ቢሰለጥንበት ነው እኔን የትግራይ ገበሬዎች በማዳበርያ ፈንታ የቤቶቻቸው ቆርቆሮ እየተነቀለ መጠሊያ አልባ እያደረጉ የሚገኙ ሊሂቃን በመደገፍ የሚፈርጀኝ? እንዴት ነው “የእነዚህ ግለሰቦች ዕድሜ ለማራዘም ነው የሚጽፈው” ተብዬ የምከሰሰው? ምን ቢፈጠር ነው የገዛ ስጋቸውን ስጋ የሚበሉ ሰብዓዊነት ያልፈጠራቸው ነፍሰ በላዎች አፍና እጅ ሆኜ የምተጋው?

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s